በዕለተ ትንሣኤ የሚከናወኑ የጨዋታ ሳምንቱ መገባዳጃ መርሀ ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች
መቻል ከ ወልቂጤ ከተማ
የነገው የጨዋታ ቀን ለሦስት ሳምንታት ከድል ጋር የተራራቁት መቻል እና ወልቂጤ ከተማ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል።
መሪው ንግድ ባንክ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ልዩነቱን የማጥበብ ወርቃማ ዕድል ያገኙት መቻሎች የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ ልዩነቱን ወደ ሦስት ማጥበብ ይችላሉ። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ያልቻለው ቡድኑ ወደ መሪው ይበልጥ ለመጠጋት ከነገው ጨዋታ ድል ያስፈልገዋል። መቻሎች የቅርብ ተቃናቃኛቸው ንግድ ባንክ ሁለት ለባዶ ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ ባከናወኗቸው አራት መርሀ ግብሮች ያስቆጠሩት የግብ መጠን ሦስት ብቻ ነው። ይህ ቁጥርም ዋንጫ ለሚያልምና በርካታ የፊት መስመር አማራጭ ላለው ቡድን ጥቂት ነው።
ቡድኑ በፊት መስመር ላይ ያለው የአፈፃፀም ክፍተት ማሻሻልም ቀዳሚ ስራው መሆን ይኖርበታል።
ከዚ በተጨማሪ በሦስት ተከታታይ መርሀ-ግብሮች መረቡን ሳያስደፍር ከወጣ በኋላ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀት በነገው ዕለት ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ ባይገመትም ወደ ቀድሞ ጥንካሬው መመለስ ግድ ይለዋል።
ከአራት ተከታታይ ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኋላ ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ያስተናገዱት ወልቂጤዎች ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዘው ከወጡ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርጉት ጉዞ ተስፋ እንዲሰንቁ ያደርጋቸዋል። በአስራ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው መድን ቀድሞ ማሸነፉን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ዘጠኝ ከፍ ማድረግ ቢችልም ሰራተኞቹ በነገው ጨዋታ ማሸነፍ ጨርሶ ላልጠፋው ተስፋቸው አስፈላጊ ነው።
በተከታታይ መርሀ-ግብሮች መቻልና መሪው ንግድ ባንክን የሚገጥመው ቡድኑ በሁለቱም ሳምንታት የሚያስመዘግባቸው ውጤቶች ወሳኝነታቸው ትልቅ ነው፤ በሊጉ ዝቅተኛው የግብ መጠን ያስቆጠረው ቡድኑ በጨዋታዎቹ የተሻለ ተፎካካሪ ለመሆን በዋነኛነት የግብ ማስቆጠር ችግሩ መቅረፍ ይጠበቅበታል። ከዚ በተጨማሪ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ መስመርም ሌላው ጥገና የሚያስፈልገው ክፍል ነው።
ወልቂጤ ከተማዎች በቅጣት ምክንያት የወንድማገኝ ማዕረግ፣ ዳንኤል ደምሱና ፋሪስ አለዊ ግልጋሎት አያገኙም። የመቻል መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም።
ወልቂጤ እና መቻል በሊጉ አምስት ጊዜ ሲገናኙ ጦሩ ሦስቴ ድል አድርጎ ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። መቻል 8 ፣ ወልቂጤ ደግሞ 2 ግቦች አስቆጥረዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዋሳ ከተማ
ፈረሰኞቹና ሀይቆቹ የሚያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ መርሀ-ግብር የተመለከቱ መረጃዎች
ከድል ጋር ከተራራቁ አራት ጨዋታዎች ያስቆጠሩት ፈረሰኞቹ ዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ወሳኝ የሆነው መርሀ-ግብር ያከናውናሉ። ድንቅ እንቅስቃሴ ባደረገባቸው ስድስት መርሀ-ግብሮች ጥሩ የፊት መስመር ጥምረት የነበራቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች የግብ ማስቆጠር ብቃታቸው ከተቀዛቀዘ ሰንበትበት ብሏል። ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩም የዚ ማሳያ ነው። ድሬዳዋ ላይ በነበረው የመጨረሻ አራት ሳምንታት ቆይታ በማጥቃቱ ተቀዛቅዞ የታየው የአሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቡድን በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት እያንዳንዱን ጨዋታዎች እንደ ፍፃሜ በመቁጠር መቅረብ ይኖርበታል፤ በተለይም የነገው ጨዋታ ከመሪው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት የሚያጠቡበት ወርቃማ ዕድል እንደመሆኑ ከድል በታች ያለ ውጤት ቡድኑን ትርፋማ አያደርግም።
ቡድኑ ባለፉት አስር ጨዋታዎች አምስት ግቦች ብቻ ያስተናገደና ከሌሎች ክፍሎች በአንፃራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኝ የተከላካይ ክፍል መያዙ ለዋንጫ በሚያደርገው ጉዞው ተስፋ እንዲሰንቅ ያደርገዋል፤ ነገር ግን በፊት መስመር ላይ የሚታዩት የአፈፃፀም ችግሮች ነገሮች በአዎንራዊ መንገድ እንዳይሄዱ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ይገመታል።
ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች ሀምበሪቾን አሸንፈው ወደ ድል መንገድ የተመለሱት ሀዋሳ ከተማዎች ቀድሞ የተጫወተው ሲዳማ ቡና ማሸነፉን ተከትሎ አንድ ደረጃ ዝቅ ብለዋል። በወራጅ ቀጠናው ካለው ቡድን በአስራ ሦስት ነጥቦች የሚርቀው ቡድኑ ምንም እንኳ አሁን ያለበት ደረጃ ለአደጋ የሚያጋልጥ ባይሆንም የውድድር ዓመቱን ከፍ ብሎ ለመጨረስ ከሚታይበት የወጥነት ችግር መላቀቅ አለበት። ሀይቆቹ ቡድኑ ሽንፈት ባስመዘገበባቸው ጨዋታዎች ጭምር ግብ ከማስቆጠር የማይቦዝን የፊት መስመር አላቸው፤ ሆኖም ከድሉ በፊት በነበሩ ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው ቡድኑ ወጥነት እንዳይኖረው አድርጎታል። የቡድኑ የኋላ ክፍል ማሻሻልም የአሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ ቀዳሚ ስራ ይሆናል ተብሎ ይገመታል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሦስት ጨዋታዎች ቅጣት የተጣለበት ሞሰስ አዶ ግልጋሎት አያገኙም፤ ሀዋሳ ከተማዎች ግን በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
ሁለቱ ቡድኖች 48 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 29 ጊዜ ባለድል ሲሆኑ ሀዋሳ ከተማ 7 ጊዜ አሸንፈዋል። ቀሪዎቹ 12 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ፈረሰኞቹ 84 ፣ ሀይቆቹ 35 ግቦች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)