የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቀናት ዕረፍት በኃላ በ23ኛ ሳምንት ውድድር የሀዋሳ ከተማ ቆይታውን ጅማሮ የሚያበስሩትን ሁለት መርሐግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፍ ቀርበዋል።
አዳማ ከተማ ከ ሻሸመኔ ከተማ
የሊጉን የሀዋሳ ቆይታ የሚያበስረው መርሐግብር አዳማ ከተማን ከሻሸመኔ ከተማ የሚያገናኝ ይሆናል።
በሰንጠረዡ በ34 ነጥቦች በ6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች በሀዲያ ሆሳዕና ከተሸነፉበት ጨዋታ ውጭ ሊጉ ከመቋረጡ በፊት ባደረጓቸው የሊግ ጨዋታዎች ላይ የነበራቸው ውጤትም ሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እጅግ አመርቂ የሚባል ነው።
ወጣቶችን ከተወሰኑ ባለ ልምድ ተጫዋቾች ጋር በማሰባጠር የተገነባው የዘንድሮው የአዳማ ከተማ ስብስብ ሰሞነኛ ብቃታቸውን ማስቀጠል ከቻሉ ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዩች ብዙ ሲባልበት በነበረው የውድድር ዘመን ሳይጠበቁ በሰንጠረዡ የተሻለ ስፍራን ይዘው የመፈፀማቸው ጉዳይ የሚቀር አይመስልም።
በ13 ነጥቦች በሰንጠረዡ ግርጌ ከሚገኙት ሀምበሪቾዎች በአምስት ነጥብ ከፍ ብለው ከበላያቸው ካለው ወልቂጤ ከተማ በሶስት ነጥቦች አንሰው በ15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሻሸመኔ ከተማዎች ምንም እንኳን ሰሞነኛ ውጤታቸው ጥሩ ባይሆንም ይህንን ሂደት ለመቀልበስ ለክለቡ መቀመጫ ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ሀዋሳ ከተማ ይፋለማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሜዳ ላይ ምንም እንኳን በጠባብ ውጤት ሽንፈትን ቢያስተናግዱም አሁን ድረስ ቡድኑ የሚያሳየው የተፎካካሪነት ደረጃ በብዙዎች ዘንድ ሻሸመኔ ከተማ በሊጉ ሊቆይ ይችላል የሚል እምነትን እያሳደሩ የቀጠሉ ሲሆን አሁን ግን ይህን ተስፋ ወደ እውነትን ለመቀየር ጊዜው የደረሰ ይመስላል ፤ ከዚህ ጋርም ተያይዞ የውድድሩ ስፍራ ለክለቡ መቀመጫ ከተማ ቅርብ እንደመሆኑ ቡድኑ በከፍተኛ የደጋፊዎች ቁጥር ታጅቦ ህልውናውን ለማስቀጠል ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርግም ይጠበቃል።
ከዚህ ባለፈም በሊጉ ግብ ካስቆጠረ ከ459 ደቂቃዎች በላይ ያስቆጠረው ቡድኑ የማጥቃት ጨዋታን መልክ ማስያዝ የአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ቀዳሚው የቤት ሥራ እንደሚሆን ይጠበቃል ፤ በተለይም በመጨረሻው የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ቡድኑ የተሻሉ ዕድሎችን ቢፈጥርም መጠቀም ያለመቻሉ ጉዳይ መፍትሄን ይሻል።
ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ ለሁለት ቀናት ብቻ ልምምድ የሠሩት ሻሸመኔ ከተማዎች እስካሁን ባለው መረጃ ከክፍያ ጋር በተያያዘ እስከ ዘጠኝ የሚደርሱ ተጫዋቾች ግልጋሎት እንደማያገኙ ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ ማይክል ኔልሰን በቅጣት ምክንያት የማይሰለፍ ተጫዋች ሲሆን በአዳማ ከተማ በኩል የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 3 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው አዳማ ከተማ ሁለቱን ሲያሸንፍ አንዱን አቻ ተለያይተዋል። አዳማ 4 ጎሎች ሲያስቆጥር ሻሸመኔ 1 አስቆጥሯል።
ባህር ዳር ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ
ምሽት 12 ሰዓት ሲል የሚጀምረው መርሐግብር ደግሞ ጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙትን ባህር ዳር ከተማዎችን ከድሬዳዋ ከተማ ያገናኛል።
በ37 ነጥቦች በሰንጠረዡ 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች እጅግ አስደንጋጭ ከነበረው እና በተከታታይ አራት የሊግ ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት ካስተናገዱ በኃላ በሊጉ ባደረጓቸው የመጨረሻ ስምንት ጨዋታዎች አምስቱን ሲረቱ በሶስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብን በመጋራት ጥሩ እምርታ ላይ ይገኛሉ።
በአንፃሩ በ33 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ በንፅፅር የተሻለ የውጤታማነት ጉዞን ከኮማንደር ሽመልስ አበበ ጋር እያሳለፉ ሲገኙ በተለይ ሊጉ በመዲናቸው በነበረው ቆይታ በሀዋሳ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት ውጭ እጅግ አስደናቂ ጊዜን ማሳለፍ ችለዋል።
በአሰልጣኝ ደግዓረግ ይግዛው የሚመሩት ባህር ዳር ከተማዎች ለስምንት ጨዋታዎች የዘለቀውን ያለመሸነፍ ጉዟቸውን ለማስቀጠል በማጥቃቱ እስካሁን በሊጉ 11 ግብ ባስቆጠረላቸው ቸርነት ጉግሳ ላይ እምነታቸውን የሚጥሉ ይሆናል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል ከዩጋንዳዊው አጥቂ ቻርልስ ሙሴጌ መጎዳት በኃላ በቡድኑ የፊት መስመር ተደጋጋሚ የመሰለፍ ዕድልን እያገኘ የሚገኘው ካርሎስ ዳምጠው ለቡድኑ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን እያሳየ ይገኛል ፤ በሊጉ 675 ደቂቃዎች ለቡድኑ ተሰልፎ የተጫወተው ካርሎስ አብዛኛዎቹ ከተጠባባቂ እየተነሳ የተጫወተባቸው ቢሆንም ከሰሞኑ ግን እያገኘ የሚገኘውን በቋሚነት የመሰለፍ ዕድል ተጠቅሞ በድምሩ አምስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል በነገው ጨዋታ ድሬዎች ከካርሎስ አብዝተው ይጠብቃሉ።
በባህር ዳር ከተማ በኩል ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኘው ሙጅብ ቃሲም ውጪ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ሦስት ተጫዋቾች ከጉዳት ተመልሰዋል ፤ ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ የነበሩት ተመስገን ደረሰ እና ዓብዱልፈታህ ዓሊ እንዲሁም የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቻርለስ ሙሴጌ ከጉዳት መልስ ቡድናቸውን የሚያገለግሉ ተጫዋቾች ሲሆኑ ያሲን ጀማል ግን አሁንም ጉዳት ላይ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በድምሩ በሊጉ በዘጠኝ አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ሶስቱ ጨዋታዎች በነጥብ መጋራት ሲፈፀሙ ባህር ዳር ከተማዎች በአምስት ጨዋታዎች ባለድል ሲሆኑ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ አንድ ጨዋታ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በጨዋታዎቹ ባህር ዳሮች አስራ ስምንት እንዲሁም ድሬዎች ደግሞ ሰባት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። (የተሰረዘው የ2012 ውድድር ዓመት አልተካተተም)