የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የፍፃሜ ተፈላሚ በነበሩ ክለቦች ላይ የቅጣት ውሳኔዎች ተጥለዋል።
የ2016 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድርን የየምድቦቻቸው የበላይ በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደጉት አርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሳምንታት በፊት የዓመቱ አሸናፊነታቸው የሚለይ የዋንጫ ጨዋታ በአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ተዘጋጅቶ በመጨረሻ በፍፁም ቅጣት ምት በተቆጠረች ብቸኛ ግብ አርባምንጭ ከተማ ሻምፒዮን መሆኑ ይታወሳል። በጨዋታው ዕለት በሁለቱም ክለቦች በኩል የስነ ምግባር ጥሰቶች ተፈፅሟል ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ቅጣትን አስተላልፏል።
1. የኢትዮ ኤሌክትሪክ በ83ኛ ደቂቃ ላይ የተሰጠውን ፍ ቅ ምት በመቃወም ውድድሩን ተጠናቆ ዳኞች ወደ መልበሻ ክፍል በመግባት ላይ እያሉ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብ አርማ የለበሱ ደጋፊዎች ውሀ በተሞላ ፕላስቲክ ወርውረው ዋና ዳኛውን ስለመማታታቸው በዳኞችና በታዛቢዎች ሪፖርት ተገልጾል። በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተሻሻለው የዲስኘሊን መመሪያ ምዕራፍ 3 አንቀፅ 66 ተ.ቁ 3 ፊደል ሀ መሰረት 25.000 /ሃያ አምስት ሺህ ብር/ ቅጣት ተወስኖበታል፡፡
2. የኢትዮ ኤሌክትሪክ ዋና አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ እንዲሁም የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ መሐመድ አህመድ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ የጨዋታ አመራሮችን አፀያፊ ስድብ በመሳደባቸው በኢ እ ፌ የተሻሻለው የዲስኘሊን መመሪያ ምዕራፍ 3 አንቀፅ 66 ተ.ቁ 1 በተጠቀሰው መሰረት ከላይ በስም የተገለጽት የቡድን አመራሮች እያነዳንዳቸው የብር 5000.00 /አምስት ሺህ የገንዘብ ቅጣትና በተጨማሪም ቡድናቸው ወደፊት ከሚያደርገው መደበኛ ጨዋታ 6 /ስድስት/ ጨዋታ ቅጣት ተወስኖባቸዋል፡፡
3. የአርባ ምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ጋር በተጫወቱበት ዕለት የአርባ ምንጭ ቡድን ደጋፊዎች ደስታቸውን ለመግለጽ ወደ ሜዳ በመግባት በተፈጠረው ሁከት ግርግር፦
3.1. የአበበ ቢቂላ ስታድየም 89 /ሰማንያ ዘጠኝ የኘላስቲክ ወንበሮች የአንዱ ዋጋ 1000.00 /አንድ ሺህ ብር/ ሂሳብ ብር 89.000 /ሰማንያ ዘጠኝ ሺህ/ ብር እንዲከፍሉ
3.2. በቀኝ ጥላ ፎቅ የሚገኘውን የቡድን አባላቶች የሚቀመጡበት የኘላስቲክ የፀሐይ መከላከያ ግማሽ መስታወት የተሰበረ በመሆኑ ማሰሪያ 7500 /ሰባት ሺህ አምስት መቶ/ ብር ሂሳብ እንዲከፍሉ
3.3. ከብረት የተሰራ ሦስት የመቆሚያ የመድረክ ጠረጴዛ የተሰበረ ስለሆነ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር እንዲያስጠግኑ
3.4. ተመልካችን ከተጫዋች የሚለየው የስታድየሙ ዙሪያ አጥር ሙሉ ለሙሉ በደጋፊዎች ከጥቅም ውጭ በመሆኑ ከስታድየሙ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ሙሉ ጥገና እንዲያደርጉ ተወስኗል፡፡
3.5. የአርባ ምንጭ ቡድን አርማ የለበሱ የክለቡ ደጋፊዎች ጨዋታው ተጠናቆ የጨዋታ አመራርሮች እና ተጫዋች ከሜዳ ላይ ወጥቶ የአጥሩን ሰብረው ወደ ሜዳ በመግባት የኘሮግራም መዝጊያውን በአግባቡ እንዳይከናወን በማድረጋቸው እና ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በፀጥታ ኃይል ሊወጡ ችለዋል። ስለሆነም ይህንን ድርጊት መፈጸማቸው በአወዳዳሪው ኮሚቴ በግልጽ የታየና በእለቱ የጨዋታ አመራሮች እና ታዛቢዋች ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡ በዚህም መሰረት በኢ እ ፌ በተሻሻለው የዲስኘሊን መመሪያ ምዕራፍ 3 አንቀፅ 66 ተ.ቁ 3 በፊደል ሀ መሰረት ብር 150,000 /አንድ መቶ ሀምሳ ሺህ ብር/ ቅጣት ተወስኖበታል።