የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ሀ” የ21ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ሲጀምር ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሞጆ ከተማ ሲያሸንፍ ንብ እና ጅማ አባቡና ነጥብ ተጋርተዋል።
ረፋድ 3 ሰዓት ሲል ሞጆ ከተማን ከጅማ አባጅፋር ያገናኘው የመጀመሪያው ጨዋታ በሞጆ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ገና ከጅምሩ በረጃጅም ኳሶች ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ሞጆ ከተማዎች ገና በ5ኛው ደቂቃ ነበር ከማዕዘን ያሻሙት ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጣቸው የፍፁም ቅጣት ምትን አሚር ራህመቶ አስቆጥሮ መሪ መሆን የቻሉት።
ጅማ አባጅፋሮች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ያገኟቸውን ዕድሎች ግን በመጠቀም ረገድ ውስንነት ነበረባቸው ፤ በአንፃሩ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ከፍ ባለ ተነሳሽነት በዛሬው ጨዋታ የተንቀሳቀሱት ሞጆ ከተማዎች በድጋሚ ያገኙትን የፍፁም ምት ኳስ ያሬድ ሽመልስ አስቆጥሮ አጋማሹን 2-0 እየመሩ ማጠናቀቅ ችለዋል።
በአንፃሩ በሁለተኛው አጋማሽ ሞጆዎች በእጃቸው የገባውን መሪነት አሳልፈው ላለመስጠት ጥንቃቄን ጨምረው የተጫወቱ ሲሆን በአንፃሩ ጅማዎች እንደ መጀመሪያው ሁሉ የግብ ዕድሎችን ለመጠቀም የተቸጀሩበት አጋማሽ ሆኖ አልፏል በዚህም መነሻነት ጨዋታው በሞጆዎች የበላይነት ተጠናቋል።
ለዕለቱ ሁለተኛ በነበረው እና በብዙዎች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ በነረበረው ጨዋታ የምድብ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ተከታዩ ኦሮሚያ ፖሊስ በልዑልሰገድ አስፋው ብቸኛ ግብ መርታት ችለዋል።
ሳቢ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥንቃቄ አዘል አጀማመር የነበረው ቢሆንም በ28ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች መሳይ ሰለሞን ያመቻቸለትን ኳስ ልዑልሰገድ አስፋው አስቆጥሮ መሪ አድርጓል።
የተቆጠረችው ግብም የጨዋታውን መልክ ሙሉ ለሙሉ የቀየረች ሲሆን በዚህም ሁለቱ ቡድኖች ይበልጥ አውንታዊ ለመሆን ሲሞክሩ ተመልከተናል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ ከመጀመሪያው አጋማሽ የበለጠ ጥሩ ፉክክር ሁለቱም ቡድኖች ለተመልካች አስመልክተዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥቡን ለማስጠበቅ አልፎ አልፎ ሲያጠቁ ኦሮሚያ ፖሊሶች ግን በኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ይበልጥ አጥቅተው ተጫውተዋል።
በ62ኛው ደቂቃ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ቢኒያም ካሳሁን ከርቀት የመታትን ኳስ የኦሮሚያ ፖሊሱ ግብ ጠባቂ በግሩም ሁኔታ ሲያድንበት በኦሮሚያ ፖሊሶች በኩል በአንፃሩ የተሳካ የኳስ ቅብብል ከማድረግ በዘለለ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በበቂ መልኩ በመግባት ሙከራዎችን ሳያደርጉ ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1ለ0 በሆነ አሸናፊነት ተጠናቋል።
የዕለቱ ሶስተኛው በነበረው የ10 ሰዓቱ መርሃግብር ንብን ከጅማ አባጅፋር አገናኝቶ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።
እምብዛም ሳቢ ባልነበረው ጨዋታ ጅማ አባቡናዎች በ9ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ ያገኙትን አጋጣሚ በረከት ታምራት በቀጥታ ወደግብ በመምታት ከመረብ ጋር አገናኝቶ ጅማ አባቡናን መሪ አድርጓል።
በ25ኛው ደቂቃ የንቡ ምስክር መለሰ ርቀት ላይ ሆኖ የመታትን ኳስ የጅማ አባቡናው ግብ ጠባቂ ከመለሰበት አጋጣሚ ውጭ ተጨማሪ ሙከራዎችን ሳንመለከት ጨዋታው ለዕረፍት ያመራ ሲሆን ከመልበሻ ክፍል ጨዋታው ሲመለስ ንቦች ይበልጥ አድገው የቀረቡበት ነበር።
ጅማ አባቡና በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ ወደኋላ አፈግፍገው ውጤቱን ለማስጠበቅ ግዜ የመግደል ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቢስተዋልም ንቦች በ82ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ንክኪ የፈጠሩትን ዕድል ባህሩ ፈጠነ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።