ብርቱ ፉክክር እና ጥቂት የግብ አጋጣሚዎችን በተመለከትንበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በባሲሩ ዑመር ብቸኛ ጎል ሲዳማ ቡናን 1ለ0 በመርታት የሊጉን መሪነት አጠናክሯል።
ሁለቱም ቡድኖች በ21ኛው የጨዋታ ሳምንታቸው ተጋጣሚዎቻቸውን ባሸነፉበት ወቅት የተጠቀሙትን ቋሚ አሰላለፍ በዛሬው ጨዋታ ላይም ምንም ለውጥን ሳያደርጉ ቀርበዋል።
በኢንተርናሽኛል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ አጋፋሪነት በጀመረው እና ፈጣን የሆኑ አጀማመሮች በተስተዋለበት የምሽቱ ጨዋታ ከነበረው ከፍ ያለ ግለት አኳያ በግብ ሙከራዎች ያልደመቀ ነበር። መሐል ለመሐል በሚፈጥሯቸው ንክኪዎች ሜዳውን በመለጠጥ በጥልቅ አጨዋወት ጠጣር ማጥቃቶችን አዘውትረው የሚጠቀሙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የሲዳማን የመከላከል አጥር አልፈው ከመክብብ ደገፉ ጀርባ የሚገኘውን መረብ ለማግኘት ዕድለኞች አልነበሩም።
ንግድ ባንኮች በቅብብል ወቅት የሚፈጥሯቸውን ስህተቶች በንቃት ነጥቀው በመስመሮች በኩል በይበልጥ የማይክል ኪፕሮልን ፈጣን እንቅስቃሴ በሽግግር አጅበው ይንቀሳቀሱ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ልክ እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ውስንነቶች ተስተውባቸዋል። ሜዳ ላይ በታክቲክ የታጠሩ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ በዝተው ከመመልከት ውጪ አንድም አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራን ያላስመለከተን ጨዋታው ያለ ጎል ለዕረፍት አምርቷል።
ከመልበሻ ክፍል መልስ በቀጠለው ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች ቡልቻ ሹራን በሀብታሙ ገዛኸኝ ለውጠዋል። ንግድ ባንኮች ከፍ ባለ ተነሳሽነት በመስመር አጨዋወት በይበልጥ መንቀሳቀስን መርጠው የነበረ ቢሆንም የግብ ማግባት ጥረቶቻቸው ግን በስልነት መታጀብ ያልቻሉ ነበሩ። ከቆመ ኳስ 57ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ ሳጥኑ ጠርዝ ኤፍሬም ታምራት ለንግድ ባንክ የተሰጠችን የቅጣት ምት ወደ ግብ በቀጥታ መቶ ኳሷ ዒላማዋን ሳትጠብቅ በግቡ ቋሚ በኩል ወጥታለች።
60ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው እንደደረሰ ንግድ ባንኮች ሲሞን ፒተር እና ፉአድ ፈረጃን በረከት ግዛው እና ቢኒያም ጌታቸው ተክተው የማጥቃት ሀይላቸውን በአዲስ ጉልበት ለማደስ ጥረት አድርገዋል። በአጋማሹ መጠነኛ መቀዛቀዞች የታየባቸው ሲዳማ ቡናዎች ፈጠን ባለ የመልሶ ማጥቃት ሽግግር ኪፕሮልን የሚፈልጉ ኳሶችን አዘውትሮ በመጠቀም ጥቃቶችን ለመሰንዘር ቢጥሩም ጥድፊያ እና ጉጉቶች የሚገኙ መልካም አጋጣሚዎችን ወደ ጎልነት እንዳይለውጡ ከማድረጉ በተጨማሪ 76ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ባሲሩ ዑመር ላይ መሐል ሜዳ ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።
ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋቾች ለመጫወት የተገደዱት እና የተጫዋቾች ቅያሪም ጭምር አድርገው የቀጠሉት ሲዳማዎች 81ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ሸዋለም የሰራውን ስህተት ተከትሎ ማይክል ኪፕሮል ከጎሉ ትይዩ ሆኖ ያገኘውን የሚያስቆጭ ዕድል የግብ ዘቡ ፍሬው ጌታሁን አግዶበታል። ጫናን በሚያሳድሩ የኮሪደር እንቅስቃሴዎች የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች የተጫወቱት ንግድ ባንኮች 85ኛው ደቂቃ ላይ ባሲሩ ዑመር ከመሐል ራሱ ያስጀመራትን ኳስ በአንድ ሁለት ወደ ወደ ቀኝ ኤፍሬም ታምራት ደርሳው ወደ ውስጥ ሲያሻግር ጋናዊው አማካይ መረቡ ላይ ኳሷን አስቀምጧት በመጨረሻም ብርቱ ፉክክር የታየበት ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጎል እስኪቆጠርባቸው ድረስ ጥሩ እንደነበሩ ገልፀው የግብ ዕድልን በመፍጠሩ ረገድ ቡድናቸው ደካማ እንደነበር እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ የቁጥር ማነስ በመፈጠሩ ጎል ሊቆጠርባቸው ቢችልም ከሞላ ጎደል ጨዋታው ጥሩ ሆኖ ማለቁን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ በበኩላቸው ማሸነፍ ግባቸው ቢሆንም ከዕረፍት በፊት ተጋጣሚያቸው ስፔስ የማይሰጥ እና ቡድናቸውን መቆጣጠር ላይ አተኩሮ እንደተጫወተ ጠቅሰው በዚህም ደስተኛ አለመሆናቸውን አክለው ከዕረፍት በኋላ ግን ለማሻሻል በትዕግስት ኳስ መቆጣጠር በመቻላቸው ውጤቱ መገኘቱን ተናግረዋል።