የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 21ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን መርሐ ግብር አርባ ምንጭ ከተማ መሪነቱን ያሰፋበትን ድል ሲያስመዘግብ ደብረብርሀን ከተማም አሸንፏል።
በዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ደብረ ብርሀን ከተማ ባቱ ከተማን 1-0 አሸንፏል። የመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ጥሩ ፉክክር የታየበት ቢሆንም እምብዛም የጎል ሙከራዎች የተስተዋሉበት አልነበረም። 17ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ጎል በማምራት ወንድወሰን ሽፈራው የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂ ሲመልሰው አብዱልከሪም መሐመድ አግኝቶ በግንባሩ ገጭቶ ክንዱ ባየልኝ በግንባር በመግጨት ያወጣበት በደብረብርሀን በኩል ሲጠቀስ በ35ኛው ደቂቃ ዝነኛው ጋዲሳ ረጅም ኳስ አሻግሮለት እስራኤል ይዞ በመግባት ቢሞክርም ወደ ላይ የወጣበት በባቱ ከተማ በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።
ከእረፍት መልስ ደብረብርሀኖች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በ67ኛ እና 72ኛ ደቂቃ አብዱልከሪም እና ማሞ አየለ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን ወደ መገባደጃው ጫናቸውን በማጠናከር ድል ያስመዘገቡበትን ጎል አግኝተዋል። በ86ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ኢዮብ አስራት ከአንድ ሁለት ቅብብል ያገኛትን ኳስ በመጀመርያ ንክኪው በማስቆጠር ደብረብርሀንን ሦስት ነጥቦች ማስጨበጥ ችሏል።
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ አርባምንጭ ወደ ድል የተመለሰበትን ሥስት ነጥብ በማስመዝገብ ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያደርገውን ግስጋሴ አሳምሯል።
በዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ የመጀመርያ ሠላሳ ደቂቃዎች የጎል ሙከራዎች እምብዛም አልታዩም ነበር።
ቀው በቀስ ጨዋታው ተጋግሎ 29ኛ ደቂቃ ላይ በፍቅር ግዛቸው በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ሳሙኤል አስፈሪ ያሻገረውን ኳስ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር አርባምንጭን መሪ አድርጓል።
ከጎሉ በኋላ የአቻነት ጎል ፍለጋ ተጭነው የተጫወቱት የካዎች ከአምስት ደቂቃ በኋላ አቻ ሆነዋል። በአንድ ሁለት ቅብብል ሙሉቀን አማኑኤል ለጁንዴክስ አወቀ ከዛም ብስራት ታምሩ የደረሰውን ኳስ ብስራት በጥሩ አጨራረስ አቻ አድርጓል። በ41ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን ሞክሮ ወደ ላይ የወጣበት ኳስም በመጀመርያው አጋማሽ አርባምንጮች በድጋሚ መሪ ለመሆን የተቃረቡበት አጋጣሚ ነበር።
ከእረፍት መልስ አርባምንጮች ተሻሽለው በመግባት ጥሩ አጋጣሚዎች መፍጠር የቻሉ ሲሆን በ54ው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ተገኝ ከእንዳልካቸው የተቀበለውኝ ኳስ መትቶ ግብ ጠባቂ ያወጣበትም ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። ከስድስች ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ መሪሁን መስቀሌ በ60ኛው ደቂቃ አክርሮ የመታው ኳስ ሲመለስ አሸናፊ ተገኝ አግኝቶ መትቶ ግብ ጠባቂ ሲመልሰው አህመድ ሁሴን አግኝቶ በማስቆጠር አርባምንጭን በድጋሚ መሪ አድርጓል።
ከጎሉ በኋላ አርባምንጮች መሪነታቸውን ለማስጠበቅ፣ የካዎችም የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም ተጨማሪ ጎል ሳንመለከት ጨዋታው በአርባምንጭ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉም አርባምንጭ አምስት ጨዋታ በሚቀረው ውድድር በደረጃ ሰንጠረዡ ከተከታዩ ነገሌ አርሲ ያለውን ልዩነት ወደ 12 ማስፋት እንዲችል አድርጎታል።