በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት የሞት ሽረት ትግል ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው ‘ጦሩ’ ከኃይቆቹ ጋር የሚያደርጉት ተጠባቂ መርሀ-ግብርን ጨምሮ ፈረሰኞቹ ከ ነብሮቹ የሚያካሂዱት ጨዋታን አስመልክተን የሚከተሉትን ነጥቦች አንስተናል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀድያ ሆሳዕና
ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች አስተናግደው ከዋንጫ ፉክክሩ የራቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከመሪው በአስራ አራት ነጥቦች ርቀው 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ፈረሰኞቹ ሻሸመኔ ከተማን ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻሉም፤ ቡድኑ በተጠቀሱት መርሀ-ግብሮች ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥቦች ማሳካት የቻለውም ሁለቱን ብቻ ነው። ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ተጋጣሚ ላይ ሦስት ጎሎችን ብቻ በማስቆጠር የቀድሞ አስፈሪነቱን ያጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ዝቅተኛው የግብ መጠን ካስተናገደ ቡድን የሚያደርገው የነገው ጨዋታ ቀላል የማይባል ፈተና እንደሚጠብቀው ይታመናል።
ቡድኑ በተዳከመበት ወቅትም ጭምር የመከላከል ጥንካሬውን ይዞ መዝለቅ መቻሉ ከነገው ጨዋታ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ሊያስችለው ይችላል ተብሎ ሲገመት የሁለቱም ቡድኖች የቅርብ ጊዜ አቀራረብ ግን ጨዋታው በግቦች የታጀበ እንደማይሆን ጠቋሚ ነው።
ከተጋጣሚያቸው በአምስት ነጥቦች ዝቅ ብለው 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች በመጨረሻው መርሀ-ግብር ከሦስት ጨዋታዎች ቆይታ በኋላ ድል አድርገዋል።
ነብሮቹ በመጀመርያው ዙር የነበራቸው የመከላከል ጥንካሬ በውስን መልኩ ቢያጡም በቅርብ ጊዜያት በአንፃራዊነት የተሻለ የማጥቃት ሀሳብን ይዘው በመቅረብ ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ ከተከታታይ ጎል አልባ ጨዋታዎች መልስ ባለፉት ስድስት መርሀ-ግብሮች ላይ በጨዋታ በአማካይ 1.5 ግቦች ማስቆጠሩም አንድ ማሳያ ነው። በነገው ጨዋታ ግን በመልሶ ማጥቃት የጨዋታ መንገድ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ሲደርሱ በቁጥር የማነሳቸው ነገር ከተጋጣሚያቸው የመከላከል ጥንካሬ ተዳምሮ በፈረሰኞቹ ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይህ እንዳይሆን ግን ባለፉት ጨዋታዎች አናሳ የተጫዋቾች ተሳትፎ የነበረው የመልሶ ማጥቃትና ቀጥተኛ አጨዋወት በቁጥር ከማብዛት ባለፈ ተደጋጋሚ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን መፍጠር ይኖርባቸዋል። በነገው ጨዋታ በድምር ስምንት ግቦች ያስቆጠሩት ወሳኙ የፊት መስመር ተሰላፍያቸው ዳዋ ሆቴሳና ብሩክ ማርቆስ በቅጣት ማጣታቸው ግን በአጨዋወቱ ትግበራ ላይ እክል እንዳይሆንባቸው ያሰጋል።
ቡድኖቹ እስካሁን ዘጠኝ ጊዜ ተገናኝተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት፤ ሀዲያ ሆሳዕና ሁለት ድሎችን አሳክተው ሦስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጠኝ ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ሦስት ግቦች አስቆጥረዋል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ናይጄሪያዊው ሞሰስ ኦዶ ቅጣቱን ባለመጨረሱ ነገም የማይኖር ሲሆን በአንጻሩ አማኑኤል ተርፉ ከቅጣት ይመለሳል። በሀድያ ሆሳዕና በኩል ግርማ በቀለ እና መለሠ ሚሻሞ በጉዳት ዳዋ ሆቴሳ እና ብሩክ ማርቆስ ደግሞ በቅጣት ምክንያት አይሰለፉም።
ሀዋሳ ከተማ ከ መቻል
ከመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦች የሰበሰቡ ሁለት ቡድኖች የሚያገናኝና ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው ጨዋታ በዋንጫ ፉክክሩ ካለው ወሳኝነት አንፃር ከወዲሁ የብዙዎች ትኩረት ስቧል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ባለው የነጥብ መቀራረብ ምክንያት በመሀከለኛው የሰንጠረዡ ክፍል ለመደላለደል ከጦሩ ወሳኝ ነጥቦች መንጠቅ የሚጠበቅባቸው ኃይቆቹ ከተከታታይ ሽንፈቶች ተላቀው በቅርብ ሳምንታት ለውጦች አሳይተዋል።
የተከላካይ ክፍላቸው ተፈትኖ በንግድ ባንክ ከተሸነፉበት ጨዋታ በኋላ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ድልና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ሀዋሳ ከተማዎች ሽንፈት ባስተናገዱብት ጨዋታ የታየባቸው የመከላከል ክፍተቶች በውስን መልኩ ቀርፈዋል። በጨዋታው ለንግድ ባንክ የመስመር አጨዋወት ተጋላጭ የነበረው ቡድኑ ባለፉት ጨዋታዎች መሻሻሎች ቢያሳይም በቆሙ ኳሶች የመከላከል አቅሙ ትኩረት አድርጎ መስራት ይኖርበታል። ባለፉት መርሀ-ግብሮች ከቆመ ኳስ መነሻ ያደረጉ ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ የነገው ተጋጣሚው መቻል በመጨረሻው ጨዋታ በቆሙ ኳሶች ግብ ከማስቆጠር በተጨማሪ ሁለት ለግብ የቀረቡ አደጋዎች የፈጠረ ቡድን እንደመሆኑም ለሂደቱ ልዩ ትኩረት አድርገው እንዲገቡ ያስገድዳቸዋል። በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኝ የፊት መስመር የገነቡት አሰልጣኝ ዘርዐይ ሙሉ በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ የፊት ጥምረቱ ላይ ትኩረት ያደረገ አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎ ሲገመት በቁጥር በዝቶ የሚያጠቃ ቡድን ለመግታት ግን ልዩ ዝግጅት ማድረግ ግድ ይላቸዋል።
ንግድ ባንክ ቀድሞ ማሸነፉን ተከትሎ ከመሪው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ከማሸነፍ ውጭ ትርፋማ የማያደርጋቸው መቻሎች በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ሙሉ ነጥብ አስፈላግያቸው ነው።
ፊት መስመር ላይ ሰፋ ያለ የተጫዋቾች ምርጫ ያለው ጦሩ በቅርብ ሳምንታት በተለየ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን አማካዮቹን በቁጥር አብዝቶ ማጥቃቱ ላይ ማሳተፋ የበለጠ ጥንካሬ አላብሶታል፤ ሆኖም በተደጋጋሚ ጊዜ የተስተዋሉት ግለኝነት የተሞላቸው የውሳኔ አሰጣጥ ክፍተቶች በርከት ያሉ ግቦች እንዳያስቆጥር እክል ሆኖበታል። ሀምበሪቾን ባሸነፉበትን ጨዋታ ጨምሮ በቅርብ ሳምንታት የተስተዋሉት መሰል ክፍተቶች መቅረፍም ለዋንጫ በሚያደርጉት ጉዞ ዋጋው ትልቅ ነው።
ከዚህ ቀደም በምንይሉ ወንድሙ ብቻ የተጣለ ይመስል የነበረው ግብ የማስቆጠር ኃላፊነት በሌሎች ተጨዋቾችም መታገዝ መጀመሩም በበጎ ጎኑ የሚነሳላቸው ነጥብ ነው። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍል በነገው ጨዋታ ፈታኝ ፍጥጫ ይጠብቀዋል። ተቀራራቢ የማጥቃት አጨዋወት ከሚከተለው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ ለመልሶ ማጥቃቶች ተጋላጭ የነበረው ቡድኑ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት አብዝቶ ከሚጠቀም ቡድን ጋር በሚያደርጉት የነገው ጨዋታ ሽግግሮች የማቋረጥና ቶሎ ወደ መከላከል ቅርፃቸው የመመለስ አቅም ማጎልበት ይኖርባቸዋል።
ሁለቱም ቡድኖች ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነውን ስብስብ ይዘው ወደ ጨዋታው ሲቀርቡ፤ ሀዋሳ ከተማዎች በመጨረሻው ጨዋታ ያልተሰለፈው ፀጋአብ ዮሐንስና መጠነኛ ህመም ገጥሞት ተቀይሮ የወጣው ታፈሰ ሰለሞን ለጨዋታ ብቁ ሆነውላቸዋል።
ሁለቱ ቡድኖች 33 ጊዜ ተገናኝተዋል። ሀዋሳ ከተማ 14 በማሸነፍ ቅድሚያውን ሲይዝ መቻል 9 ጨዋታ አሸንፏል። ቀሪዎቹ 10 ጨዋታዎች አቻ የተለያዩባቸው ግንኙነቶች ናቸው። በጎሎች የታጀበ ታሪክ ያለው ይህ ግንኙነት 75 ጎሎች የተቆጠሩበት ሲሆን ሀዋሳ 41 መቻል በበኩሉ 34 ጎሎችን አስቆጥረዋል።