ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ተከታታይ ድል ተቀዳጅቷል

በሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ራምኬል ጀምስ ለሦስተኛ ጊዜ ባስቆጠረው ወርቃማ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ቡናማዎቹ ሻሸመኔ ከተማን 2ለ1 እንዲያሸንፍ አስችሏል።

በ25ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐግብር ሻሸመኔዎች በ24ኛ ሳምንት በሀዲያ 3ለ1 ከተሸነፉበት አሰላለፍ አቤል ማሞ ፣ ቻላቸው መንበሩ ፣ ያሬድ ዳዊት እና ገዛኸኝ ደሳለኝን አስወጥተው ኬን ሳይዲ ፣ የአብሥራ ሙሉጌታ ፣ ወጋየሁ ቡርቃ እና አብዱልቃድር ናስርን ሲያስገቡ ቡናማዎቹ በአንጻሩ ወላይታ ድቻን 2ለ1 ካሸነፉበት አሰላለፍ አማኑኤል አድማሱን አስወጥተው መሐመድኑር ናስርን አስገብተዋል።


ምሽት 12 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ፊሽካ ተጀምሮ መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት ቀዝቃዛ አጀማመር በነበረው ጨዋታ  የመጀመሪያው የግብ ዕድል 18ኛ ደቂቃ ላይ ሲፈጠር ብሩክ በየነ ከአብዱልከሪም ወርቁ በተቀበለው ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ ሲመልስበት ያንኑ ኳስ ያገኘው መሐመድኑር ናስር ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረገው ፉክክር ውጪ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ባላስመለከተን ጨዋታ 25ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ ያመቻቸለትን ኳስ ብሩክ በየነ ሊጠቀምበት ሲል የመሃል ተከላካዩ ምንተስኖት ከበደ በአስደናቂ ሁኔታ ተንሸራትቶ ሲያግድበት 33ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የሻሸመኔው ማይክል ኔልሰን ከቀኝ መስመር ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረው ኳስ ወደ ግብ አቅንቶ በረከት አማረ እንደምንም አስወጥቶታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይፈጠር አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀጥል ሻሸመኔዎች 50ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የመጀመሪያ የሆነውን የግብ ዕድል ፈጥረው ኢዮብ ገብረማርያም በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ቀንሶት ማንም ሳይጠቀምበት በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። በሁለት ደቂቃዎች ደግሞ የቡናው አማኑኤል ዮሐንስ ከሳጥን አጠገብ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ግብ አልባ የሆነው ጨዋታ 55ኛው ደቂቃ ላይ በሻሸመኔዎች አማካኝነት ግብ ሊያስመለክተን እጅግ ተቃርቦ ኢዮብ ገብረማርያም ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ በግሩም ሁኔታ ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ሁዛፍ ዓሊ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ እጅግ ደካማ በሆነ እና ኃይል በቀላቀለ ሙከራ ወርቃማውን ዕድል አባክኖታል።


ኢትዮጵያ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ተጭነው መጫወታቸውን ሲቀጥሉ 61ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን ለግብ የቀረበ ሙከራቸውን አድርገው አብዱልከሪም ወርቁ ከቅጣት ምት አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ሲወጣበት በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ራምኬል ጀምስ ከማዕዘን ተሻምቶ በተመለሰ ኳስ ከረጅም ርቀት እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ አክርሮ በመምታት ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

በሁለቱም በኩል ግለቱ ይበልጥ እየጨመረ በሄደው ጨዋታ ቡናማዎቹ 72ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በፍቃዱ ዓለማየሁ በግሩም ክህሎቱ ታጅቦ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በድንቅ ቅብብል የወሰደውን ኳስ በመጨረሻም መስፍን ታፈሰ ካመቻቸለት በኋላ በቀላሉ አስቆጥሮታል። ነገር ግን መሪነታቸው ከሦስት ደቂቃ በላይ ሳይቆይ የሻሸመኔው ሁዛፍ ዓሊ ከራምኬል ጀምስ ጋር ታግሎ እየገፋ የወሰደውን ኳስ መረቡ ላይ አሳርፎት ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ሻሸመኔዎች የአቻነት ግብ ካገኙ በኋላም በሁዛፍ ዓሊ አማካኝነት ንጹህ የግብ ዕድል አግኝተው አጥቂው እጅግ ግድየለሽነት በታየበት ሁኔታ ኳሱን ወደ ውጪ ልኮታል። በአንጻሩ በተረጋጋ መንፈስ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 90+1ኛው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያ ጎል አግኝተዋል። አብዱልከሪም ወርቁ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ራምኬል ጀምስ እንደ መጀመሪያው ዙር ግንኙነታቸው ሁሉ በመጨረሻ ደቂቃ ኳሱን በግንባር ገጭቶ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሻሸመኔ ከተማው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የተጫዋቾችን እንቅስቃሴ አድንቀው ከውጤቱ ነጥብ ይዘው መውጣት ይገባቸው እንደነበር በመጠቆም ሁዛፍ ዓሊ በግድየለሽነት ያባከነው ኳስ ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረው በሜዳው ምክንያት አጨዋወታቸውን ለመቀየር መገደዳቸውን ሲገልጹ የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ በበኩላቸው በተለይም በሜዳው ምክንያት በእንቅስቃሴው መቸገራቸውን ጠቅሰው ያን ያህል ጥሩ ባይሆንም ከውጤት አንጻር ጥሩ ነገር እንዳገኙ በመናገር ራምኬል ጀምስን ከቆመ ኳስ እንዲጠቀም አልመው በቋሚ አሰላለፍ ማስገባታቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ገልጸው በሊጉ እስከ ሦስተኛ መጨረስ እና የኢትዮጵያ ዋንጫንም የማንሳት ፍላጎት እንዳላቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።