ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድኖች አምስት ጎል አስቆጥረው አምስተኛ ተከታታይ ድላቸውን አግኝተዋል

ኢትዮጵያ መድኖች በፍጹም የበላይነት በጎል ተንበሽብሸው 5-0 ሲያሸንፉ ድሬደዋ ከተማዎች አስከፊ ሽንፈት አስተናግደዋል።

ድሬዳዋ ከተማ በባለፈው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ያሬድ ታደሰ እና ሄኖክ ሀሰንን በኤልያስ አህመድ እና ከድር አዩብ በመቀየር ለጨዋታው ሲቀርብ በአንፃሩ ተከታታይ ድል በማድረግ ላይ ሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች አቡበከር ሳኒን በመሐመድ አበራ ብቻ በመተካት ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል።


ፌደራል ዳኛ ሙሉቀን ያረጋል በመሩት በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የቡድኖቹ እንቅስቃሴ በድሬዳዋዎች በኩል በራሳቸው ሜዳ  ክፍል በቁጥር በመብዛት በሁለት ሦስት ኳስ ንኪኪዎች ወደፊት በመሄድ አደጋ ለመፍጠር ቢያስቡም ብዙም ስኬታማ አልነበሩም። በአንፃሩ ኢትዮጵያ መድኖች በሁሉም የሜዳ ክፍል ኳሱን በጥራት በማንሸራሸር ክፍት ቦታ ለማግኘት በትዕግስት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው በስተመጨረሻም የመጀመርያ ጎላቸውን 17ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተዋል። ከማዕዘን ምት የተሻገረውን በግንባር ተገጭቶ ሲመለስ ዮናስ ገረመው መልሶ ወደ ሳጥን የላከውን የድሬዳዋ ተጫዋቾች በፍጥነት ከራሳቸው ሜዳ አለመውጣታቸውን ተከትሎ አለን ካይዋ ያገኘውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ ለቡድኑ የመጀመርያውን ጎል አስገኝቷል።

ከአምስት ደቂቃ በኋላ በድጋሚ መነሻውን ከቆመ ኳስ ከሀይደር ሸረፋ የተላከውን ብሩክ ሙሉጌታ በግንባሩ በጥሩ ሁኔታ የገጨውን ግብ ጠባቂው አብዮ ካሳዬ እንደምንም ተወርውሮ ባያድንበት ኖሮ ለመድኖች ሁለተኛ ጎል ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ጥራት ባለው ቅብብሎቻቸው ወደ መስመር ተጠግተው በተለይ መሐመድ አበራን ትኩረት ያደረገው የማጥቃት መስመራቸው ስኬታማ ሆኖላቸው ተጨማሪ ሁለተኛ ጎል በ29ኛው ደቂቃ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። መሐመድ አበራ የተቆጣጠረውን ኳስ ወደፊት በመግፋት ለአጥቂዎቹ ለማሻገር የላከውን መሐመድ አብዱልለጢፍ በእጁ የኳሱን አቅጣጫ መቀየሩን ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሀይደር ሸረፋ የመታውን ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ ቢያድነውም ረዳት ዳኛው ኤፍሬም ኃይለማርያም ግብ ጠባቂው ወጥቶ ነው ያዳነው በማለት በድጋሚ እንዲመታ አድርገዋል። ይህ ውሳኔ ተገቢ አይደለም በማለት የድሬዳዋ የቡድን አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ ቢያሰሙም የዳኛው ውሳኔ ሳይቀየር ሀይደር ሸረፋ በድጋሚ መቶት ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

ሁለት ጎሎች ከተቆጠሩባቸው በኋላ ወደ ጨዋታው ለመግባት ወደ ፊት አጥቅተው በመጫወት መሻሻል ያሳዩት ብርትካናማዎቹ 37ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድ አብዱልለጢፍ በፍጥነት ወደ ፊት በመሄድ ያሻገረውን ቻርልስ ሙሴጌ ኳሱን በግንባሩ ከመሬት ጋር አንጥሮ የመታውን ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ አድኖበታል። ብዙም ሳይቆይ በ40ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ከገባ በኋላ በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ አቅም የፈጠረው አድናን መኪ ሳይጠበቅ ከሳጥን ውጪ በጥሩ ዕይታ የመታውን በድጋሚ ግብ ጠባቂው አቡበከር እንደምንም ወደ ውጭ አውጥቶበታል። በድጋሚ ድሬዳዋዎች አቤል አሰበ በጥሩ መንገድ ከርቀት መጥኖ የላከለትን አድናን መኪ ሳጥን ውስጥ ነፃ ኳስ አግኝቶ በተገቢው ሁኔታ በግንባሩ ሳይገጫት ወደ ሰማይ የሰደዳት ለድሬዎች የምታስቆጭ ሌላ አጋጣሚ ሆኖ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲጀምር ብርትካናማዎቹ በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃ ያሳዩት የማጥቃት ጥረት ላይ በተሻለ አቀራረብ ወደ ሜዳ ይመለሳሉ ተብሎ ቢጠበቅም 48ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ መድኑ አለን ካይዋ ከብሩክ ሙሉጌታ በጥሩ ሁኔታ የተቀበለውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ በድንቅ አጨራረስ ለቡድኑ ሦስተኛ ለራሱ ሁለተኛ ጎል ማስገኘት ችሏል። ኢትዮጵያ መድኖች ተጋጣሚያቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ጎል ፍለጋ ለቀውት የሚሄዱትን ሰፊ ቦታን መስመሩን አስፍተው ተደጋጋሚ ማጥቃታቸውን ቀጥለው ተጨማሪ ጎል 60ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ድንቅ ምሽት ያሳለፈው አጥቂው አለን ካይዋ ከመጀመሪያው ጎሉ ጋር ተመሳሳይ በሆነ እንቅስቃሴ ለቡድኑ አራተኛ ለራሱ ሐት-ትሪክ የሠራበትን ጎል አስቆጥሯል።

አራት ጎል በማስተናገዳቸው ነገሮች የከበዱባቸው ድሬዳዋዎች 64ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፊል ጌታቸው ከሳጥን ውጭ በድንቅ ሁኔታ የመታውን የግቡ አግዳሚ ከመለሰበት ውጭ ያልተሳካ የማጥቃት እንቅስቃሴ እና ከጨዋታ ውጭ አቋቋም በማብዛት ደካማ ምሽት አሳልፈዋል። በአንፃሩ በሰፊ የጎል ልዩነት መምራት የቻሉት መድኖች በቀሪው ደቂቃዎች ጨዋታውን በተገቢው ሁኔታ በመቆጣጠር  90+4ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ሙሉጌታ የድሬዳዋ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ የማሳረጊያ አምስተኛ ጎል ተቆጥሮ ጨዋታው በኢትዮጵያ መድኖች 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ሽንፈት ያስተናገዱት አሰልጣኝ ሽመልስ በሰጡት አስተያየት መሐል ሜዳ ላይ ብልጫ እንደተወሰደባቸው እና የኋላ ክፍሉ መከላከል ላይ ቅንጅት አለመኖሩ ለማሸነፍ አስበው የመጡበትን እቅድ እንዳያሳኩ እንዳደረጋቸው እና ይህ ሽንፈት በዓመቱ ውስጥ ካጋጠማቸው ሽንፈት አስከፊው መሆኑን ተናግረዋል። አምስተኛ ተከታታይ ድል ያገኙት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በበኩላቸው ከሠሩት ሥራ አንፃር ውጤቱ ተገቢ መሆኑን ገልፀው እንደ ቡድን ሁሉም ተጫዋቾች በመንቀሳቀሳቸው ደስተኛ እንደሆኑ ፣ አጥቂያቸው አለን ካይዋ ለእርሳቸው አጨዋወት የሚሆን ተጫዋች መሆኑን እና በብቃቱ እንደሚተማመኑ ተናግረዋል።