የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች በ2017 ለተጫዋቾች ደሞዝ እና ኢንሴንቲቭ የሚያወጡት ወጪ ገደብ ተበጀለት።
ዛሬ 9፡30 በሂልተን ሆቴል የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በ4ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተወሰኑ ውሳኔዎችን በተመለከተ ለብዙሃን መገናኛ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በቅድሚያም በረዳት ፕሮፌሰር ጌቱ ደጉ ( ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ) ዳሰሳዊ ሪፖርት ቀርቧል። ያለፉትን አንድ ዓመት ካምፓኒው ከፌዴሬሽን ጋር ሲነጋገሩ እና ከክፍያ መመሪያ ጋር ተያይዞ ሥራዎች ሲሠሩ እንደነበር በመግለጽ የጸደቁ መመሪያዎችን ሲናገሩ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች የክፍያ ስርዓት በመመሪያ አንድ እንደተያዘ እና ከራኒንግ ኮስታቸውን ውጪ ሌሎች በውል ያሉትን ነገሮች ማኔጅ እናድርግ የሚለውን ማሰባቸውን በመጠቆም ያለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ያለውን ዳታ ሰብስበው እንደሠሩ ይህም ተጫዋቾች ሲፈርሙ ያለውን ሕጋዊ ነገር በማየት መሆኑ ተገልጿል። ረዳት ፕሮፌሰሩ አክለውም “በ2017 የኢትዮጵያን እግርኳስ ፉክክር ወደ ሜዳ እንመልሳለን። አሁን ፉክክሩ ከሜዳ ውጪ ነው” በማለት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በበኩላቸው ሊጉ እንደተቋቋመ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ችግር ማስጠናታቸውን እና ጥናቱም መደርደሪያ ላይ እንዳይቀር አሁን አንደኛውን አንኩዋር ጉዳይ መፍትሄ መስጠታቸውን ተናግረዋል። የክለቦችን የፋይናንስ አስተዳደር መልክ ለማስያዝ ተሞክሯል ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው የደሞዝ ግሮዝ ክፍያ ፣ ግሮዝ ሳለሪ እና ኢንሴንቲቭ በ2015 የተፈፀመ ክፍያ እና የ2016 ክፍያ ታሳቢ በማድረግ 52 ሚሊየን ብር ዓመታዊ የተጫዋቾች ደሞዝ እና ኢንሴንቲቭ ወጪ በሚል መወሰኑን ይፋ አድርገዋል። መጠባበቂያ ደግሞ 5 ሚሊየን ሆኖ አጠቃላይ 57 ሚሊዮን እንዲሆን ተወስኗል። ጎን ለጎን አፈፃፀሙ በጽሕፈት ቤቱ የሚመራ ይሆናል ተብሏል።
ይህ ውሳኔ የክለቦቹን የሴት እና ሌሎች የዕድሜ ቡድኖች እንደማያካትት የተነገረ ሲሆን ጥያቄው ከክለቦች የመጣ እንደሆነ እና ሀሳቡን ሙሉ ለሙሉ እንደደገፉት ሲነገር ከክለቡ በተጨማሪ ተጫዋቾችም ተጎጂ ሲሆኑ እንደነበር ተመላክቷል።
የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ወጪ ዓምና ከነበረው ዘንድሮ በ38% ማደጉ የተገለጸ ሲሆን መመሪያው የውጪ የአውሮፖ እና የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መመሪያዎች ተጠንተው የእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ተደርጎበት እንደተሠራ እና “ሌሎች ማኅበራት ያልገቡበት ምክንያት መግባት ስለሌለባቸው ነው” በማለት የተጫዋቾች ማኅበር በውሳኔው ስላለመሳተፉ ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ ተሰጥቶ መግለጫው ተጠናቋል።