በ13 ክለቦች መካከል እንደሚደረግ የሚጠበቀው የሴካፋ ካጋሜ ካፕ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ሲለዩ የውድድሩ ቀንም ማሻሻያ ተደርጎበታል።
የምስራቅ እና መካከለኛውን የአፍሪካ ሀገራትን ያቀፈው ሴካፋ የቀጠናውን የተለያዩ የብሔራዊ ቡድኖች ውድድር ከማዘጋጀቱ በተጨማሪ እንደ ሴካፋ ካጋሜ ካፕ ያሉ የክለቦችን ውድድርም እንደሚያደርግ ይታወቃል። ያለፉትን ሁለት ዓመታት ያልተከናወነው ይህ የሴካፋ የክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ቀድሞ ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ የቀን ማሻሻያ ተደርጎበት ከሰኔ 29 እስከ ሐምሌ 15 ድረስ በታንዛኒያ እና ዛንዚባር ይከናወናል።
በዚህ ውድድር የቀጠናው ሀገራት ክለቦች በንቃት እንደሚሳተፉ ሲጠበቅ ቢቆይም ሀገራችን ኢትዮጵያ በውድድሩ ተሳታፊ እንደማይኖራት ይፋ ሆኗል። ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምንም የወጣ መረጃ ባይኖርም ሴካፋ ይፋ ባደረገው የውድድሩ ተሳታፊዎች ዝርዝር ላይ ኢትዮጵያዊ ክለብ አለመኖሩ ታይቷል።
የዲ አር ኮንጎ ቲፒ ማዜምቤ፣ የማላዊው ናያሳ ቢግ ቡሌትስ እንዲሁን የዛምቢያው ሬድ አሮስ ተጋባዥ ክለቦች መሆናቸው ሲረጋገጥ በቀጠናው ከሚገኙ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ኬኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ዛንዚባር እና ደቡብ ሱዳን ከተወጣጡ ክለቦች መካከል ውድድሩ የሚከናወን ተገልጿል።