ሪፖርት | መቻል ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

መቻሎች 22 ሙከራዎችን አድርገው አንድም ሙከራ ሳይደረግባቸው ሀምበርቾን 2ለ0 ረተዋል።

12፡00 ሲል በዋና ዳኛ ተካልኝ ለማ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ መቻሎች በቁጥር በዝተው ጫና ማሳደር የጀመሩት ገና በ2ኛው ደቂቃ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ሽመልስ በቀለ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ የመታው ኳስ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። በአምስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ግሩም ሀጎስ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ አስወጥቶበታል።


መቻሎች ሙሉ በሙሉ ኃይላቸውን በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ በማድረግ መጫወታቸውን ሲቀጥሉ 30ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው በረከት ደስታ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሽመልስ በቀለ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፖሉማ በድንቅ ቅልጥፍና አግዶበታል።

ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ የሚሄዱ ኳሶችን እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ መቻሎች 33ኛው ደቂቃ ላይ ወርቃማ የግብ ዕድል ፈጥረው ሽመልስ በቀለ በጥሩ ክህሎት ተከላካዮችን በማለፍ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ለምንይሉ ወንድሙ የማቀበል አማራጭ ቢኖርም ራስ ወዳድነት በተሞላበት መልኩ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

ሀምበርቾዎች ሙሉ በሙሉ በመከላከል ላይ ተደራጅተው የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ በመመከት ሲያሳልፉ በአጋማሹ አንድም ሙከራ ሳያደርጉ ቀርተዋል። ይባስ ብሎም 40ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበው ግሩም ሀጎስ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሽመልስ በቀለ ሙሉ በሙሉ ሳያገኘው ቀርቶ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስም ካቆሙበት የማጥቃት እንቅስቃሴ የቀጠሉት መቻሎች 48ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ከነዓን ማርክነህ ከሳጥን አጠገብ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ መልሶበታል።

ጨዋታው 53ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጥሮበታል። ሽመልስ በቀለ ከሳጥን አጠገብ የተገኘውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፎታል። አማካዩ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም ተጨማሪ ግብ አስቆጥሯል። ከበረከት ደስታ ጋር ተቀባብሎ ወደ ሳጥኑ ያስገባውን ኳስ በተረጋጋ አጨራረስ ግብ አድርጎታል።


መቻሎች መሪነታቸውን ካጠናከሩ በኋላ በመጠኑ ጨዋታውን እያረጋጉ ሲሄዱ 73ኛው ደቂቃ ላይ በበረከት ደስታ 78ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በምንይሉ ወንድሙ ያደረጓቸውን ሙከራዎች ሁለት ግቦች ይቆጠሩበት እንጂ ድንቅ ቀን ያሳለፈው ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ መልሷቸዋል።

ሀምበርቾዎች ቀስ በቀስ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ቢታትሩም ደካማ አደረጃጀታቸው ፈተና ሆኖባቸዋል። 81ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ሊቆጠርባቸው ተቃርቦ ዳዊት ዳሞ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረው ኳስ የግቡን የቀኝ ቋሚ ገጭቶ ተመልሷል።

የአንድ ቡድን ብቻ ጨዋታ ይመስል በነበረው ዕለት መቻሎች 88ኛው ደቂቃ ላይ 21ኛ ሙከራቸውን አድርገው ምንይሉ ወንድሙ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ በጥሩ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታውም በመቻል 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀምበርቾው አሰልጣኝ ብሩክ ሲሣይ ቢያንስ አንድ ነጥብ ዓልመው ቢገቡም ተጫዋቾች ልምምድ ባለመሥራታቸው ለጨዋታው ዝግጁ እንዳልነበሩ ገልጸው ፍላጎታቸው ባይሟላም ጨዋታውን ላደረጉ ተጫዋቾቻቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸው ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ጨዋታውን መቆጣጠር መቻላቸውን ገልጸው ከተጋጣሚያቸው አንጻር ዲያጎናል የሚደረጉ ቅብብሎችን ላለማድረግ ተነጋግረው ውጤታማ እንደሆኑበት ጠቁመዋል።