ሀዲያ ሆሳዕናዎች ሻሸመኔ ከተማን 3-1 በሆነ ውጤት በመርታት ከሦስት ጨዋታዎች በኃላ ዳግም ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል።
ሻሸመኔ ከተማዎች በአዳማ ከተማ በ23ኛው ሳምንት ከተረታው የቡድን ስብስብ ባደረጓቸው አምስት ለውጦች አቤል ማሞ ፣ አሸብር ውሮ ፣ ያሬድ ዳዊት ፣ ማይክል ኔልሰን እና ምንተስኖት ከበደ በኬኒ ሳይዲ ፣ ወጋየሁ ቡርቃ ፣ ኢቢሳ ከድር፣ አሸናፊ ጥሩነህ እና ጌታለም ማሙዬ ምትክ ሲጠቀሙ በአንፃሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ በፋሲል ከነማ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ባደረጓቸው ሦስት ለውጦች ታፔ አልዛየር ፣ ቃለዓብ ውብሸት እና ካሌብ በየነን አስወጥተው በምትካቸው ያሬድ ከበደ ፣ ዳግም ንጉሴ እና ሔኖክ አርፊጮን ተክተው ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።
በፌደራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው መሪነት ጅማሮውን ያደረገው ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማዎች የተሻለ አጀማመርን ያደረጉበት ነበር በዚህም በ8ኛው ደቂቃ እዮብ ገ/ማርያም በደረቱ አብርዶ ያመቻቸለትን ኳስ ሁዛፍ ዓሊ ከሳጥን ጠርዝ በቀጥታ ሞክሯ ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል የወጣችበት እንዲሁም በ10ኛው ደቂቃ ላይ ገዛኸኝ ደሳለኝ ከቆመ ኳስ ከተሻማ ኳስ ያገኘውን ሁለተኛ ኳስ ተጠቆሞ ያደረገው ሙከራ የሻሸመኔ ከተማን የበላይነት ማሳያ ነበሩ።
ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ሻሸመኔ ከተማዎች በ16ኛው ደቂቃ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር እዮብ ገ/ማርያም ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ያሳለፈውን ኳስ ቻላቸው መንበሩ ተረጋግቶ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በያሬድ በቀለ መክኖበታል።
በብዙ መልኩ የተቀዛቀዘ አጀማመርን ያደረጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ግን ሳይጠበቁ መሪ መሆን ችለዋል ፤ 20ኛው ደቂቃ ላይ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከራሳቸው የሜዳ አጋማሽ በረጅሙ የላኩትን ኳስ ዳዋ ሆቲሳ የመጀመሪያ ኳስ በማሸነፍ የጨረፈለትን ኳስ ተመስገን ብርሃኑ የግል ጥረቱን በመጠበቀም ከሻሸመኔ ተጫዋቾች ታግሎ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችን ግብ አስቆጥሯል።
ከግቧ መቆጠር በኃላ በተወሰነ መልኩ ተቀዛቅዞ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማዎች በ22ኛው ደቂቃ በእዮብ ገ/ማርያም አማካኝነት ካደረጉት ሙከራ ውጭ የነበራቸውን የማጥቃት ሂደት ማስቀጠል ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን ጨዋታውም በአመዛኙ በመሀል ሜዳ ላይ የተገደበ መልክን የያዘ ቢመስልም በአጋማሹ መገባደጃ ላይ ሀዲያዎች ሁለተኛ ግባቸውን አስቆጥረዋል ፤ ዳዋ ሆቲሳ ወደ ኃላ ተመልሶ ከሳሙኤል ዮሀንስ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሻሸመኔ ሳጥን ከገባ በኃላ ወደ ውስጥ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ተመስገን ብርሃኑ ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሁለተኛውን ግብ በማስቆጠር ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ቤት እንዲያመሩ አስችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ስንታየሁ መንግሦቱን ቀይረው በማስገባት የጀመሩት ሻሸመኔ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በበለጠ ሁዛፍ እና ስንታየሁን ታሳቢ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶችን ለመጠቀም ጥረት ያደረገ ሲሆን አጋማሹን እንደ መጀመሪያው ሁሉ ጫና በመፍጠር የጀመሩት ነበር ፤ በ54ኛው ደቂቃ ማይክል ኔልሰን ከርቀት በቀጥታ አክርሮ በመምታት ባደረጋት እና ያሬድ በቀለ በግሩም ሁኔታ ባዳነበት ኳስ የአጋማሹን ቀዳሚ ሙከራም ማድረግ ችለዋል።
በ55ኛው ደቂቃ በሻሸመኔዎች በኩል ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ የሚገጭ ተጫዋች በሳጥን ውስጥ አለመገኘቱን ተከትሎ ወደ መስመር የሄደችውን ኳስ ተከላካዩ ገዛኸኝ ደሳለኝ በቀጥታ ወደ ግብ ያደረጋት ሙከራ ያሬድ በቀለ በአግባቡ መቆጣጠር አለመቻሉን ተከትሎ ሻሸመኔ ከተማዎችን ወደ ጨዋታው የመለሰች ግብ ሆና ተቆጥራለች።
ከግቧ መቆጠር በኃላ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሻሸመኔ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ የሚያስቆጥሩ ቢመስልም በሂደት ግን ሀዲያ ሆሳዕናዎች የበላይነት ወስደው በመጫወት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል ፤ በ60ኛው ደቂቃ በተመስገን ብርሃኑ እንዲሁም በ75ኛው ደቂቃ በሳሙኤል ዮሀንስ አማኝነት ያደረጓቸው ሙከራዎች ለጥቂት ዒላማቸውን ሳይጠብቁ ሲቀሩ በ74ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ከተከላካይ ጀርባ ሾልኮ በመሮጥ ያደረገው ግሩም ሙከራ አቤል ማሞ አድኖበታል።
እያየለ የመጣው የሀዲያ ሆሳዕና ጫናም በስተመጨረሻ አሸናፊነታቸውን ያረጋገጠች ሦስተኛ ግብ አስገኝቷል ፤ በ79ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቲሳን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ደስታ ዋሚሾ በ84ኛው ደቂቃ ሔኖክ አርፊጮ ከርቀት ያሻማውን የቆመ ኳስ የሻሸመኔ ተጫዋቾች በአግባቡ መከላከል አለመቻላቸውን ተከትሎ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ጨዋታው በሀዲያ ሆሳዕና የ3-1 አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሻሸመኔ ከተማው አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ጥሩ አጀማመር ቢያደርጉም አስቀድመው በስህተት ግብ ማስተናገዳችን ወደ ጨዋታው ለመመለስ አስቸጋሪ አድርጎብናል ሲሉ ፊት መስመር ላይ የሚገኙ ዕድሎችን ወደ ግብነት መቀየር እና ቀላል የመከላከል ስህተቶች ቡድናቸውን ነጥቦችን እንዳያሳካ እያደረገው እንደሆነም ገልፀዋል በአንፃሩ የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው ከውጤቱ በላይ እንደ ቡድን ሆነ በግለሰቦች ደረጃ እያዩት የሚገኙት መሻሻል ተስፋ ሰጪ መሆኑ አንስተው በመጀመሪያው አጋማሽ ፊት መስመር ላይ ያደረጓቸው ሽግሽጎች ውጤታማ እንዳደረጓቸው ገልፀዋል።