በተርኪ ሊግ ካይዘሪስፖር የሚጫወተው የመስመር ተጫዋች ሀገሩ ጊኒ ቢሳው ከኢትዮጵያ እና ግብፅ ጋር ባለባት ጨዋታ ግልጋሎት እንደማይሰጥ ይፋ አደረገ።
ካናዳ፣ አሜሪካ እና ሜክሲኮ በጋራ በሚያዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የተለያዩ ሀገራት የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ ይገኛሉ። ሀገራችን ኢትዮጵያም በምድብ አንድ ተደልድላ የምትገኝ ሲሆን የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታዎቿንም የፊታችን ሀሙስ እና እሁድ ከጊኒ ቢሳው እንዲሁም ጂቡቲ ጋር ታከናውናለች።
ኢትዮጵያን በሜዳዋ የምታስተናግደው ጊኒ ቢሳው ቀድማ ከጠራቻቸው 25 ከሀገር ውስጥ ሊግ ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾች አንዳንዶቹን በጉዳት እያጣች የነበረ መሆኑን ባለፉት ቀናት መረጃዎችን ስናጋራ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ የቡድኑ ወሳኝ የመስመር ተጫዋች ከጨዋታዎቹ ውጪ መሆኑ ተሰምቷል።
በኢትዮጵያ እና ግብፅ ጨዋታ ለብሔራዊ ቡድኑ ግልጋሎት የማይሰጠው ተጫዋች ካርሎስ ማኔ ነው። የ30 ዓመቱ የመስመር ተጫዋች በግል የኢንስታግራም ገፁ እንዳስታወቀው ከሆነ በተርኪ ሊግ ከሚወዳደረው ክለቡ ካይዘሪስፖር ጋር ያለው ውል ባለንበት ወር የሚጠናቀቅ በመሆኑ ከክለቡ ጋር ያለውን የወረቀት ስራዎች ለመፈፀም ቡድኑን እንደማይቀላቀል አስታውቋል።
ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ሌላ መረጃ ፋሊ ካንዴ፣ ማርሲያኖ ቻሚ፣ ዚ ቱርቦ እና ቡራ የተባሉት ከሀገር ውስጥ ሊግ ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾች በትናንትናው ዕለት ቢሳው የሚገኘውን ስብስብ እንደተቀላቀሉ ተመላክቷል።