ሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በአዳማ ሳይንስ እና ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሲጀመር ሁለቱም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
4:00 ላይ በአዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ መካከል የዙሩ የመጀመርያ ጨዋታ ተደርጎ ሁለት አቻ ተጠናቋል። በስፍራው የፌዴሬሽኑ የውድድር ዳይሬክተር አቶ ከበደ ወርቁ፣ የአዳማ ሳ/ቴ/ዩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ለሚ ጉታ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተሾመ አብደላ፣ የአዳማ ከተማ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አንበስ መገርሳ በክብር እንግድነት ተገኝተው ጨዋታውን ያስጀመሩ ሲሆን ቀዳሚው ጎል የተቆጠረው ገና በአንደኛው ደቂቃ ነበር። ድሬዎች ወደ አዳማ የግብ ክልል ይዘው በመሄድ ከመስመር የተሻማውን ኳስ ሊዲያ ጌትነት በግንባሯ ገጭታ በማስቆጠር ድሬዳዋ ከተማን መሪ አድርጋለች።
ከጎሉ በኋላ የተሻለ የተንቀሳቀሱት አዳማዎች የጠራ የግብ እድል ባይፈጥሩም በተደጋጋሚ ወደ ድሬ የግብ ክልል የደረሱ ሲሆን ማጥቃታቸው ፍሬ አፍርቶ በ37ኛው ደቂቃ በሬዱ በቀለ ቡድኗን አቻ አድርጋ ወደ እረፍት አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ድሬዎች እንደ መጀመርያው ሁሉ ጨዋታው እንደተጀመረ ወደፊት ኳስ ይዘው በመሄድ ቃልኪዳን ተስፋዬ ከርቀት መትታ በማስቆጠር በድጋሚ ድሬን መሪ አድርጋለች።
ከመጀመርያው አጋማሽ ተመሳሳይ መልክ በነበረው ጨዋታ አዳማዎች ለአቻነት ጎል ጥረት በማድረግ 70ኛው ደቂቃ ላይ ይታገሱ ተገኝወርቅ ከበሬዱ የተቀበለችውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥራ ቡድኗን አቻ አድርጋለች። በቀሪ ደቂቃዎችም የሚጠቀስ ሙከራ ሳንመለከት 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ 10:00 ላይ መቻል ከ ቦሌ ክፍለ ከተማ ተጫውተው ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል። ጥሩ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ቦሌዎች ኳስ በመያዝ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን መቻሎች ደግሞ ኃይል የቀላቀለ አጨዋወት አስመልክተውናል።
ወደ ጎል በመጠጋት የተሻሉ የነበሩት ቦሌዎች በተለይ በ37ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ለማስቆጠር ተቃርበው የነበረ ቢሆንም የግብ ጠባቂ ስህተት ታክሎበት ትዕግስት ወርቁ አግኝታ ብትመታውም ቤተልሄም በቀለ በግሩም መከላከል አውጥታው ጎል ሳይሆን ቀርቷል።
ከእረፍት መልስ በአንፃራዊነት የተቀዛቀዘ አጋማሽ የነበረ ሲሆን የጠራ ሙከራ ሳንመለከትበት ጨዋታው ያለ ጎል ተጠናቋል።