ብርቱካናማዎቹ በካርሎስ ዳምጠው ግሩም ግብ ሻሸመኔ ከተማን 1ለ0 በመርታት የመቀመጫ ከተማቸውን ቆይታ በድል አጠናቅቀዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ድሬዳዋ ከተማ እና ሻሸመኔ ከተማ ተገናኝተው ብርቱካናማዎቹ ከወላይታ ድቻ ጋር 1-1 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ፣ ኤልያስ አህመድ ፣ ሄኖክ አንጃው ፣ ሙኸዲን ሙሳ እና አሜ መሐመድ በዳግማዊ ዓባይ ፣ ሱራፌል ጌታቸው ፣ ሄኖክ ሀሰን ፣ ያሬድ ታደሰ እና ዘርዓይ ገብረሥላሴ ተተክተው ገብተዋል። ሻሸመኔዎች በአንጻሩ ከወልቂጤ ጋር ያለ ግብ ከተለያዩበት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ጌታለም ማሙዬ ፣ አሸናፊ ጥሩነህ እና አብዱልከሪም ቃሲም ያሬድ ዳዊት ፣ ሀብታሙ ንጉሤ እና ስንታየሁ መንግሥቱን ተክተው ገብተዋል።
10፡00 ሲል በዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በሻሸመኔ ከተማዎች በኩል ቅድሚያም በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ያካተቱት ገዛኸኝ ደሳለኝ ትጥቅ ረስቶ በመምጣቱ በምንተስኖት ከበደ ለመተካት የተገደዱት ( ከሳምንታት በፊት የሀዲያ ሆሳዕናው ሰመረ ሀፍተይ ማልያ ረስቶ በመምጣቱ በሳሙኤል ዮሐንስ መተካቱ የሚታወስ ነው ) ሻሸመኔዎች በሰኮንዶች ውስጥ ፈጣን እንቅስቃሴ አድርገው በአሸናፊ ጥሩነህ አማካኝነት ግብ ቢያስቆጥሩም አጥቂው ከጨዋታ ውጪ የነበረ በመሆኑ ጎሉ ተሽሮባቸዋል።
ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ግለት የመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች 4ኛው ደቂቃ ላይ በአቤል አሰበ ካደረጉት ሙከራ በኋላ 23ኛው ደቂቃ በሙኸዲን ሙሳ አማካኝነት ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ ሲመለስባቸው 33ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ካርሎስ ዳምጠው ከራሱ የግብ ክልል በረጅሙ በተሰነጠቀለት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
በቁጥር እየበዙ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ መታተራቸውን የቀጠሉት ብርቱካናማዎቹ በካርሎስ ዳምጠው እና አሜ መሐመድ ተጨማሪ ሙከራዎችን ማድረግ ሲችሉ 45+4ኛው ደቂቃ ላይ ወሳኝ ግብ አግኝተዋል። ሙኸዲን ሙሳ ከግራ መስመር ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ካርሎስ ዳምጠው ከሳጥን ውጪ በአስደናቂ ሁኔታ በግራ እግሩ አክርሮ በመምታት መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ጨዋታውን በጀመሩበት ግለት መቀጠል ያልቻሉት ሻሸመኔ ከተማዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ለጥቂት ደቂቃዎች ተጭነው መጫወት ሲችሉ 45+6ኛው ደቂቃ ላይ ንጹህ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዋል። በዚህም ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ያሻገረለትን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው አሸናፊ ጥሩነህ ኳሱን ተቆጣጥሮ አንድ ተከላካይ በማለፍ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ አድኖበታል በዚህም ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ጨዋታውን በተሻለ ግለት መጀመር የቻሉት ሻሸመኔዎች 51ኛው ደቂቃ ላይ በካርሎስ ዳምጠው አማካኝነት ሙከራ ካስተናገዱ በኋላ 53ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ወጋየሁ ቡርቃ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ኢዮብ ገብረማርያም በግንባሩ በመግጨት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ በድንቅ ቅልጥፍና አውጥቶበታል።
መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋቾች ቅያሪዎችን በማድረግ በጨዋታው ብልጫ ለመውሰድ ጥረት ቢያደርጉም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለማየት ግን እስከ 76ኛው ደቂቃ ድረስ መጠበቅ ግድ ሆኗል። በተጠቀሰው ደቂቃም ካርሎስ ዳምጠው እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ከሳጥን ውጪ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ቢሞክርም ተመልሶበታል። በዚህኛው አጋጣሚ ግብ ጠባቂው በአጋማሹ ተቀይሮ የገባው አቤል ማሞ ነበር።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የጨዋታው ፍጥነት እየጨመረ ሄዶ ድሬዳዋ ከተማዎች 79ኛው ደቂቃ ላይ በሱራፌል ጌታቸው ከፈጠሩት የግብ ዕድል በኋላ 82ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ አግዶበታል። ሆኖም በአንድ ደቂቃ ልዩነት ሻሸመኔዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ኢዮብ ገብረማርያም ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ በድንቅ ቅልጥፍና አግዶበታል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በብርቱካናማዎቹ በኩል 90ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ካዳነበት ኳስ እና በሻሸመኔ ከተማ በኩል ደግሞ 90+6ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ ገብረማርያም ያደረጋት ቀላል ሙከራ ውጪ ውጤት ቀያሪ ክስተት ሳይፈጠር ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች ቡድናቸውን በቅጣት ምክንያት ከ10 ጨዋታዎች በኋላ የመሩት የሻሸመኔ ከተማው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ እንደ ቡድን ቡድናቸው መስተካከል እንዳለበት ጠቅሰው ያሉበት የወራጅ ቀጠና ሜዳ ላይ ከሚያሳዩት እንቅስቃሴ አንጻር የሚመጥን እንዳልሆነ ሲገልፁ ለገዛኸኝ ደሳለኝ የተሠራለት ማልያ ለጨዋታው ባለመድረሱ ተጫዋቹ ከቋሚ አሰላለፍ እንዲወጣ ምክንያት እንደሆነው አሳውቀዋል። የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ኮማንደር ሽመልስ አበበ በበኩላቸው በመቀመጫ ከተማቸው የተደረገውን የመጨረሻ ጨዋታ ማሸነፋቸው ደስ እንዳሰኛቸው በመግለጽ ደጋፊዎቻቸውን ለሰጧቸው ድጋፍ አመስግነዋል።