የትግራይ ክለቦች በቀጣይ የውድድር ዓመት ወደ ነበሩበት ሊግ ዕርከን በመመለሳቸው እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በመቐለ ከተማ መግለጫ ተሰጥቷል።
የትግራይ ክልል ክለቦች ከ2017 የውድድር ዘመን ጀምሮ ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት ሊግ ተመልሰው እንዲወዳደሩ መወሰኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በትላንትናው ዕለት ማስታወቁ አይዘነጋም ፤ በጉዳዩ ዙርያ በዛሬው ዕለትም መግለጫ ተሰጥቷል። መግለጫውንም የትግራይ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተኽላይ ፍቃዱ እና የትግራይ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ነጋ አሰፋ በጋራ የሰጡ ሲሆን በመግለጫ ስለውሳኔው እና የክልሉ እግር ኳሱ ስላለበት ወቅታዊ ሁኔታ ማብራርያ ተሰጥቷል።
ክለቦቹ ቀድሞ ሲወዳደሩበት ወደ ነበረው ሊግ በመመላሰቸው ደስታ እንደተሰማቸው በመግለፅ መድረኩን የከፈቱት አቶ ነጋ አሰፋ ይህ እንዲሳካ ከፍተኛ ጥረት እንደተደረገ በመግለፅ ለሂደቱ መሳካት አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል። ፕሬዝዳንቱ ክለቦቹ በአስገዳጅ ሁኔታ ከውድድሩ መውጣታቸውን ገልፀው አንድ ደረጃ ወርደው እንዲጫወቱ ከተወሰነበት ጊዜ አንስቶ ውሳኔው ለማስቀየር ከክለቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።
በተዋቀረው ልዑክ ከሚመለከታቸው የፌደራል ሀላፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ለመደረሩ አንስተው ከወራት በፊት ያካሄድነው ውይይትም በጥሩ መግባባት የተቋጨ እንደነበር ገልፀው ፤ በየፊናችን ማለትም የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን እንዲሁም እንደ ትግራይ የተሰጠን የቤት ስራ በአግባቡ ማከናወናችን ተከትሎም ክለቦቹ ወደ ነበሩበት ሊግ እንዲመለሱ ሆኗልም ብለዋል።
ቀጥለው ሀሳባቸውን የሰጡት የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተኽላይ ፍቃዱ በበኩላቸው ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አካላት ያደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ጥሩ ውጤት እንዳመጣ ገልፀው ቀጣይም እግርኳሱ ወደ ነበረበት ደረጃ ለመመለስ የተጀመሩት እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል ብለዋል።
ቀጥሎም ስለ ክለቦቹ ቀጣይ እቅዶችና የትግራይ ስቴድየም ሁኔታን አስመልክቶ በጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ከመድረኩ ምላሽ አግኝተዋል።
ስለ ክለቦቹ ቀጣይ እቅዶች መልስ የሰጡት አቶ ነጋ አሰፋ ከውሳኔው በፊት ቀደም ብለው ዝግጅቶች እንደጀመሩ በመግለፅ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል። “ቀድመን በሰራናቸው ስራዎች እንደምንመለስ እናውቅ ነበር ቅድመ ዝግጅቱም ቀደም ብለን ነው የጀመርነው፤ ከክለቦቹም ጋር ተነጋግረንበታል።በተጨማሪም ቀደም ብለን ገቢ ለማሰባሰብ የጀመርነው ሂደት አለ በቅርቡም ይቀጥላል፤ ከዛ በተጨማሪ በክለቦቹም በኩል በተናጠል የተጀመሩ ስራዎችም አሉ” ካሉ በኋላ ውድድራቸው በተሻለ ብቃት እንዲከወኑ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
የትግራይ ስቴድየም አስመልክተው ሀሳባቸው የሰጡት ኮሚሽነር ተኽላይ ፍቃዱ በበኩላቸው ስቴድየሙ በውስን መልኩ የማደስ እቅድ እንዳለ ገልፀው እቅዳቸው እንዲሳካ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ እና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በቀጣይ እንደሚወያዩ ገልፀዋል።