ብርቱ ፉክክር በተደረገበት የ19ኛው ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ በቸርነት ጉግሳ የፍጹም ቅጣት ምት ግቦች ወልቂጤ ከተማን 2ለ1 አሸንፏል።
በአለልኝ አዘነ ሕልፈት ምክንያት በይደር ተይዞ በቆየው የ19ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ተገናኝተው የሊጉን የ22ኛ ሳምንት ጨዋታ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ያለ ጎል አጠናቀው የነበሩት ባህርዳር ከተማዎች በሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን ያደረጉ ሲሆን በዓባይነህ ፊኖ እና ጉዳት በገጠመው ሙጂብ ቃሲም ቦታ የአብስራ ተስፋዬ እና ሐብታሙ ታደሠን ሲተኩ በኢትዮጵያ መድን በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንታቸው ወቅት ሽንፈት አስተናግደው በነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በበኩላቸው ባደረጉት የአራት ተጫዋቾች ቅያሪ ወንድማገኝ ማዕረግ ፣ ጋዲሳ መብራቴ ፣ ዳንኤል መቅጫ እና ፉዓድ አብደላ አርፈው አዳነ በላይነህ ፣ ተስፋዬ መላኩ ፣ ዳንኤል ደምሱ እና ሳምሶን ጥላሁን ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ምሽት 12፡00 ሲል በዋና ዳኛ ሚካኤል ጠዓመ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወልቂጤዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ተጭነው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ግን በግብ ሙከራ ቀዳሚ የሆኑት ባህር ዳሮች 6ኛው ደቂቃ ላይ በቸርነት ጉግሳ አማካኝነት በግንባር የተገጨ ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ ተይዞባቸዋል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ቸርነት ጉግሳ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው የአብሥራ ተስፋዬ ጥሩ ሙከራ አድርጎ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ተመጣጣኝ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ሲከተሉ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ 29ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለ የግብ ዕድል ፈጥረው ሀብታሙ ታደሰ ከፍጹም ፍትሕዓለው በተቀበለው ኳስ በደረቱ አብርዶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ በጥሩ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል።
እንዳላቸው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ የተስተዋሉት ወልቂጤዎች በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው መድን ተክሉ ከሳጥን ውጪ በድንቅ ሁኔታ የሰነጠቀውን ኳስ ያገኘው ተመስገን በጅሮንድ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የላይ አግዳሚ መልሶበታል።
እጅግ ማራኪ ፉክክር የተደረገበት እና ጥሩ የኳስ ፍሰት ሲታይበት የነበረው ጨዋታ በኋላም ያለ ግብ ወደ ዕረፍት አምርቷል። በሠራተኞቹ በኩል ሄኖክ ኢሳይያስ ባልተለመደ መልኩ በመስመር አጥቂነት ቦታ ላይ ተሰልፎ መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ የጣና ሞገዶቹ ጥሩ አጀማመር አድርገው ቸርነት ጉግሳ በግሩም ክህሎት በርካታ ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ታደሰ በውሳኔ ድክመት ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ወልቂጤ ከተማዎች በጉዳት ምክንያት አዳነ በላይነህን አስወጥተው ጋዲሳ መብራቴን ለማስገባት ሲገደዱ የመስመር አጥቂ ቦታ ላይ ተሰልፎ ሲጫወት የነበረው ሄኖክ ኢሳይያስ ወደ ተፈጥሯዊው የመስመር ተከላካይነት ቦታው ተመልሷል።
ባህር ዳሮች በቁጥር በዝተው በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ ተጭነው መጫወት ሲችሉ 53ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሰ ከቸርነት ጉግሳ የተመቻቸለትን ኳስ ሳይጠቀምበት ከቀረ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሀብታሙ ታደሰ ከፍጹም ጥላሁን በተቀበለው ኳስ የግብ ዕድል ሊፈጥር ሲል ሳጥን ውስጥ በተሠራበት ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ቸርነት ጉግሳ አስቆጥሮታል።
ወልቂጤ ከተማዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በሙሉ የማጥቃት ኃይላቸው መታተራቸውን ሲቀጥሉ 81ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። ተመስገን በጅሮንድ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ፔፔ ሰይዶ ሲመልስበት የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ፉዓድ አብደላ በድንቅ ክህሎት ተከላካዮች አታልሎ ማስቆጠር ችሏል። ግብ አስቆጣሪው ፉዓድ ከጥቂት ደቂቃ በኋላም ጥሩ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ሲመልስበት ኳሱን ያገኘው ተመስገን በጅሮንድ ቢያስቆጥረውም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሯል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ በመጨረሻው ቅጽበት የጣና ሞገዶቹ የፍጹም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ሄኖክ ኢሳይያስ በእጁ በመንካቱ የፍጹም ቅጣት ምቱ ሲሰጥ ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ ከዳኛ ጋር በፈጠረው ሰጣ ገባ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። ሆኖም ቅያሪ በመጨረሳቸው ግብ ጠባቂ ቀይረው ማስገባት ያልቻሉት ሠራተኞቹ ከጌቱ ኃይለማርያም እና መሳይ ጳውሎስ ጋር ካመነቱ በኋላ በመጨረሻም መድን ተክሉን በግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ ለመተካት ተገደዋል። ሆኖም ቸርነት ጉግሳ ኳሱን መረብ ላይ አሳርፎት ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የወልቂጤ የቡድን አባላት ከጨዋታ ውጪ በሚል በተሻረባቸው ጎል ያላቸውን ከፍተኛ ቅሬታ አሰምተዋል።