“የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚባል ውድድር ከመጥፋቱ በፊት የፋይናንስ ስርዓቱ መስተካከል አለበት” ሥራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ ሰይፈ
“ላይተገበር የሚወጣ ሕግ የለም” የፋይናንስ አስተዳደሯ ማስተዋል አስረስ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አ.ማ በ2017 ዓ.ም በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ላይ ተግባራዊ በሚያደርገው “የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ” ላይ ለስፖርቱ ሚድያ ባለሙያዎች ዛሬ በካፒታል ሆቴል ከቀኑ 08፡00 ጀምሮ የግማሽ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መድረክ ተዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።
መርሐግብሩን የከፈቱት የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ቆይታቸው ረጅም ቢሆንም ከአደረጃጀታቸው እና ከክለብ ላይሰንሲንግ አኳያ ውስንነት እየታየባቸው በመሆኑ በዚህ የክፍያ ስርዓት ከቀጠሉ ፕሪሚየር ሊጉ ይቆማል ወይም ከነጭራሹ ይጠፋል ብለው እንደሚሰጉ በመግለጽ “አሳፋሪ” ብለው በገለጹት አሠራር መሠረት ሊጉ ሳይፈርስ መመሪያ ማዘጋጀቱ ግዴታ እንደሆነባቸው ተናግረዋል።
ሥራ አስኪያጁ ከዚህ በፊት የተጫዋች ደመወዝ 50ሺህ ተወስኖ አንድ ቀን ሳይሞላው ሕጉ መፍረሱን በማስታወስ የተረጋጋ የእግርኳስ ውድድር ለመፍጠር ስላዘጋጁት ሰነድ ተፈጻሚነት የስፖርቱ ሚዲያዎች ክትትል እያደረጉ ተቋማት በትክክል እየሠሩ መሆን አለመሆናቸውን በትክክለኛ መንገድ መዘገብ እንደሚገባቸው አበክረው ገልጸዋል።
በመቀጠል “ተግባራዊ ላይደረግ የሚወጣ ሕግ የለም” ያሉት የአክሲዮን ማኅበሩ የፋይናንስ አስተዳደር ኃላፊ የሆኑት ማስተዋል አስረስ በበኩላቸው “የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የክፍያ ሥርዓት አስተዳደር መመሪያ”ን በጥልቀት ሲያብራሩ በተለይም ስለ መመሪያው ዓላማ ፣ ስለ ተፈጻሚነት ወሰን ፣ ስለ አፈጻጸም ሂደቶች እና ስለ ተከለከሉ ተግባራት ፣ ስለ ፋይናንስ አሠራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ፣ ስለ ፋይናንስ አስተዳደር ቁጥጥር አደረጃጀት ስርዓት እና ውሳኔ አሰጣጥ ፣ ስለ ይግባኝ ሰሚ ፣ ስለ ቅጣቶች እና የተፈጻሚነት መመሪያው ስለሚፀናበት ጊዜ በጥልቀት አብራርተዋል።
ይህ መመሪያ ሚያዚያ 17/2016 በተደረገው 4ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ የጸና እንደሚሆን የተጠቆመ ሲሆን በአንቀጽ 9 ከተደነገጉ ቅጣቶች አንጻር
9.1 በዚህ መመሪያ አፈጻጸም ረገድ የሚቀርበው መረጃ ፣ ሰነድ እና ማስረጃ ሐሰተኛ ፣ የተጭበረበረ ወይም አሳሳች በሆነ መልኩ ያቀረበ ክለብ እና የክለብ አባል ከሊጉ ውድድር ያለምንም ማስጠንቀቂያ ይሰናበታል። ይህንን ያቀረበው ክለብ ከሆነ በማኅበሩ ውስጥ ያለው አክሲዮን ይሰረዛል፣ በተወዳዳሪነቱ የሚፈጸምለት ክፍያም ካለ ሙሉ ለሙሉ ለጽ/ቤቱ ገቢ ይሆናል።
9.2 የክለቡን የአንድ ወር ጥቅል ደመወዝ ሪፖርት በጊዜ ገደብ ውስጥ ለጽ/ቤቱ ያላቀረበ ፤ ቀነ ገደቡ ባለቀ በመጀመሪያው ቀን ብር ሃምሳ ሺህ ይቀጣል።
9.2.1. ሰነዱን እስኪያስገባ ተጨማሪ 10(አስር) ቀን ይሰጠዋል። ከዚህ ቀን በኋላ በሚኖር በእያንዳንዱ ሰነዱን ላስገባበት ቀን ተጨማሪ ብር 10 ሺህ ቅጣት ታክሎ መክፈል አለበት።
9.2.2. መቅረብ የነበረበት ሪፖርት ለ30 ቀናት የዘገየ እንደሆነ ተጨማሪ 3 ነጥብ ተቀናሽ ይደረጋል። ነጥብ የሌለው እንደሆነ ወደፊት ከሚያገኘው ነጥብ እንዲቀነስ ለውድድር እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ውሳኔውን እንዲያስፈጽም ያሳውቃል።
9.3 ወርሃዊ ደመወዝ ጣሪያውን የሚተላለፍ ስለመሆኑ የሚያሳይ ጠቋሚ ማስረጃ ሲገኝ
9.3.1 በጽሑፍ ስለሁኔታው ውጤቱ ማስገንዘቢያ ደብዳቤ ይሰጠዋል።
9.3.2 የበጀት ዓመቱን ከክፍያ ጣሪያ በላይ እስከ ብር 5 ሚሊዮን መተላለፉ ከተረጋገጠ “21” ነጥቦች ይቀነስበታል። ከብር 5 ሚሊዮን በላይ ከተሰጠው የክፍያ ጣሪያ በላይ መተላለፉ ከተረጋገጠ “ከሊጉ ይሰናበታል።”
9.4 የቅድመ ክፍያ ደመወዝ እና ፊርማ የከፈለ ክለብ
9.4.1 ድርጊቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ ስፖርት ክለቡ 3 ሚሊዮን ብር ለክለቡ ሥራ አስኪያጅ ፣ ፕሬዚደንት ፣ ቦርድ አባል/ሥራ አስፈጻሚ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል።
9.4.2 ድርጊቱ ከአንድ አባል በላይ ወይም ለሁለተኛ ጊዜ ተፈጽሞ ቢገኝ ክለቡ በውድድር ዓመቱ የተጫዋች ዝውውር እንዳያደርግ ለእያንዳንዱ ድርጊት 3 ሚሊዮን ይቀጣል። የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ፣ ፕሬዚዳንት እና በውሳኔው የተሳተፉ የቦርድ አባላት/ ሥራ አስፈጻሚ ለሁለት የውድድር ዘመን ከማንኛውም ክለብ አመራርነት እንዳይሳተፉ ይታገዳሉ።
9.4.3 ክፍያውን የተቀበለው የክለብ አባል ድርጊቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ከፈጸመ 200 ሺህ ብር ይቀጣል። ቅድመ ክፍያውንም በሰባት ቀናት ውስጥ ለአክሲዮን ማኅበሩ ተመላሽ ማድረግ ይኖርበታል። ቅድመ ክፍያውንም ተመላሽ እስኪያደርግ ድረስ ከውድድር ይታገዳል።
9.4.4 ተቀባዩ ድርጊቱን የፈጸመው ለሁለተኛ ጊዜ ከሆነ ለሁለት ዓመት በሊጉ ውስጥ ከማንኛውም ዓይነት ውድድር እገዳ ይጣልበታል።
9.5 በአክሲዮን ማኅበሩ ካስመዘገበው የባንክ አካውንት ውጪ ክፍያ የሚያደርግ ክለብ
9.5.1 ክለቡ ድርጊቱን የፈጸመው ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ 6 ነጥብ እና በእያንዳንዱ ተከፋይ አባል ብዛት ልክ ብር 3 ሚሊዮን ይቀጣል።
9.5.2 ጥፋቱ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸመ ከሆነ ክለቡ “ከሊጉ እንዲወርድ” ይደረጋል።
9.6 ደጋፊ የክፍያ ሰንጠረዥን ከባንክ ማስረጃዎች ጋር በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በየወሩ ወይም ሲጠየቅ ያላቀረበ ክለብ
9.6.1 ጥፋቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ 50 ሺህ ብር ይቀጣል።
9.6.2 የውድድር ዘመኑ እስከሚጠናቀቅ ባሉት ቀጣይ ወራቶች ተመሳሳይ ጥፋት ከፈጸመ ቅጣቱ በብር 100ሺህ እየጨመረ ይሄዳል።
9.7 በሦስተኛ ወገን ክፍያ የተቀበለ
9.7.1 የክለብ አባሉ ጥፋቱን የፈጸመው ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ ቅጣት ብር 200ሺህ እና በሦስተኛ ወገን የወሰደውን ገንዘብ ለአክሲዮን ማኅበሩ ገቢ ያደርጋል።
9.7.2 ጥፋቱ ለሁለተኛ ጊዜ ከሆነ 500ሺህ ብር ፣ በሦስተኛ ወገን የወሰደውን ገንዘብ ለአክሲዮን ማኅበሩ ገቢ ያደርጋል። የአንድ ዓመት ዕገዳ ይጣልበታል።
9.8 በመመሪያው መሠረት ለቀረበ የምርመራ ጥያቄ ምላሽ ያልሰጠ ክለብ ወይም የክለብ አባል
9.8.1 ጥያቄው በቀረበለት 10 ቀናት ውስጥ በጽሑፍ ምላሽ ካልሰጠ የ20ሺህ ብር ቅጣት እና ተጨማሪ ምላሽ እንዲሰጥ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል።
9.8.2 በተጨማሪ 5 ቀናት ውስጥ ምላሽ ካልሰጠ የ500 ሺህ ብር ቅጣት ይጣልበታል።
9.8.3 ምርመራው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ያልተባበረ ክለብ በሚቀርበው ሪፖርት መሰረት ከ15 ነጥብ ቅነሳ ጀምሮ ከሊጉ እንዲወርድ እና በማኅበሩ ያለው አክሲዮን ተሰርዞ በተሳታፊነት የሚፈጸሙ ክፍያ መብቱን እስከማሳጣት የሚደርስ ውሳኔ ይሰጥበታል።
የፋይናንስ አስተዳደሯ ማስተዋል አስረስ ይህንን በጥልቀት ካብራሩ በኋላ የሚዲያ ባለሙያዎች ላነሷቸው ጥያቄዎች በእሳቸው እና በሥራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ ሰይፈ መልስ ሲሰጥበት በተለይም ከዋጋ መናር ጋር ተያይዞ በዘንድሮ አማካይ ወጪ ለከርሞው በተመሳሳይ ማሰቡ አስቸጋሪ ስለሚሆንበት ሁኔታ ፣ ከጠረጴዛ ስር ስለሚደረጉ ድርድሮች ፣ ስለ ወገንተኝነት ፣ እንደ መቻል ላሉ ኦዲት ስለማይደረጉ ተቋሞች ፣ ችግር የሚፈጥረው ክለብ መፍትሔ ፈልጉልኝ ብሎ መማጸን ስለማብዛቱ ፣ የተጫዋቾች መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆን…እና በርካታ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች ቀርበው ሥራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ ሰይፈ እንደዚህ ዓይነት ፕሮግራም ማዘጋጀታቸው እና እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች መነሳታቸው ግብዓት እንደሚሆናቸው ጠቁመዋል።