በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ጠንካራ የቡድን ግንባታን ከሚከተሉ ቡድኖች መካከል አንዱ መሆን ቢችልም ከሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን ለሁለት ጊዜያት ያህል ለመውረድ ተገዷል። ቡድኑ በ2015 የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ መሪነት ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማደግ መወዳደር የቻለ ቢሆንም በዓመቱ መጨረሻ የሰበሰባቸው ውስን ነጥቦች ዳግም ወደ ከፍተኛ ሊጉ እንዲወርድ አድርገውታል። በወረደበት ዓመት መመለስ እንዲችል በፕሪምየር ሊጉ የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ላይ ቡድኑን ተረክበው የነበሩት አሰልጣኝ በረከት ደሙን በማስቀጠል እንዲሁም ደግሞ አዳዲስ የአሰልጣኝ ቡድን አባላትንም ጭምር በማካተት በቡድኑ ውል ያላቸውን ፣ ወጣት እና አዳዲስ ተጫዋቾችን በማቀፍ በከፍተኛ ሊጉ ምድብ “ለ” ስር ክለቡ ሲወዳደር ከቆየ በኋላ በሰበሰባቸው ከፍ ያሉ ነጥቦች ታግዞ ወደ 2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደግ ችሏል። ለአርባምንጭ ከተማ በተጫዋችነት ዘመኑ ግልጋሎት የሰጠው እና አሁን ደግሞ በዋና አሰልጣኝነት የከፍተኛ ሊግ የማሰልጠን ልምድ ባይኖረውም ክለቡን በዓመቱ ካሳደገው አሰልጣኝ በረከት ደሙ ጋር ሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።
ስለ ውድድር ዘመን ጉዞው…
“የውድድር ዘመን ጉዟችንን መስከረም አስራ ሁለት ነው የጀመርነው ፣ የስድስት ሳምንት የዝግጅት ጊዜ ይኖረናል በሚል ታሳቢ አድርገን ምክንያቱም የከፍተኛ ሊግ ውድድር መቼ እንደሚጀመር በወቅቱ መረጃ ስላልነበረን የባለፈውን ዓመት ታሳቢ አድርገን የስድስት ሳምንት ዝግጅት በማድረግ ነው የጀመርነው። ዝግጅታችንን ስንጀምር ውል ያላቸውን ወደ ሰባት ተጫዋቾችን እና ከ20 ዓመት በታች በ2015 ያደጉትን አምስት ተጫዋቾችን በዘንድሮው ዓመት ከ20 ዓመት በታች ያደጉትን አምስት ልጆችን ጨምረን በአስራ ሰባት ተጫዋቾች ነው የጀመርነው ፣ ስንጀምር አንድ ሁለት ሦስት ልጆች ከውል ጋር ተያይዞ ከክለቡ ጋር ንግግር ላይ ስለነበሩ እነርሱን ማካተት አልቻልንም። በሒደት ዝግጅቶችን ጀምረን የምንፈልጋቸውን ተጫዋቾች በማስፈረም ስንፈልጋቸው ያጣናቸውን ፕላን ቢ ላይ የያዝናቸውንም ተጫዋቾች አካተን ዝግጅት አድርገናል ፣ ጥሩ ነበር ዝግጅቱ ጠንካራ የአካል ብቃት ሥራን ሠርተናል ፣ በቀን ሁለት ጊዜ በጂምናዚየም እና በመስክ በሜዳ ላይ አከናውነናል። በመጨረሻም የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማድረግ የተሟላ ስኳድ ይዘን ወደ ውድድር ገብተናል ጥሩ የዝግጅት ጊዜ ነበር ፣ በውድድር ላይም ምድባችንን ካወቅን ቀን ጀምሮ እያንዳንዱን ጨዋታ ማሸነፍ የሚያስችል የአካል ብቃት ፣ የቴክኒክ ፣ የስነ ልቦና እና የታክቲክ ሥራዎችን ሠርተናል። ሀዋሳ ላይ በነበሩት ውድድሮች በጥሩ መንገድ ተጉዘናል ፣ በሁለተኛው ዙርም የተወሰነ ቡድኑን አፕዴት ማድረግ ስለነበረብን በተጎዱ ተጫዋቾች ምትክ ሁለት ተጫዋቾችን ጨምረን በጥሩ መንገድ ተጉዘናል እስከ አሁን የነበረው በጥሩ መንገድ አልፏል ደስ የሚል ጊዜ ነበር።”
ክለቡ ከፕሪምየር ሊጉ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ወርዶ በድጋሚ የተመለሰው በተደጋጋሚ የሚከሰተው ይህ የመውረድ አደጋ ምክንያት ምንድነው…
“ክለቡ በተደጋጋሚ ጊዜ ወርዷል ፣ በእግር ኳስ ክለብ ስታዋቅር በስሜት መሆን የለበትም ብዬ አስባለሁ በዕውቀት ነው መሆን ያለበት እኛ አካባቢ ፓቴንሺያሉ አለ ፣ ጥሩ ተጫዋቾች አሉ ክለቡም አቅሙ በፈቀደ መጠን ጥሩ ነገርን እያደረገ ይገኛል ነገር ግን በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ምክንያቶች ናቸው ክለቡን ወደ ታችኛው ሊግ እንዲወርድ ያደረጉት ፣ አደረጃጀት እና ቡድን የመምራት አቅማችንን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ብናደርግ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። ብዙ ጊዜ እስከ አሁን የወረድነው በጣም በጥቃቅን ነገሮች ነው ፣ መጀመሪያ ብዙ ነገር ከጣልን በኋላ መጨረሻ አካባቢ ርብርብ ይደረጋል ፣ ይሄ የሚደረገው ርብርብ ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ በዕቅድ ቢሠራ እና ያለውን ሪሶርስ በአግባቡ ብንጠቀም ይሄ ነገር አይፈጠርም። የቡድን ማኔጅመንት ችግር በተደጋጋሚ ቡድኑ እንዲወርድ አድርጎታል ብዬ አስባለሁ ይሄ ነገር ከዚህ በኋላ ይፈጠራል የሚል ዕምነት የለኝም ከስህተቶቻችን በመማር ጠንካራ የቡድን አደረጃጀት ያለው የተረጋጋ ቡድን ይኖራል ብዬ አስባለሁ።”
በከፍተኛ ሊጉ ብዙም የማሰልጠኑ ልምድ ሳይኖርህ ይህንን ክለብ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መመለስ መቻልህ ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብህ….
“በከፍተኛ ሊግ ብዙ ልምድ የለኝም ፣ ይሄ ማለት ግን በአሰልጣኝነት ሕይወት ልምድ የለኝም ማለት አይደለም። ከስምንት ዘጠኝ ዓመት በላይ በአሰልጣኝነት ቆይቻለሁ በፕሪምየር ሊግ የማሰልጠን ልምድ አጋጥሞኛል ከአንድም ሁለት ጊዜ ወጣቶች ላይም ለአምስት ለስድስት ጊዜ ከፍተኛ የውድድር መንፈስ ያለው ውድድር ላይ ተሳትፌያለሁ እና ለአሰልጣኝነት ልምድ አለኝ ብዬ አስባለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ ውድድሮች እንደሚታወቀው በሦስት በአራት ዕርከን ይከፈላሉ ፣ ፕሪምየር ሊግ ፣ ከፍተኛ ሊግ ፣ አንደኛ ሊግ እያለ እኔ የከፍተኛ ሊግ የማሰልጠን ልምድ ባይኖረኝም ከከፍተኛ ሊጉ በላይ የሆነውን ፕሪምየር ሊግ ማሰልጠን ችያለሁ እና የራሴን ቡድን በአግባቡ ካደራጀው ፣ በአግባቡ ልምምዶችን ካሠራው ፣ ቡድኑን ማኔጅ የማደርግበትን መንገድ በትክክለኛ መንገድ ካደረኩ ፣ ውጤት ማምጣት እንደምችል ዐምን ነበር ፣ ያንንም ከኮቺንግ ስታፍ ጋር በመተባበር ጠንካራ ሥራ ሠርተናል የስራችን ውጤት ደግሞ በዓመቱ መጨረሻ ጥሩ ሆኗል። ለማንኛውም ለውድድር ጠንካራ ሥራ ነው መጀመሪያ የሚያስፈልገው ልምድን በጠንካራ ሥራ ነው የሸፈንነው ይሄ ደግሞ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ።”
በመጨረሻም …
“እንደሚታወቀው ክለባችን ባለፈው ዓመት ሲወርድ ጥሩ አልነበረም ፣ ብዙ ሰው አዝኖ ነበር እና ያንን ለመካስ ከተጫዋቾቻችን ጋር ከአመራሮች ጋር ሆነን ጠንክረን ሠርተን ወደሚገባን ቦታ ተመልሰናል ወደ ሚገባው ቦታ መመለስ አንዱ ሥራ እንጂ የመጨረሻው ሥራ አይደለም። ከዚህ በኋላም ፕሪምየር ሊግ ላይ የተረጋጋ እንዲሆን በጊዜ ሒደት ውጤታማ እንዲሆን ሁላችንም የየራሳችንን የስራ ድርሻ አውቀን የራሳቸንን ሥራ በአግባቡ መሥራት ከቻልን የተረጋጋ ቡድን ይኖረናል። አመራሩም የአመራር ሥራ ፣ አሰልጣኙም የአሰልጣኝ ሥራ ፣ ተጫዋቹም የተጫዋች ሥራ ፣ ደጋፊም የደጋፊን ሥራ መሥራት መቻል አለበት ፣ ምክንያቱም ቡድን የበርካታ ሰዎች ክምችት ነውና ሁሉም የየራሱን የማይሠራ ከሆነ ፣ አንዱ የተሰጠው የስራ ድርሻ ሌላ ሆኖ ወደ ሌላው የሥራ ኃላፊነት የሚገባ ከሆነ የተረጋጋ ቡድን መሥራት ይከብዳል። ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የራሱን ሥራ በአግባቡ እንዲሠራ ደጋፊውም ድጋፉን ባሸነፍን ጊዜ ብቻ ሳይሆን በምንሸነፍበትም ፣ አቻ በምንወጣበትም ጊዜ የቡድኑን የሜዳ ላይ ዕድገት በማየት በትዕግሥት እንዲደግፈን እላለሁ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በቀጣይ ዓመት ስንሳተፍ ዕድገት ያለው በወጣቶች የተገነባ ጥሩ ቡድን ይኖረናል ብዬ አስባለሁ። ደጋፊው ላደረገልን ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋናንም ማቅረብ እፈልጋለሁ።”