የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ23ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ23ኛው ሳምንት ጎልተው በወጡ ተጫዋቾች ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አደራደር 4-3-3

ግብ ጠባቂ

አቡበከር ኑራ – ኢትዮጵያ መድን

መድኖች በጨዋታ ሳምንቱ በእጅጉ ተፈትነው ከዕረፍት መልስ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሀምበርቾን ባሸነፉበት ወቅት የግብ ዘቡ አቡበከር ኑራ ደምቆ ውሏል። ግብ ጠባቂው ሀምበርቾዎች ከዕረፍት በፊት የፈጠሯቸውን የአንድ ለአንድ ግንኙነት እና ከሳጥን ውጪ የተደረጉ አደገኛ ሙከራዎችን በመመከት ቡድኑ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አበርክቶው ከፍ ያለ ነበር።

ተከላካዮች

ብርሃኑ በቀለ – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻን በረታበት ጨዋታው ወላይታ ድቻዎች በይበልጥ ለማጥቃት የተጠቀሙበትን የቀኝ የሜዳውን ክፍል በመቆጣጠር እና አልፎም ቡድኑ ለማጥቃት ሲታትር ተስቦ በመጫወት በሜዳው ቡድኑ ሦስት ነጥብን ሲያሳካ የመስመር ተከላካዩ እንቅስቃሴ ድንቅነት ላቅ ያለ ነበር ማለት ይቻላል።

ምኞት ደበበ – ፋሲል ከነማ

ዐፄዎቹ የሀዋሳ ቆይታቸውን በድል በከፈቱበት የሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ ከዕረፍት በፊት እየተመሩ ቢወጡም ከዕረፍት መልስ ግን ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ድልን ሲያገኙ የመሃል ተከላካዩ ምኞት ከተሰጠው የመከላከል ሚናው በተጨማሪ ቡድኑን አሸናፊ ያደረገች ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር መቻሉ በሳምንቱ የምርጥ ስብስባችን አካል አድርገነዋል።

ሰለሞን ወዴሳ – ሀዋሳ ከተማ

ኃይቆቹ ፈረሰኞቹን ከአምስት ዓመታት በኋላ ሲያሸንፉ የመሃል ተከላካዩ ብቃት እጅግ ግሩም ነበር። ከመከላከሉ ባሻገር በማጥቃት እንቅስቃሴው ብርቱ ተሳትፎ ያደረገው ሰለሞን በተለይም በሁለት አጋጣሚዎች ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችል ዓሊ ሱለይማን ላስቆጠራት ግብም በድንቅ ዕይታ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ፍጹም ፍትሕዓለው – ባህር ዳር ከተማ

የያሬድ ባየህን በግል ጉዳይ ከቡድኑ ጋር አለመኖር ተከትሎ በተከታታይ ጨዋታዎች የቋሚ ተሰላፊነት ዕድል ያገኘው ፍጹም የጣና ሞገዶቹ ድሬዳዋ ከተማን 1ለ0 ሲያሸንፉ ያሳየው ብቃት ድንቅ ነበር። ከፍሬዘር ካሳ ጋር በመጣመር ካደረጋቸው ማራኪ እንቅስቃሴዎች ባሻገር በአንድ አጋጣሚም በጭንቅላቱ በመግጨት ከመስመር ያገደው የሱራፌል ጌታቸው ኳስ ለቡድኑ ውጤት ማማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበረው በመሆኑ ወደ ግራ መስመር ተከላካይነት በመውሰድ በተከታታይ ሳምንት በምርጥ 11 ስብሰባችን ውስጥ እንድናካትተው አስገድዶናል።

አማካዮች

አማኑኤል ዮሐንስ – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና በንግድ ባንኩ ጨዋታው ከሁለት ለምንም ተነስቶ የአቻ ውጤትን ባስመዘገበበት ወቅት የቡድኑን የመሃል ሜዳ ሚዛን ከመቆጣጠር በተጨማሪ የማጥቂያ መንገዶችን በነፃነት ሲፈጥር የታየው አማኑኤል ቡድኑ ወደ ጨዋታ የተመለሰበትን የመጀመሪያ ግብም ከሳጥን ውጪ በግሩም ሁኔታ ማስቆጠር በመቻሉ በምርጥ ስብስባችን ውስጥ ተካትቷል።

አማኑኤል ጎበና – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ ከመመራት ተነስቶ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ግቦች 2ለ1 ሲያሸንፍ ድንቅ የነበረው አማኑኤል የሳምንቱ ምርጥ የሚያስብለውን እንቅስቃሴ አድርጓል ቢባል ማጋነን አይሆንም። አማካዩ መሃል ሜዳው ላይ ካደረገው ዕረፍት የለሽ ጠንካራ እንቅስቃሴ ባሻገር የቡድን ማሸነፊያ ግብም በተረጋጋ አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።

መስዑድ መሐመድ – አዳማ ከተማ

አዳማዎች የሀዋሳ ቆይታቸውን ሻሸመኔን 1-0 በማሸነፍ ሲጀምሩ ባለ ብዙ ልምዱ አማካይ መስዑድ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቁ በኩል ግሩም  እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል። በአጫጭር ቅብብሎች የቡድን ማጥቃት ሲያሳልጥ የነበረው መስዑድ አብረው ለሚጫወቱት ታዳጊዎች ልምዱን በማካፈሉ በኩል ውጤታማ እየሆነ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ሳምንትም በቦታው በምርጥ ስብስባችን ውስጥ ሊካተት ችሏል።

አጥቂዎች

ይስሃቅ ካኖ – ሲዳማ ቡና

የዓመቱ ሪከርድ በሆነ ብዛት በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ ሲዳማዎች ወላይታ ድቻን 2-1 ሲያሸንፉ የመስመር አጥቂው ብቃት ልዩ ነበር። ዕረፍት የለሽ በሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲታትር የዋለው አጥቂው በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችል የቡድኑን የመጀመሪያ ግብም በስሙ ማስመዝገብ ችሏል።

ምንይሉ ወንድሙ – መቻል

መቻሎች ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የሚያንደረድራቸውን ወሳኝ ውጤት በጨበጡበት የወልቂጤው ጨዋታ አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ ቀኑ ነበር። ተጫዋቹ የተገኙ ዕድሎችን በአግባቡ በመጠቀም ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ሀት-ትሪክ መሥራት የቻለ ሲሆን በተጨማሪነት ደግሞ ያስቆጠራቸውም ግቦች የግል አቅሙን ያሳዩ በመሆናቸው በሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ ሆኗል።

አቡበከር ሳኒ – ኢትዮጵያ መድን

መድኖች ወሳኝ በነበረው የሀምበርቾው ጨዋታ ተፈትነውም ቢሆን ውጤት ባገኙበት ወቅት ከዕረፍት መልስ አቡበከር ሳኒ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሮ ለቡድኑ ድል መሳካት ድርሻው ከፍ ያለ በመሆኑ የሳምንቱ ምርጥ አካል ተደርጓል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ኃይቆቹ ከ10 ግንኙነቶች በኋላ ፈረሰኞቹን ሲያሸንፉ በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ተወስዶባቸው እየተመሩ ቢወጡም ከዕረፍት መልስ 2ለ1 በማሸነፍ ድል ሲቀዳጁ የአሰልጣኙ አስተዋጽኦ በጉልህ የሚታይ ነበር። በተለይም ክፍተት በነበረበት ቦታ ያደረጓቸው ውጤታማ ቅያሪዎች አድናቆትን ያስተረፉ ሲሆን በዚህም አሰልጣኙ ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እና ከአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጋር ተፎካክረው ይህንን ምርጥ ቡድን እንዲመሩ መርጠናቸዋል።

ተጠባባቂዎች

ፔፔ ሰይዶ
ፍሬዘር ካሳ
ጃቢር ሙሉ
ፍሬው ሰለሞን
ወገኔ ገዛኸኝ
አብዱልከሪም ወርቁ
በዛብህ መለዮ
ነቢል ኑሪ
ሳይመን ፒተር
ዓሊ ሱሌይማን