የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የ22ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ በሦስት ጨዋታዎች ጅማሮውን ሲያደርግ ነገሌ አርሲ ሦስት ነጥብ አሳክቶ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል።
በእለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ጋሞ ጨንቻን ከባቱ ከተማ አገናኝቶ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ጨዋታው ብዙም የጎል ሙከራ ያልተመለከትንበት እና ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ ያስተዋልንበት ጨዋታ የነበረ ሲሆን ባቱዎች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩ ቢሆኑም ወደ ግብ እድልነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል። በረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት የሞከሩት ቦዲቲዎችም በ16ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ መኮንን አማካኝነት ካደረጉት ሙከራ ውጪ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳንመለከት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደመጀመርያው ሁሉ ሳቢ ያልነበረ ሲሆን ቦዲቲዎች 65ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ከርቀት አክርሮ የመታውን ግብ ጠባቂው ኢያሱ ባዳነበት እና ማቲያስ ኤልያስ ከመስመር የተሻገረለትን በግንባሩ ገጭቶ በሞከረው ሙከራ የተጋጣሚያቸውን ጎል ፈትሸዋል። ባቱዎች በበኩላቸው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ብርሀኑ አዳሙ እና ሚፍታህ ማህቡብ ጥሩ እድሎች አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተው ጨዋታው ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
የእለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በውዝግቦች ታጅቦ ተካሂዶ ነገሌ አርሲ ቦዲቲ ከተማን 1-0 ማሸነፍ ችሏል።
ጥሩ አጀማመር በማድረግ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት አርሲዎች ወደፊት በመሄድ ገብረመስቀል ዱባለ ቢሞክርም ግብ ጠባቂ አውጥቶበታል። በቦዲቲዎች በኩል በመልሶ ማጥቃት 21ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ቆልቻ ቁጥሩ ከመስመር ያሻገረለትን ኤፍሬም አበራ ቢመታም ግብ ጠባቂው አውጥቶበታል።
42ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት የተጣለለትን ኳስ ትንሣኤ ኑራ ከተከላካዮች አምልጦ በመውጣት በጥሩ አጨራረስ ነገሌ አርሲን ቀዳሚ አድርጓል። ጎሉን ያስቆጠረው ተጫዋች ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ነበር በሚልም የቦዲቲ ተጫዋቾች ተቃውሟቸውን ገልፀዋል።
ከእረፍት መልስ ቦዲቲዎች የአቻነት ጎል ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ሲሆን 65 እና 72ኛ ደቂቃ ላይ በሳምሶን ቆልቻ አማካኝነት ጥሩ ሙከራዎች ቢያደርጉም ወደ ግብነት ሳይቀየር ቀርቷል። 75ኛው ላይ ደግሞ ነገሌ አርሲዎች በመልሶ ሜጥቃት ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል በማምራት ፍፁም ተስፋማርያም ያሻገረውን የቦዲቲ ተከላካይ በጭንቅላቱ ገጭቶ ለማራቅ ቢሞክርም አቅጣጫ ቀይሮ ቁጥሩ ገብረመስቀል ዱባለ ያገኘውን ኳስ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ አቋቋም በሚል በአጨቃጫቂ ሁኔታ ተሽሯል።
ጨዋታው ቀጥሎ 82ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻማለትን ኳስ ሳምሶን ቆልቻ በእጁ ጎል ለማስቆጠር በመሞከሩ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገደ ሲሆን ቦዲቲዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ ጨዋታው በነገሌ አርሲ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ደሴ ከደብረብርሀን አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታው ደሴዎች የተሻለ አጀማመር በማድረግ የተንቀሳቀሱ ሲሆን ከመስመር ብሩክ ቦጋለ ያሻገረለትን ኳስ የኋላሸት በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው በቀላሉ አድኖበታል።
ጨዋታው ቀጥሎ 33ኛው ደቂቃ ላይ የደብረብርሀኑ መሐመድ ሻፊ በሰራው ጥፋች በሁለት ቢጫ ከሜዳ የተወገደ ሲሆን ደብረብርሀኖች ከወጣባቸው በኋላ ጥሩ ተንቀሳቅሰው ለማጥቃት ወደፊት በመሄድ በደሴ ሳጥን ውስጥ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ 35ኛው ደቂቃ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት የተሻ ግዛው አስቆጥሮ መሪ ሆነዋል።
ደሴ ከግቡ መቆጠር በኋላ ጥሩ በመንቀሳቀስ ጎል ፍለጋ ተጭነው መጫወት የቻሉ ሲሆን 44ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ አብዱሰላም ይዞ በመግባት ያመቻቸውን የኋላሸት ሞክሮ ግብ ጠባቂው ወደ ውጪ ወጥቶበታል። የተገኘው የማዕዘን ምት ተሻምቶ በተከላካዮች ሲመለስም ፍፁም ተስፋዬ አግኝቶ በማስቆጠር ደሴን አቻ አድርጓል።
ከእረፍት መልስ ጨዋታው በጥሩ ፍሰት ቢከናወንም እምብዛም ሙከራ ያልተስተዋለበት ሆኗል። በጎዶሎ ቁጥር ቢጫወቱም ተቋቁመው ለመውጣት ጥረት ያደረጉት ደብረብርሀኖች በመጨረሻ አሸንፎ ለመውጣት ተቃርበው የነበረ ሲሆን 85ኛው ደቂቃ ላይ አብርሀም ምህረት ከግብ ጠባቂ ተገናኝቶ ሞክሮ ወደውጪ የወጣበት ሲሆን ተጨማሪ ጎል ሳንመለከት ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።