በኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የጦና ንቦቹ ኢትዮጵያ መድንን 1ለ0 በማሸነፍ ወደ ፍጻሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
ቀን 9 ሰዓት ላይ በዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮጵያ መድኖች የተሻለውን የመጀመሪያ የግብ ዕድል 5ኛው ደቂቃ ላይ ፈጥረው መሐመድ አበራ ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ (ቺፕ) የሞከረው ኳስ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ወላይታ ድቻዎች በግራው የማጥቂያ መስመራቸው በብሥራት በቀለ አማካኝነት ሁለት ሙከራቸውን ማድረግ ችለዋል። ሆኖም ግን ሙከራዎቹ ለግብ የቀረቡ አልነበሩም። በመጠኑ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች በጥሩ ቅብብል በወሰዱት ኳስ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ወገኔ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
በሁለቱም በኩል በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ ፉክክሮች ውጪ የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩም። በዚህም 21ኛው ደቂቃ ላይ ወገኔ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጪ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ከያዘበት ኳስ ውጪ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ አጋማሹ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ይበልጥ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ኢትዮጵያ መድኖች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ መጫወት ቢችሉም ወላይታ ድቻዎች 56ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን ለመምራት ተቃርበው ብሥራት በቀለ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ፍቅሩ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የጦና ንቦቹን የመከላከል አደረጃጀት ሰብረው ለመግባት የተቸገሩት ኢትዮጵያ መድኖች 73ኛው ደቂቃ ላይ ወገኔ ገዛኸኝ ካደረገው ፈታኝ ያልሆነ ሙከራ ውጪ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።
ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች 78ኛው ደቂቃ ላይ በብሥራት በቀለ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ሲችሉ 86ኛው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያ ጎል አስቆጥረዋል። ቢኒያም ፍቅሩ ያመቻቸለትን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ የተቀበለው ብሥራት በቀለ በግሩም አጨራረስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም የጦና ንቦቹ ወደ ፍጻሜው ማለፋቸውን ያረጋገጡ የመጀመሪያ ቡድን ሆነዋል።