የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 22ኛ ሳምንት የምድብ ለ የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው አዲስ ከተማ ተከታታይ አራተኛ ድሉን ሲያመስዘግብ የካ እና ካፋ ነጥብ ተጋርተዋል።
በእለቱ የመጀመርያ ጨዋታ አዲስ ከተማ ክ/ከተማ ሸገር ከተማን ከእረፍት በኋላ በተቆጠሩ ጎሎች 3-1 አሸንፏል።
በጨዋታው ጅማሮ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ሸገሮች
8ኛው ደቂቃ ላይ ዱላ ሙላቱ አሻግሮለት ሀይከን ድዋሙ ሞክሮ ወደ ላይ በወጣበት ኳስ የተጋጣሚ ግብ ፈትሸዋል።
ቀስ በቀስ የበላይነት መውሰድ የጀመሩት አዲስ ከተሞች 14ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ቅዱስ ተስፋዬ መትቶ በወጣበት ኳስ የመጀመርያ ሙከራ ሲያደርጉ 34ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ቅዱስ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ የሚጠቀሱ ነበሩ።
አራት ጎሎች በተመለከትንበት ሁለተኛው አጋማሽ አዲስ ከተማዎች ስኬታማ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ 50ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ሁለት ተቀባብለው ከመስመር ከቦጃ የተሻገረውን ኳስ ቅዱስ ተስፋዬ በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሮ መሪ አድርጓል። ሆኖም መሪነታቸው ለሰባት ደቂቃ ብቻ የቆየ ሲሆን ፋሲል አስማማው ከዱላ ሙላቱ የተሻገረለትን ኳስ ግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሮ ሸገርን አቻ አድርጓል።
ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ ቅፅበታዊ ምላሽ የሰጡት አዲስ ከተማዎች ከሦስት ደቂቃ በኋላ መሪነታቸውን አስመልሰዋል። በአንድ ሁለት ቅብብል ከቅዱስ ተስፋዬ የተመቻቸለትን ኳስ አህመድ አብዲ በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት በመቀየር ነበር አዲስ ከተማን በድጋሚ መሪ ያደረገው።
የአዲስ ከተማ ማጥቃት ቀጥሎ 68ኛው ደቂቃ ላይ ሸገሮች ለማጥቃት ባመሩበት ወቅት የዉትን ቦታ በመጠቀም ቅዱስ ከመሐል ያሻገረለትን ኳስ አህመድ አብዲ አምልጦ በመውጣት መሪነቱን አስፍቷል።
ከጎሎቹ በኋላ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ የተጫወቱት አዲስ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተቀይሮ በገባው ተካልኝ አስፋው አማካኝነት ለግብ የቀረበ እድል ቢያገኙም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳንመለከት በአዲስ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በየካ ክ/ከተማ እና ካፋ ቡና መካከል ተደርጎ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
የተቀዛቀዘ የጨዋታ እንቅስቃሴ በተመለከትንበት ጨዋታ የካዎች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ካፋ ቡናዎች በአንፃሩ በረጃጅም ኳሶች ለመጫወት ሙከራ አድርገዋል። ብዙም ሙከራ ባልተስተዋለበት ጨዋታ 38ኛው ደቂቃ ላዬ ከመስመር ከደረጄ ነጋሽ የሻገረውን ኳስ ጁንዴክስ ያመከናት የአጋማሹ ብቸኛ ሙከራ ነበረች።
ከእረፍት መልስ ከመጀመርያው ተመሳሳይ የሆነ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን የካዎች የተሻለ የጎል ሙከራዎች በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አድርገዋል። ጁንዴክስ አወቀ ሞክሮ የጎሉ ብረት የመለሰበት እና ክብሮም ፃድቁ ከመስመር ይዞ ገብቶ ሞክሮ በግብ ጠባቂ ጥረት የወጣበት እና ተካልኝ ገብረስላሴ ያሻማውን አንተነህ ተሻገር በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ። በአንፃሩ ካፋዎች በ72ኛው ደቂቃ ላይ ዮናታን ከመስመር ይዞት ገብቶ መትቶ ግብ ጠባቂው ካወጣበት ውጪ ተጠቃሽ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ያለ ጎል ፍፃሜውን አግኝቷል።