በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተካሄደው የምሽቱ ጨዋታ ፈረሰኞቹን ከሰባት ጨዋታ በኋላ ወደ ድል ሲመልስ ሲዳማ ቡናዎች ተከታታይ ሁለተኛ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል።
ባለ ሜዳዎቹ ሲዳማ ቡናዎች በአዳማ ከተማ ሽንፈት ካስተናገደው ቡድናቸው ሁለት ተጫዋቾችን ለውጠዋል ደስታ ዮሐንስ እና ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃንን በማሳረፍ አበባየሁ ዮሐንስ እና ማይክል ኪፕሩቪን ይዘው ገብተዋል። በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ስብስባቸው ፍሪምፖንግ ሜንሱ፣ አማኑኤል ኤርቦ እና ዳዊት ተፈራ በማሳረፍ ሻሂዱ ሙስጠፋ፣ ብሩክ ታረቀኝ እና ሞሰስ ኦዶ ለዛሬው ጨዋታ ተጠቅመዋል።
በበርካታ ተመልካቾች ታጅቦ ኢንተርናሽናል አልቢትር አሸብር ሰቦቃ ባስጀመሩት ይህ ጨዋታ በጎል ሙከራዎች አይታጀብ እንጂ እንደ ደጋፊው ድባብ ሞቅ ብሎ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ሞቅ ብሎ ነበር የጀመረው። ሲዳማ ቡናዎች በአንፃራዊነት ጫና ፈጥረው በጀመሩበት የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ውስጥ በ16ኛው ደቂቃ ማይክል ኪፕሮቪ የአማኑኤል ተርፉ መዘናጋትን ተከትሎ ኳሱን ታግሎ በመንጠቅ ወደ ጎል የመታውን ግብ ጠባቂው ባህሩ ሲመልሰው ለጎሉ በቅርብ ርቀት የነበረው ይገዙ ቦጋለ በማይታመን ሁኔታ ወደ ላይ የሰደዳት አጋጣሚ የሚያስቆጭ ነበር።
ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ለመውጣት የተቸገሩት ፈረሰኞቹ በአንድ ሁለት አጋጣሚ የግራ መስመር ተከላካዩ ሻሂዱ ወደ ፊት በመሄድ ከሚያደርገው ጥረት ውጭ እንብዛም አስፈሪ ያልነበረው ቡድናቸው በ31ኛው ደቂቃ ግን ግልፅ የጎል ዕድል መፍጠር ችለው ነበር። ሞሰስ በጥሩ መንገድ የላከለትን ተገኑ ተሾመ ኳሱን ወደ ፊት በመግፋት ብቻውን ከግብ ጠባቂው መክብብ ደገፋ ቢገናኝም መክብብ አምክኖበታል።
በአጋማሹ የረባ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳንመለከት ተቀዛቅዞ የተጠናቀቀው የምሽቱ ጨዋታ ከዕረፍት ሲመለስ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ በአሰልቺነቱ ቀጥሏል። አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ፈጣን ቅያሪ በማድረግ ፍቅረኢየሱስ እና አቤኔዘርን ቀይረው በማስገባት ቶሎ ቶሎ ወደ ማጥቃቱ ዞን ቢገቡም በአጥቂዎቻቸው የውሳኔ ችግር ጥረታቸው እንዳይሳካ ሆኗል። ፈረሰኞቹ ባልተደራጀ የቡድን ሥራ ምክንያት ኳሱን ተቆጣጥረው በተገቢው መንገድ ለአጥቂዎቻቸው ጥራት ያላቸው ኳሶች የማያደርሱ በመሆናቸው ለጎል የቀረበ ሙከራ ለማድረግ በእጅጉኑ ሲቸገሩ ተመልክተናል።
በተለያዩ ምክንያቶች የጨዋታው እንቅስቃሴ እየተቆራረጠ ለደጋፊዎች በማይመጥን ሁኔታ እጅግ አሰልቺ በሆነ መንገድ ቢቀጥልም የጨዋታውን ግለት ከፍ ያደረገች ጎል በ77ኛው ደቂቃ ፈረሰኞቹ አግኝተዋል። ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ኤርቦ ራሱ ያዘጋጀውን ኳስ በረከት ወልዴ በጥሩ መንገድ ከተከላካይ ጀርባ ለራሱ አማኑኤል የተጣለለትን በድንቅ አጨራረስ ቦታ አይቶ በተረጋጋ ሁኔታ መረቡ ላይ አስቀምጦት ለቡድኑ እፎይታ ሰጥቷል።
ከጎሉ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታው ለመግባት በተደጋጋሚ ወደ ፊት የሄዱት ሲዳማ ቡናዎች 87ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ብርሀኑ በቀለ በጠንካራ ምት ወደ ጎል የላከውን ግብጠባቂው ባህሩ ነጋሽ እንደምንም ኳሱን በእግሩ አውጥቶበታል። በአንፃሩ ሻሂዱ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ያሻገረለትን አማኑኤል ኤርቦ በግንባሩ የገጨው እና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣው ለፈረሰኞቹ ሁለተኛ ጎል ለመሆን የሚችል አጋጣሚ ሆኖ ጨዋታውን አንድ ለምንም በሆነ ውጤት አሸንፈው ወጥተዋል።
ተከታታይ ሁለተኛ ሽንፈት ያስተናገዱት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በአስተያየታቸው ጨዋታው ያን ያህል ከባድ ያልነበረ ቢሆንም የራሳቸው ተጫዋቾች ጨዋታውን እንዳከበዱት ተናግረው። በመጀመርያው አጋማሽ ያገኙትን ለመሳት የሚከብድ ጎል ማምከናቸው ጨዋታውን እንዳከበደባቸው እና ያልገመቱት ውጤት እንደተመዘገበ ተናግረዋል። በዋና አሰልጣኝነት ቡድኑን ከተረከቡ በኋለ የመጀመርያ ድል ያሳኩት አሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬ በበኩላቸው ድሉ ለቡድናቸው የቀጣይ ጨዋታ በስነልቦናው እንደሚያዘጋጃቸው ገልፀው በመጀመርያው አጋማሽ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው በማሸነፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።