የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የ21ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ሲጀመር ሸገር ከተማ ከተከታታይ ሽንፈት ያገገመበትን ድል ሲያስመዘግብ ነገሌ አርሲ እና ቦዲቲ ከተማ ነጥብ ጥለዋል።
በዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ሸገር ከተማ ቢሾፍቱ ከተማን 2-0 በማሸነፍ ከተከታታይ ሽንፈት በኃላ ወደ ድል ተመልሷል።
በኳስ ቁጥጥር ተሽለው በመገኘት በተደራጀ ሁኔታ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመሄድ ጥረት በማድረግ ጨዋታውን የጀመሩት ሸገሮች በ12ኛው ደቂቃ ዘነበ ከድር ያሻገረለትን ኳስ ፋሲል አስማማው ሞክሮ ወደ ውጪ በወጣበት ኳስ ተጋጣሚያቸውን መፈተሽ ጀምረዋል።ከአምስት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ዘነበ ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ሀይከን ድዋሙ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ሸገርን መሪ አድርጓል።
ከግቧ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ቢሾፍቱዎች በ35ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል አምርተው ዳዊት ሸፈራው ያደረጋት ሙከራ በተከላካዩ ሲሳይ የወጣበቶ ኳስ ለግብ የቀረበ ሙከራን አድርገዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ቢሾፍቱዎች ተሻሽለው በመግባት የጎል እድሎች መፍጠር የቻሉ ሲሆን በተለይ 62ኛው ደቂቃ ላይ አብዱላዚዝ ዑመር ከዳንኤል በኃይሉ የተቀበለውን ኳስ ግብ ጠባቂ አልፎ ያመከነው አስቆጪ እድል ነበር።
ያገኙትን መሪነት ለማስጠበቅ የተጫወቱት ሸገሮች በ80ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን አስተማማኝ ያደረገች ግብ አክለዋል። ቢሾፍቱዎች ለማጥቃት በሚያመሩበት ወቅት የተቋረጠውን ኳስ ዱላ ሙላቱ አግኝቶ ኳሷን ይዞ በመግባት ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር በሸገር 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በዕለቱ ሁለተኛ በነበረው መርሃግብር ነገሌ አርሲ ከኦሜድላ ሁለት አቻ የተለያዩበት ነበር።
ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ እስከ እኩሌታው ድረስ ሙከራዎች ያልተስተዋሉበት ሲሆን 24ኛው ደቂቃ ላይ ነገሌ አርሲዎች ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ትንሳኤ ኑሪ ከመስመር መሬት ለመሬት የተሻገረለትን ኳስ ከተከላካይ ቀድሞ በመምታት ነገሌ አርሲን መሪ አድርጓል።
ግብ ካስተናገዱ በደቂቃዎች ልዩነት ኦሜድላዎች አቻ መሆን ችለዋል ፤ ቻላቸው ቤዛ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ በማስቆጠር የጨዋታውን ውጤት ወደ አቻነት መቀየር ችሏል።
ከአቻነት ግቧ በኋላ ጨዋታው የመቀዛቀዝ ሁኔታ ታይቶበት ወደ እረፍት ሲያመራ ከእረፍት መልስ አርሲዎች ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ 59ኛው ደቂቃ በድጋሚ መሪ ሆነዋል። ከጥሩ ቅብብሎች በኋላ በቃሉ መኩርያ ከመስመር የተቀበለውን ኳስ በቀኝ እግሩ ተቆጣጥሮ በመዞር በግራ እግሩ በጥሩ ሁኔታ አስቆጥሮ ነገሌ አርሲን መሪ አድርጓል።
አርሲ ነገሌዎች ያገኙትን መሪነት ለማስጠበቅ ኳስ ቁጥጥር ላይ አተኩረው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ኦሜድላዎች የአቻነት ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት 77ኛው ደቂቃ ላይ ሰምሮላቸዋል። መነሻውን ከግራ መስመር ያደረገው ኳስ ሰይፈ ዛኪር በጥሩ ሁኔታ ያመቻቸለትን ኳስ ቢኒያም ካሣሁን ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ በማድረግ ጨዋታው ነጥብ በመጋራት ተፈፅሟል።
በዕለቱ የማሳረጊያ ጨዋታ ጋሞ ጨንቻ ከ ቦዲቲ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
በደጋፊዎቻቸው ታጅበው የተጫወቱት ጋሞ ጨንቻዎች በመጀመርያው አጋማሽ ብልጫ በመውሰድ በማትያስ ኤልያስ እና ያሬድ መኮንን አማካኝነት ሙከራዎች ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። ቦዲቲዎች በአንፃሩ የተዳከመ የማጥቃት እንቅስቃሴ አሳይተው የጎል እድሎት ሳይፈጥሩ ያለ ጎል ወደ እረፍት አምርተዋል።
በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቦዲቲዎች ተሻሽለው መቅረብ የቻሉ ሲሆን ጎል በማስቆጠርም ቀዳሚ ሆነዋል። 77ኛው ደቂቃ ላይ ውብሸት ወልዴ ያመቻቸለትን ኳስ ኤፍሬም አበራ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ ቦዲቲን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
የቦዲቲ መሪነት የቆየው ለሦስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። ጨንቻዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ጫና በመፍጠር 80ኛው ደቂቃ ላይ ከሩቅ የተመታውን ኳስ ቦዲቲዎች በአግባቡ ባለማራቃቸው ከሳጥኑ አቅራቢያ የነበረው ያሬድ መኮንን አስቆጥሮ ጨንቻን አቻ አድርጓል። ከጎሉ በኋላም ጋሞዎች ወደፊት በመጫወት ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት ጨዋታው ተጠናቋል።