የምሽቱ ድራማዊ እና አዝናኝ ጨዋታ አምስት ጎል አስመልክቶን መቻሎችን ሁለቴ ከመመራት ተነስተው ወሳኝ ሦስት ነጥብ እንዲያገኙ ሲያስችል ሀይቆቹን አሳዛኝ ተሸናፊ አድርጓል።
ሀዋሳ ከተማ የሮዱዋ ደርቢ ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ቡድናቸው ሲሳይ ጋቺቾ፣ በረከት ሳሙኤል፣ ታፈሰ ሰለሞን፣ ተባረክ ሄፋሞ ፀጋአብ ዮሐንስ፣ መድሀኔ ብርሀኔ፣ አቤኔዘር ዮሐንስ እና እስራኤል እሸቱ ተክተው ሲገቡ መቻሎች በበኩላቸው የጨዋታ ብልጫ ወስደው ሀምበሪቾን ከሸነፈው ስብስባቸው ምንም ዓይነት የተጫዋቾች ለውጥ ሳያደርጉ ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል።
በዋንጫ ፉኩኩሩ ላይ መወሰን የሚችለውን ፍልሚያ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ አስጀምረውታል። ገና ከጅማሬው አንስቶ በእያንዳንዱ የሜዳ ክፍል በሚደረጉ ፍልሚያዎች ትኩረት የሚስብ እንቅስቃሴ እያስመለከቱን ቀጥለዋል። በ5ኛው ደቂቃ በመቻሎ ከግራ መስመር ሽመልስ በቀለ የላከውን ከተከላካዮች ጀርባ ነፃ አቋቋም ላይ የሚገኘው ከንዓን ማርክነህ ኳሱን አግኝቶ የመታው ለጥቂት በቋሚው ስር የወጣው የጨዋታውን ግለት ከፍ ያደረገ ነበር።
ሀዋሳዎች አደገኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ እንቅስቃሴያቸው ቢቋረጥም ጥሩ የማጥቃት ፍላጎት በማሳየት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ በ13ኛው ደቂቃ ጎል አግኝተዋል። ኳሱን ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ማራቅ ያልቻሉት መቻሎች የሰሩን ስህተት ኢዮብ ዓለማየሁ ለዓሊ ሱሌማን አቀብሎት በሚገርም ውሳኔ ኳሱ እንደመጣ አዙሮ ከሳጥን ውጭ በመምታት የቡድኑን ቀዳሚ ጎል አስገኝቷል።
የሀይቆቹን የመከላከል አጥር ሰብረው ለመግባት የተቸገሩት መቻሎች የኳሱን አቅጣጫ በመቀያየር በመስመር አድልተው ምላሽ ለመስጠት ሲሞክሩ በ16ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል ምንይሉ ወንድሙ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ያሻገረውን ሽመልስ በቀለ ኳሱን ወደ ጎል ደገፍ ቢያደርገውም ግብጠባቂው ቻርልስ በጥሩ ንቃት ያዳነባቸው ተጠቃሽ ነበር።
ውጥረት የተሞላበት ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ በአንድ ሁለት ቅብብል በረጃጅም ኳሶች ጫና ለመፍጠር የሞከርኩት ሀዋሳዎች በ18ኛው ደቂቃ ኢዮብ ዓለማየሁ ከጎሉ ቅርበት ነፃ ኳስ አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው አስቆጪ ሆኖ አልፏል። ክፍት የሜዳ ክፈል ለማግኘት መፈናፈኛ ያጡት መቻሎች በመጨረሻም ወደ ጨዋታው የተመለሱበትን ጎል አግኝተዋል። 36ኛው ደቂቃ ከረጅም ርቀት ሳጥን ውስጥ የተላከውን ሽመልስ በቀለ ለማለፍ ያሰበውን ኳስ ከንዓን ማርክነህ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ የቡድኑን አቻነት ጎል አስገኝቷል።
ከጎሉ በኋላ መቻሎች በበረከት ደስታ አማካኝነት ተጨማሪ ጎል ማግኘት ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ሊወጣባቸው ችሏል። በአንናፃሩ 43ኛው ደቂቃ በሀይቆቹ በኩል ልዮነት ፈጣሪ ተጫዋች የሆነው ዓሊ ሱሌማን በግራ መስመር በጥሩ ንክኪ ከኢዮብ አለማየሁ የተቀበለውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎል ቢመታውም የግቡ ቋሚ የከለከለው አጋጣሚ የሚያስቆጭ ዕድል ነበር። ጨዋታውም በድርጊት ተሞልቶ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።
የጨዋታው እንቅስቃሴ ከዕረፍት ሲመለስ በ49ኛው ደቂቃ ሀዋሳ ከተማዎች በፈጥን የማጥቃት ሽግግር ዓሊ ሱሌማን በሚገርም ብቃት ኳሱን እየገፋ ወደ ሳጥን በመግባት በሚያደርገው ጥረት የመቻሉ ተከላካይ ነስረዲን ኃይሉ ዓሊን መቆጣጠር አቅቶት የኃይል አጨዋት መጠቀሙን ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት እራሱ ዓሊ ለቡድኑም ለራሱም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።
ከደቂቃዎች በኋላ ሀዋሳዎች በድጋሚ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል ዓሊ ሱሌማን በግል ጥረቱ ፍጥነቱን በመጠቀም ወደ ፊት ለመሄድ በሚያደርገው ጥረት ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በነስረዲን ሀይሉ ያልተመጣጠነ ጉልበት በመጠቀሙ ምክንያት ጥፋት ቢሰራበትም ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ሳያሳምናቸው በመቅረቱ ፍፁም ቅጣት ምት ሳይሰጡ መቅረታቸው ሀዋሳዎችን አላስደሰተም ነበር።
በሁለቱም በኩል በፈጣን የማጥቃት ሽግግር በሚደረጉ ምልልሶች እጅግ ሳቢ ፉክክር እያስመለከተን የቀጠለው ጨዋታ በተለይ መቻሎች ከዋንጫው ፉክክር ላለመራቅ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የማጥቃት አቅማቸውን በማሳደግ ቢሞክሩም አደገኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ ኳሶች ቢበላሽባቸውም 69ኛው ደቂቃ ላይ ወሳኝ ጎል አግጋኝተዋል። የሀዋሳው ተከላካይ ሰለሞን ወዴሳ በተገቢው መንገድ ከራሱ የሜዳ ክፍል ያላራቀውን ኳስ ከንዓን ማርክነህ ባልተለመደው ግራ እግሩ በግሩም ሁኔታ መቶ ለራሱ ለቡድኑም ሁለተኛ የአቻነት ጎል አስገኝቷል።
የጨዋታው ደቂቃዎች የገፋ በሄደ ቁጥር ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ከባድ የሆነ ድራማዊ ትዕይንት እያስመለከተን የቀጠለው ጨዋታ መቻሎችን መሪ ያደረገች አስገራሚ ጎል ተቆጥሯል። 80ኛው ደቂቃ ከሳሙኤል ሳሊሶ ከርቀት የተላከውን ኳስ በተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ አብዱ ሞታላቦ በሚገርም የአየር ላይ መቀስምት የሀዋሳ መረብ ላይ አስቀምጦታል።
በቀሩት ደቂቃዎች ሀዋሳዎች በሙሉ አቅማቸው ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም በጥንቃቄ ተከላክለው ጨዋታውንም ተቆጣጥረው ወሳኙን ድል 3-2 በማሸነፍ ሊወጡ ችለዋል።
ተሸናፊው አሰልጣኝ ዘራይ ሙሉ ሲባገሩ ጨዋታው እጅግ ፈጣን ነበር ሆኖም ሦስት ለአንድ ሊመሩበት የሚችሉበትን የፍፁም ቅጣት ምት መከልከላቸው ጨዋታውን መቀየሩን ተናግረው። በእንቅስቃሴው የተሻለ ቡድን ይዘው እንደቀረቡ ተናግረዋል። ድል ያደረጉት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራ ሲናገሩ በጣም ጥሩ ጨዋታ ነው ሁለቴ ከመመራት ተነስተው ማሸነፋቸው በተጫዋቾቻቸው ጥንካሬ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረው። በከንዓን እንቅስቃሴ ልዮ እንደነበረ እና የሊጉን መሪ ጨዋታን እንደማይከታተሉ እና ነጥብ እንዲጥል እንደማይመኙ ገልፀዋል።