በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ መቻል ተቀይሮ በገባው አብዱ ሞታሎባ ግሩም ጎል ከሊጉ መሪ ያለውን ነጥብ ወደ ሦሰት ዝቅ ያደረገበትን ውጤት ፋሲል ከነማን 1-0 በመርታት አስመዝግቧል።
ፋሲል ከነማዎች ሊጉ ከመቋረጡ በፊት በመሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት ካስተናገደው ቡድናቸው ምኞት ደበበ ፣ ጋቶች ፓኖም እና ጃቢር ሙሉን በሽመክት ጉግሳ ፣ ዓለምብርሀን ይግዛው እና ኤልያስ ማሞ ሲተኩ ከሻሸመኔ ከተማ ጋር በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንታቸው ነጥብ የተጋሩት መቻሎች በበኩላቸው አስቻለው ታመነን በነስረዲን ሐይሉ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶን በዮሐንስ መንግሥቱ ለውጠው ገብተዋል።
ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ የአልጄሪያ እና ጊኒን ከዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ መልስ በመሩት የሁለቱ ቡድኖች የሳምንቱ ተጠባቂ መርሀግብር የመጀመሪያው አጋማሽ አስቀድሞ ከተሰጠው ግምት አንፃር ሜዳ ላይ ቡድኖቹ ከሚያደርጉት ደካማ እንቅስቃሴ በተጨማሪ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚሄዱበት ጥረት እጅጉን ውስንነቶች ይታይባቸው ነበር። በመስመሮች በኩል የሚደረጉ የማጥቂያ መነሻዎችን በመጠቀም ግቦችን ለማግኘት ሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ አቀራረብን ቢያስመለክቱንም በጨዋታው ጥራት ያለውን የግብ ዕድል ለመመልከት ጨዋታው አስናፍቆን ረጅሙን ደቂቃ ቆይቷል።
ተደጋጋሚ ሜዳ ላይ በሚሰሩ ጥፋቶች ይቋረጥ የነበረው የጨዋታው ሂደት እንደነበረው ወረድ ያለ አቀራረብ ሁሉ ጥራት ያለውን የግብ ዕድል ያየነው 42ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ፋሲሎች በይበልጥ የጥቃት ምንጫቸው ካደረጉበት የቀኝ የሜዳ ክፍል ወደ ሳጥን የተላከን ኳስ ጌታነህ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ሲመታ ግርማ ዲሳሳ በእጅ መንካቱን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ መምታት ቢችልም የግብ ዘቡ አልዮንዚ ናፊያን በጥሩ ብቃት ኳሷን አምክኗታል። ሳቢነቱ የደበዘዘው እና በእጅጉም ደካማ የነበረው የመጀመሪያው አርባ አምስትም ያለ ጎል ተገባዷል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታ ተመልሶ ሲቀጥል በብዙ ነገሮች ከቀዳሚው አጋማሽ የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል። ምንይሉ ወንድሙን በአቤል ነጋሽ በመተካት ወደ ሜዳ የገቡት መቻሎች 48ኛው ደቂቃ ላይ አከታትለው ሁለት ሙከራዎች አድርገዋል። አማካዩ ዮሐንስ መንግስቱ ከቀኝ በኩል የደረሰውን ኳስ ነፃ ቦታ ለነበረው አቤል ቢሰጠው አጥቂው ወደ ላይ ኳሷን የሰደዳት እና ከነዓን ማርክነህ ወደ ቀኝ የላከለትን ሽመልስ በቀለ በቀኙ ቋሚ ብረት አስታኮ ወደ ውጪ አውጥቶታል። ቃልኪዳን ዘላለም የተሰለፈበትን የግራ መስመር ከመሐል በሚገኙ ተለጣጭ ኳሶች አዘውትረው ለመጠቀም የሚሞክሩት ፋሲሎች 55ኛው ደቂቃ ጌታነህ ወደ ግብ መቶ አሊዮኒዝ ናፊያን ሲመልስበት 60ኛው ደቂቃ አፍቅሮት ለቃልኪዳን ወደ ግራ አቀብሎት ተጫዋቹ በቶሎ ያገኛትን አጋጣሚ ቢመታም ንቁው አሊዮንዚ አግዶበታል።
የመጨረሻዎቹን ሀያ አምስት ደቂቃዎች ጨዋታውን ወደ ራሳቸው በማድረግ ብልጫውን እየያዙ የመጡት መቻሎች ታውኮ የነበረውን የመሐል ክፍል ካረጋጉ በኋላ ከፍ ባለ ተነሳሽነት መጫወትን ቀጥለው በረከት ከግራ በግቡ አግዳሚ ከላካት ዕድል መልስ 68ኛው ደቂቃ ሽመልስ ከተከላካዮች መሐል ለመሐል አሾልኮ የሰጠውን በረከት መረቡ ላይ አሳረፈው ተብሎ ሲጠበቅ ሳማኪ በጥሩ ዕይታ ኳሷን መልሶበታል። የፋሲልን የኋላ አጥር ለመፍረስ ግብ ለማስቆጠር መታተራቸውን የቀጠሉት መቻሎች 86ኛው ደቂቃ ላይ ከፋሲሉ ዳግም አወቀ እግር ስር የተነጠቀን ኳስ ከነዓን ማርክነህ በአግባቡ አመቻችቶለት ተቀይሮ የገባው ቶጓዊው አጥቂ አብዱ ሞታሎባ ከሳጥን ውጪ እጅግ ግሩም ጎልን ከመረብ አሳርፎ መቻልን አሸናፊ አድርጓታል።
ከጨዋታው መቋጫ በኋላ የፋሲል ከነማው ረዳት አሰልጣኝ ሙሉቀን አቡሀይ ጨዋታው ከባድ እንደነበር ጠቁመው በጨዋታው ያገኙት እና ጌታነህ ከበደ ያመከናት የፍፁም ቅጣት ምት አለመጠቀማቸው ቡድናቸውን ጫና ውስጥ እንደከተታቸው በንግግራቸው ገልፀዋል። የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸው ጥሩ እንደተጫወቱ ጠቁመው የፍፁም ቅጣት ምቱ ቢቆጠርባቸው መልሰው ያገቡ እንደነበር በማስረዳት ከዕረፍት መልስ ባደረጉት የታክቲክ ለውጥ ውጤትን ይዘው ሊወጡ እንደቻሉ ተናግረዋል።