በቢጫ ሰርጓጆቹ ቤት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ተከላካይ
ስፔንን በምታህል በእምቅ ችሎታዎች በተጥለቀለቀች ሀገር በታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ መጫወት እንዲህ እንደዋዛ የሚገኝ ዕድል አይደለም። ላማስያና ላፋብሪካን የመሳሰሉ ታዳጊዎችን እንደ አሸን የሚያፈሩ አካዳሚዎች ባሉባት ሀገር የሀገሪቱን ማልያ ለብሶ ለመጫወት ፉክክሩ ቀላል አይደለም ፤ የሦስቱ ትላልቅ አካዳሚ ተጫዋቾች የታዳጊ ብሔራዊ ቡድኖቹን አጥለቅልቀውታልና !
ከቪያሪያል ታዳጊ ቡድን የተገኘ አንድ ተስፈኛ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ግን ይህንን ሰብሮ በሦስት የዕድሜ እርከኖች ላይ የትናንሾሹ ቀዮች (La Rojita) ማልያ ለመልበስ በቅቷል። ስሙ ኦስካር ሽመልስ ጊል ይባላል። ትውልዱ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ሲሆን በአሁን ወቅት በቪያሪያል ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ቡድን ውስጥ በመጫወት ላይ ይገኛል።
በቢጫ ሰርጓጆቹ ቤት ትልቅ ተስፋ ከሚሰጣቸው ታዳጊዎች ተርታ የሚመደበው ይህ የመሀል ተከላካይ የስፔን ታዳጊ ብሔራዊ ቡድንን ወክሎ በተለያዩ ውድድሮች መሳተፍ የቻለ ሲሆን የቤኒካሲም ከተማ በስፖርት ዘርፍ ላቅ ያለ ውጤት ላመጡ ስፖርተኞች በሚሸልመት ዓመታዊ መድረክ ላይም በእግር ኳስ ዘርፍ ተሸላሚ ሆኗል።
ገና ታዳጊ እያለ ጫማውን እንኳን በትክክል ማሰር ያቅተው እንደነበር የሚናገረው ሽመልስ የአሳዳጊ አባቱ ሁዋን እገዛ እዚ ደረጃ ላይ እንዲደርስ እንደረዳው ይነገራል። በካስቴሎን ግዛት ውስጥ በእግር ኳስ ብዙ ደቂቃዎችን ከተመለከቱት ሰዎች አንዱ ሊሆን ይችላል የሚባልለት ሁዋን ከተስፈኛው ሽመልስ ጊል በተጨማሪ ፓኮ ተካልኝ የሚባል በካስቴሎን ከአስራ ዘጠኝ ዓመት በታች ቡድን የሚጫወት ሌላ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጫዋችም አብቅቷል።
ያ ትናንት ጫማውን እንኳ በአግባቡ ማሰር ያቅተው የነበረው ተጫዋች አሁን ዘመኑን የዋጀ ከእድሜው ጋር የማይመጣጠን ጥንካሬ እና ፍጥነትን ተላብሶ ጫማውን በደንብ ከማሰር በተጨማሪ የቢጫ ሰርጓጆቹ ተስፋ ለመሆን በቅቷል።