በዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ምክንያት የተቋረጠው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አስቀድሞ በወጣለት መርሐ-ግብር ይጀምር ይሆን በሚለው ዙርያ የተጠናከረ ዘገባ
የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሊጠናቀቅ የአራት ሳምንታት ጨዋታዎች በቀረበት በአሁኑ ወቅት ከባለፈው ሳምንት አንስቶ ብሔራዊ ቡድን ከፊቱ ለሚኖሩት የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች እና ዝግጅት ሲባል ሊጉ መቋረጡ ይታወሳል። የውድድሩ የበላይ አካል አክስዮን ማህበሩ ሊጉ ከብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች መልስ ውድድሩ ከ27ኛ – 30ኛው ሳምንት ሐሙስ ሰኔ 06 ተጀምሮ ቅዳሜ ሰኔ 29 እንደሚጠናቀቅ የውድድሩ ቦታም በሀዋሳ ከተማ – ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚሆን ከቀናት በፊት ይፋ መደረጉ ይታወቃል።
ብሔራዊ ቡድኑ መጀመርያ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታውን ባለፈው ሐሙስ ሲያከናውን ቀሪ አንድ ጨዋታውን ነገ ምሽት ካደረገ በኋላ ቡድኑ ወደ ሀገር ቤት የሚመለሰው ማክሰኞ ምሽት በመነሳት ረቡዕ ሰኔ 5 ቀን ማለዳ አዲስ አበባ እንደሚደርስ አውቀናል። ይህን ተከትሎ የሊጉ ክለቦች ተጫዋቾቻቸው ለብሔራዊ ቡድን ከሰጡት ግልጋሎት እና ከነበረው የጉዞ ድካም አንፃር ለጨዋታው የሚኖራቸው ዝግጅት ያለ በቂ ዕረፍት በቀጥታ ወደ ውድድር ማስገባት በውጤታቸው ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ተሳቢ በማድረግ ውድድሩ ከሚጀምርበት ከሰኔ 6 ቀን የተወሰነ ሽግሽግ ይደረግበት የሚል ጥያቄ ክለቦች እያነሱ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ይሄን በመያዝ ውድድሩ ቀድሞ ከወጣለት መርሐ ግብር ማሻሻያ ሊደረግበት ይችላል ወይ በማለት ሶከር ኢትዮጵያ ለጉዳዮ ቅርበት ካላቸው አካላት እንዳገኘችው ምላሽ ከሆነ “ብሔራዊ ቡድኑ የሚመጣው ማክሰኞ እንደሆነ ከፌዴሬሽኑ መረጃ እንዳላቸው እና ረቡዕ እንደሚመለሱ እንደማያቁ ገልፀው። ውድድሩ አሁን ከወጣለት መርሐ-ግብር የሚሸጋሸግ ከሆነ ወደ ሐምሌ ወር እንዲገፋ ስለማይፈለግ ምንም ዓይነት ለወጥ እንደማይደረግ አሰቀድሞ በተያዘለት ጊዜ መሠረት እንደሚጀምር ማረጋገጫ ሰጥተውናል።
በለተለይ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች ለአወዳዳሪው አካል መርሐ-ግብሩ ይስተካከልልን የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረቡ ከመሆኑ አንፃር በዚህ ዙርያ የሚፈጠሩ አዳዲስ ነገሮች ካሉ ተከታትለን ወደ እናተ የምናደርስ ይሆናል።