የኢትዮጵያ ወንዶች ከፍተኛ ሊግ ምድብ ”ሀ” 23ኛ ሳምንት ዛሬ በተረገ አንድ ጨዋታ ጅማሮውን ሲያደርግ ከዚህ በፊት ወጥቶለት ከነበረው መርሐግብር ላይ የቀን ማሻሻያ ተደርጎበት ዛሬ በተደረገው ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡና ጅማ አባቡናን ረቷል።
ቀን 5:00 ላይ በተደረገው መርሐግብር ይርጋጨፌ ቡና ከዕረፍት በፊት ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ጅማ አባ ቡናን 2-1 አሸንፏል።
ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርጉት ፍልሚያ ከጀማሮው አንስቶ ግብ ለማስቆጠር ሁለቱም ቡድኖች ከባባድ ሙከራዎችን በማድረጋቸው ሳቢ በነበረው ጨዋታ ጅማ አባ ቡና የተሻለ የግብ ማግባት ሙከራ በማድረግ እና ግብ በማግባት ቀዳሚ ነበር። በርከት ካለ የግብ ሙከራ በኋላ ጅማ አባ ቡና ቀዳሚ መሆን የሚችልበትን ግብ ከመረብ ጋር አገናኝቷል። በ23ኛው ደቂቃ በአንድ ለአንድ ቅብብል ገብተው በረከት ታምራት ኳሷን ወደ ግብ ሲመታት የይርጋጨፌ ቡናው ተከላካይ ጨርፏት እስጢፋኖስ ተማም አግኝቶ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ጅማ አባ ቡናን መሪ እንዲሆኑ አድርጓል።
ሆኖም ግን የጅማ አባ ቡና ደስታቸው ከአንድ ደቂቃ በላይ መቆየት አልቻለም። ግብ ካስቆጠሩ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ይርጋጨፌ ቡና የአቻነት ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። ይርጋጨፌ ቡናዎች በ24ኛው ደቂቃ ኳስ ጀምረው በፍጥነት በአንድ ለአንድ ቅብብል ወደ ጅማ አባ ቡና ግብ ክልል ደርሰው የአብሥራ ወርቅነህ ኳሱን ከፍ አድርጎ ከተከላካይ ጀርባ ሲጥለው አቤኔዘር ዘሪሁን በደረቱ አቁሞ በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎ አቻ እንዲሆኑ አስችሏል። አቻ ከሆኑ በኋላ በመነቃቃት የተጫወቱት ይርጋጨፌ ቡናዎች ተጨማሪ ግብ አክለዋል። በ36ኛው ደቂቃ የይርጋጨፌ ቡናው አቤኔዘር ዘሪሁን ኳስን ይዞ ወደ ሳጥን ሲገባ የጅማ አባ ቡናው ተከላካይ ሱራፌል ገዙ በሠራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ለይርጋጨፌ ቡናዎች ተሰጥቷቸዋል። ፍፁም ቅጣት ምቱን አገኘው ብርሀኑ ከመረብ ጋር አገናኝቶ በይርጋጨፌ ቡና መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከመልበሻ ክፍል መልስ ጨዋታው እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ አጨዋወት ሳያሰመለክት ቀርቷል። ሆኖም ግን ጅማ አባ ቡና የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በሚያደርገው ሙከራ የኳስ ብልጫ መውሰድ ችሏል። ይርጋጨፌ ቡናዎች በአንፃሩ ውጤቱን ለማስጠብቅ ሙሉ ለሙሉ ወደ ኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ የተስተዋሉ ሲሆን በዚህም ውጤታማ መሆን ችለዋል። ጨዋታውም በሁለተኛው አጋማሽ እምብዛም የግብ ሙከራ ሳያስመለከት በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች በይርጋጨፌ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።