የምሽቱ መርሐግብር በመሃል ተከላካዮች በተቆጠሩ ግቦች 1-1 ተጠናቋል።
በምሽቱ መርሐግብር ድሬዳዋ ከተማ እና አዳማ ከተማ ተገናኝተው ብርቱካናማዎቹ በ23ኛው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ 1ለ0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ ዳግማዊ ዓባይ ፣ ኤልያስ አህመድ ፣ ሄኖክ አንጃው እና ሙኸዲን ሙሳን አስወጥተው አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ፣ አቤል አሰበ ፣ ሄኖክ ሀሰን እና ቻርለስ ሙሴጌን ሲያስገቡ አዳማዎች በአንጻሩ ሻሸመኔን 1ለ0 ካሸነፉበት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ፍቅሩ ዓለማየሁ እና ነቢል ኑሪ በአድናን ረሻድ እና ቦና ዓሊ ተተክተው ገብተዋል።
ምሽት 12 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ዮናስ ካሳሁን መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አዳማዎች በቢኒያም ዐይተን ብርቱካናማዎቹ ደግሞ በካርሎስ ዳምጠው አማካኝነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ተጠቃሽ እንቅስቃሴ አልተደረገም ነበር።
በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ መውሰድ የቻሉት አዳማዎች የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ 25ኛው ደቂቃ ላይ አድርገው ቢኒያም ዐይተን ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ዐብዩ ካሣዬ ይዞበታል። በአምስት ደቂቃዎች ልዩነትም ሱራፌል አዎል እና ቻርለስ ሪባኑ ያደረጓቸውን ጥሩ ሙከራዎች ተከላካዮቹ ተደርበው አስወጥተውባቸዋል።
በስኬታማ ቅብብሎች መጠነኛ ብልጫ ይወሰድባቸው እንጂ በተደጋጋሚ መታተራቸውን የቀጠሉት ድሬዳዋ ከተማዎች 32ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን ፈጥረው በቀኝ መስመር ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ከአንድ ንክኪ በኋላ ያገኘው ኢስማኤል አብዱልጋኒዩ በጎኑ ተገልብጦ ያደረውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ይዞበታል።
እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር እና የማጥቃት እንቅስቃሴ ንጹህ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት አዳማዎች 45+1ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ሱራፌል አዎል ግብ ጠባቂውን በግሩም መረጋጋት አታልሎ ማለፍ ቢችልም የግራ መስመር ተከላካዩ መሐመድ አብዱለጢፍ በፍጥነት ደርሶ ኳሱን አቋርጦበታል።
ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል በተሻለ ግለት መጫወት የቻሉት ብርቱካናማዎቹ 58ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር የሚችሉበት ወርቃማ ዕድል አግኝተዋል። ፍቅሩ ዓለማየሁ ሱራፌል ጌታቸው ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ያሬድ ታደሰ መትቶት ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ መልሶበታል።
ድሬዳዋ ከተማዎች 61ኛው እና 63ኛው ደቂቃ ላይም በካርሎስ ዳምጠው አማካኝነት በቀኝ መስመር ከአሰጋኸኝ ጴጥሮስ እና ከሱራፌል ጌቻቸው በተነሱ ኳሶች በግንባር የተገጩ ግሩም ሙከራዎችን አድርገው ሁለቱም በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥተውበታል።
በሁለተኛው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ አይወሰድባቸው እንጂ በማጥቃት እንቅስቃሴው ተቀዛቅዘው የቀረቡት አዳማዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች እየተነቃቁ ሄደው በቻርለስ ሪባኑ እና በቦና ዓሊ አማካኝነት ሙከራዎችን ማድረግ ሲችሉ የመጀመሪያው በካርሎስ ዳምጠው ሁለተኛው በዐብዩ ካሣዬ ታግደዋል።
ጨዋታው 78ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጥሮበታል። ቦና ዓሊ ከመሃል የተሻገረለትን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ከፍል ላይ ሆኖ ወደ ውስጥ አሻግሮ ለፍቅሩ ዓለማየሁ ሲያቀብለው ፍቅሩም በድንቅ ክህሎት ሁለት ተጫዋቾችን አታልሎ በማለፍ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ በውስጥ በኩል ገጭቶ መሬት ላይ በመንጠር መረቡ ላይ አርፏል። በደቂቃ ልዩነትም ድሬዎች የመልስ ምት ለመስጠት ጥረት አድርገው አቤል አሰበ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ብርቱ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው በመጫወት 87ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው የመሃል ተከላካዩ ኢያሱ ለገሠ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ሽመልስ አበበ ተጭነው ለመጫወት አቅደው መግባታቸውን ገልጸው ያመከኑት የፍጹም ቅጣት ምት ውጤት ቀያሪ ክስተት ሊሆን እንደሚችል ሲጠቁሙ የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው ጨዋታው መጥፎ እንዳልነበር በመናገር ባለመረጋጋት የሚሠሯቸው ስህተቶች ለተጋጣሚያቸው ዕድል መፍጠር ምክንያት እንደነበሩ ገልጸው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ያን ያህል ውጤታማ እንዳልነበር አልሸሸጉም።