በ25ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወላይታ ድቻን 5ለ0 በሆነ ሰፋ ውጤት አሸንፏል።
በ25ኛው ሳምንት የመጀመሪያ መርሐግብር ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባገናኘው ጨዋታ የጦና ንቦቹ በ24ኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 ከተሸነፉበት ስብስብ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ፍጹም ግርማ ፣ መሳይ ኒኮል እና ኢዮብ ተስፋዬ ኬኔዲ ከበደ ፣ ናትናኤል ናሴሮ እና ዘላለም አባተ ተክተው ሲገቡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በአንጻሩ ወልቂጤ ከተማን 2ለ0 ከረቱበት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ እንዳለ ዮሐንስ እና አዲስ ግደይ ወጥተው ካሌብ አማንክዋህ እና ተስፋዬ ታምራት በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተካትተዋል።
9፡00 ሲል በዋና ዳኛ ዮናስ ካሳሁን መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከፍተኛ ብልጫ በመውሰድ አጥቅተው መጫወታቸውን የጀመሩት ገና በጊዜ ነበር። በዚህ እንቅስቃሴያቸውም 7ኛው ደቂቃ ላይ በሳይመን ፒተር 16ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በኪቲካ ጅማ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።
ጨዋታው 20ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሳይመን ፒተር ከግራ መስመር ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው የመስመር ተከላካዩ ፍጹም ግርማ ለማቋረጥ የሞከረው ኳስ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱን ነክቶ የራሱ መረብ ላይ አርፏል።
በሚያገኙት ኳስ ሁሉ በግሩም የቡድን ቅንጅት ተደራጅተው መጫወታቸውን የቀጠሉት ባንኮቹ 29ኛው ደቂቃ ላይም መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ካሌብ አማንክዋህ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሳይመን ፒተር ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ አሻግሮት ባሲሩ ዑማር በቀላሉ ግብ አድርጎታል።
በዛሬው ጨዋታ እጅግ ተዳክመው የቀረቡት ድቻዎች 38ኛው ደቂቃ ላይ ብዙዓየሁ ሰይፉ ከማዕዘን ተሻግሮ በተመለሰ ኳስ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እጅግ ሲቸገሩ ተስተውሏል።
በፈጣን የማጥቃት ሽግግር እንቅስቃሴ የተሳካ ቀን ያሳለፈው የንግድ ባንኩ ሳይመን ፒተር አስቀድመው ለተቆጠሩ ሁለት ጎሎች ቁልፍ መነሻ የነበረ ሲሆን 44ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በስሙ ተጨማሪ ግብ አስቆጥሯል። ኪቲካ ጅማ ከሱሌይማን ሀሚድ የተሻገረለትን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ወደ ውስጥ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አጥቂው በቀላሉ መረቡ ላይ አሳርፏታል።
ከዕረፍት መልስ ወላይታ ድቻዎች አንተነህ ጉግሳን አስወጥተው ፊንያንስ ተመስገንን በማስገባት መከላከላቸውን ለማስተካከል ጥረት ቢያደርጉም 55ኛው ደቂቃ ላይ አራተኛ ጎል ተቆጥሮባቸዋል። ኪቲካ ጅማ ያመቻቸለትን ኳስ ሳይመን ፒተር ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደ ውስጥ ያቀበለውን ኳስ ኤፍሬም ታምራት ግብ አድርጎታል።
የጦና ንቦቹ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ይበልጥ በራስ መተማመናቸውን እያጡ ሲሄዱ 62ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የግብ ዕድል ፈጥረው አበባየሁ ሀጂሶ ከብሥራት በቀለ የተቀበለውን ኳስ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ተቀይሮ በገባበት ቅጽበት ኳሱን ያገኘው ዮናታን ኤልያስ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።
ንግድ ባንኮች በማያቋርጥ የማጥቃት ሽግግር አጥቅተው መጫወታቸውን ሲቀጥሉ 77ኛው ደቂቃ ላይ አምስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ካሌብ አማንክዋህ በረጅሙ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ኪቲካ ጅማ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት በመግባት በተረጋጋ አጨራረስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።
በመጠኑ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ በወላይታ ድቻ በኩል 88ኛው ደቂቃ ላይ አበባየሁ ሀጂሶ ፣ 90+3ኛው ደቂቃ ላይ ዮናታን ኤልያስ በንግድ ባንኮች በኩል ደግሞ 90ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ቢኒያም ጌታቸው ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 5ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ 8 ተጫዋቾችን በጉዳት 1 ተጫዋች ደግሞ በቅጣት ማጣታቸው ለሽንፈቱ መንስዔ እንደሆነ ጠቁመው በመጀመሪያ አጋማሽ ያስተናገዷቸው 3 ጎሎች የጨዋታውን ሂደት ሙሉ በሙሉ እንደቀየሩት እና ንግድ ባንክ ከሊጉ በተጫዋቾች ስብሰብ የተሻለ በመሆኑ ለዋንጫ መጫወቱ የሚገርም ነገር እንዳልሆነ ሀሳባቸውን ሲሰጡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ በበኩላቸው ከጨዋታው በፊት አቅደው የገቡትን ነገር እንዳሳኩ ገልጸው በሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች አምስት አሸንፈው ፣ ሁለት አቻ በመውጣት ሽንፈት አለማስተናገዳቸው ወደ ዋንጫው ለሚያደርጉት ግስጋሴ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።