በ26ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ ሠራተኞቹን 3ለ0 ረተዋል።
በ26ኛ ሳምንት የመጀመሪያ መርሐግብር ወልቂጤዎች በ25ኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ 1ለ0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ መሳይ አያኖ እና ተስፋዬ መላኩ ወጥተው ፋሪስ አለዊ እና ጌቱ ኃይለማርያም ሲገቡ ድሬዳዋዎች በአንጻሩ በኢትዮጵያ መድን 5ለ0 ከተሸነፉበት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ መሐመድ አብዱለጢፍ ፣ ከድር አዩብ እና ኤልያስ አህመድን አስወጥተው ቴዎድሮስ ሀሙ ፣ ዳግማዊ ዓባይ እና ሄኖክ አንጃውን አስገብተዋል።
9 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ድንቅ አጀማመር ያደረጉት ብርቱካናማዎቹ ገና በ25 ሴኮንድ ወርቃማ አጋጣሚ አግኝተዋል። ዳግማዊ ዓባይ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ቻርለስ ሙሴጌ ሊጠቀምበት ሲል ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ ጥፋት በመሥራቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ሱራፌል ጌታቸው አስቆጥሮታል። ሆኖም ግን ጉዳት ያስተናገደው ቻርለስ ሙሴጌ በተመስገን ደረሰ ተቀይሮ ለመውጣት ተገድዷል።
በተሻለ ግለት ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ድሬዳዋ ከተማዎች 14ኛው ደቂቃ ላይም መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ሱራፌል ጌታቸው በግሩም ሁኔታ ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው ካርሎስ ዳምጠው በተረጋጋ አጨራረስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል። ብርቱካናማዎቹ አከታትለውም በአሰጋኸኝ ጴጥሮስ እና በሱራፌል ጌታቸው አማካኝነት ተጨማሪ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር።
ቀስ በቀስ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት ወልቂጤ ከተማዎች 33ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን የተሻለ የግብ ዕድላቸውን ፈጥረው ተመስገን በጅሮንድ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሣዬ ከመለሰው በኋላ ዳንኤል ደምሱ ለሙሉዓለም መስፍን አመቻችቶለት ሙሉዓለም በግራ እግሩ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
ብርቱካናማዎቹ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው እየተቀዛቀዙ ሄደው ሠራተኞቹ ጨዋታውን መቆጣጠር ሲችሉ ጋዲሳ መብራቴ ከቀኝ መስመር ሙከራ አድርጎ በአብዩ ካሣዬ ከተመለሰበት በኋላ 45+3ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ዳንኤል ደምሱ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሣዬ በግሩም ቅልጥፍና አስወጥቶበታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ ፉክክሮች ውጪ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያስመለክተን ዘልቆ 62ኛው ደቂቃ ላይ ግን ግብ ተቆጥሮበታል። የድሬዳዋው ካርሎስ ዳምጠው ከሳጥን አጠገብ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ወንድማገኝ ማዕረግ በእጁ ነክቶት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ራሱ ካርሎስ ዳምጠው መረቡ ላይ አሳርፎት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ግብ አድርጎታል።
ወልቂጤ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተር ቢችሉም ከሦስት ጨዋታ ቅጣት የተመለሰው ግብ ጠባቂያቸው ፋሪስ አለው ከካርሎስ ዳምጠው ጋር በተፈጠረ ግጭት በመሳይ አያኖ ለመቀየር ሲገደድ 83ኛው ደቂቃ ላይ ግን ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አዳነ በላይነህ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው መሐመድ ናስር በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል። ይህም የተሻለው ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ 3ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት ቡድናቸውን የሚያነሳሳ ነገር እንደሚያስፈልግ እና በተጋጣሚቸው ዘንድ የተሻለ መነሳሳት እንደነበር በመጠቆም አስበው ከገቡት አንጻር ያልጠበቁትን እንቅስቃሴ እንዳዩ በመናገር ማሸነፍ ብቻ እንደሚያስፈልጋቸው ሲናገሩ የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ሽመልስ አበበ በበኩላቸው ተጋጣሚያቸው መሃል ላይ ጥሩ ኳስ ስለሚጫወት የአማካይ ቁጥራቸውን ማብዛታቸውን ገልጸው ጨዋታውን እንደጠበቁት እንዳገኙት ተናግረዋል።