እጅግ ያነሱ የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት የምሽት ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ እና የጦና ንቦቹ ነጥብ በመጋራት ጨዋታቸውን ፈፅመዋል።
ባህር ዳር ከተማ ሀምበሪቾን ከረታው ስብስብ ባደረጓቸው ሦስት ለውጦች ረጀብ ሚፍታህ ፣ በረከት ጥጋቡ እና ፀጋዬ አበራን በማስወጣት በምትካቸው መሳይ አገኘሁ ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ፍሬው ሰለሞን ዳግም ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት በማምጣት የባለፈው ሳምንት ድሉን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ሲገቡ በወላይታ ድቻ በኩል በሊጉ መሪ ሽንፈት ካጋጠማቸው አስከፊ ሽንፈት ለማገገም በማለም ባደረጓቸው ሦስት ለውጦች ፍፁም ግርማ፣ መሳይ ኒኮል እና እዮብ ተስፋዬ በማስወጣት ኪዳኔ ከበደ፣ ናትናኤል ናሲሮ እና ባዬ ገዛኸኝን ተክተው ቀርበዋል።
የባለፈው የውድድር ዘመን ምስጉን ዋና ዳኛ በነበሩት ፌደራል ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ መሪነት በጀመረው የምሽቱ ጨዋታ በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ባህር ዳር ከተማዎች እንደወሰዱት ብለጫ አደጋ ቀጠና ውስጥ ለመግባት የነበራቸው ሂደት አስፈሪ አልነበረም።
በራሳቸው የሜዳ ክፍል በቁጥር በዝተው መከላከልን ቀዳሚ ምርጫቸው ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች የጣና ሞገዶቹ የሚያደርጉትን ቅብብሎችን በማቋረጥ በፍጥነት ወደ ፊት ለመሄድ ቢያስቡም በሚፈለገው ልክ አስፈሪ መሆን ተስኗቸው አምሽተዋል።
ጨዋታው 18ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ከቀኝ መስመር ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት ፍራኦል መንግስቱ በቀጥታ ወደ ጎል መቶት የግቡ አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ ባህር ዳሮች በጨዋታው የፈጠሩት የመጀመርያው ለጎል የቀረበ ሙከራ ሆኖ ተመዝግቧል።
በጨዋታው ጅማሪ ከተከተሉት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በመውጣት በቁጥር በዝተው ኳሱን ተቆጣጥረው በተሻለ ወደ ፊት መሄድ የጀመሩት የጦና ንቦቹ በዚህ እንቅስቃሴ 32ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ከቀኝ መስመር የላካትን ኳስ ቡዙዓየሁ ሰይፉ በግንባሩ በጥሩ ሁኔታ ቢገጫትም ኳሷ ኢላማውን ሳትጠብቅ
የቀረችበት አጋጣሚ ለቡድኑ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
የጨዋታው ሚዛን ወደ ወላይታ ድቻ አድልቶ በቀጠለው ጨዋታ ጥራት ያላቸው ተጨማሪ ሙከራዎችን ሳንመለከት አጋማሹ ተጠናቋል።
ጨዋታው ከዕረፍት ሲመልስ ብዙም የተለየ ነገር ሳይኖር በተመሳሳይ እንቅስቃሴ የቀጠለ ሲሆን ይልቁንም ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር የጨዋታ እንቅስቃሴ ከሜዳው መጨቀይት ጋር ተዳምሮ ይባስ ብሎ ወደ አሰልቺ ተቀይሯል።
ባህር ዳር ከተማዎች ፊት ላይ የነበረባቸውን የመሳሳት አቅማቸውን ለማሳደግ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይሮ በማስገባት ፍላጎት ቢያሳዩም ስኬታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በጨዋታው 78 ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር በኩል አንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ያደረሱትን ኳስ የዓብስራ ተስፋዬ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ ወደ ጎል መቶት ግብጠባቂው ቢንያም ገነቱ በቀላሉ ሊቆጣጠረው ችሏል ፤ በዚህም ጨዋታው ጎል ሳይቆጠረበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጨዋታው ቀድመው እንደጠበቁት ጠንካራ እንደነበር ጠቁመው በጉዳት ባጧቸው ተጫዋቾች ምክንያት የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ክፍተት እንደነበረባቸው በመግለጽ ወሳኝ ሁለት ነጥቦችን እንደጣሉ ሲናገሩ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በበኩላቸው ካላቸው የተጫዋች ስብስብ አንጻር አንዱ ነጥብ ትልቅ እንደሆነ በመናገር ከትልቅ ሽንፈት መልስ ከትልቅ ክለብ ጋር ተጫውተው ነጥብ መጋራታቸው እንዳስደሰታቸው በመጠቆም የያዙት የተጫዋቾች ስብስብ ሦስተኛው አማራጫቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።