ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስን በተከታታይ አሸንፏል

ፍጹም ተቃራኒ አጋማሾችን ባስመለከተው የምሽቱ ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ በተመስገን ደረሰ ብቸኛ ግብ ፈረሰኞቹን 1-0 ረተዋል።

በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ድሬዳዋ ከተማዎች በ26ኛው ሳምንት ወልቂጤ ከተማን 3ለ0 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ዳግማዊ ዓባይ ፣ ቴዎድሮስ ሀሙ ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና ቻርለስ ሙሴጌ ወጥተው መሐመድ አብዱለጢፍ ፣ ኤልያስ አህመድ ፣ ተመስገን ደረሰ እና አሜ መሐመድ ገብተዋል። ፈረሰኞቹ በአንጻሩ ሲዳማ ቡናን 1ለ0 ካሸነፉበት አሰላለፍ ባደረጉት የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ ሄኖክ አዱኛ ፣ ረመዳን የሱፍ ፣ ናትናኤል ዘለቀ ፣ ቢኒያም በላይ እና ሞሰስ ኦዶ ወጥተው ብሩክ ታረቀኝ ፣ አማኑኤል እንዳለ ፣ ዳዊት ተፈራ ፣ ፍሪምፖንግ ክዋሜ እና የአብሥራ ተስፋዬ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተካተዋል።

ምሽት 12 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ተከተል ተሾመ መሪነት ሕይወቱ ላለፈው የድሬዳዋው የልብ ደጋፊ ፍጹም የአንድ ደቂቃ የሕሊና ጸሎት ተደርጎ የተጀመረው ጨዋታ በሁለቱም በኩል ክፍት እንቅስቃሴ ቢደረግበትም የጠሩ የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩበትም ነበር።

ለተመልካች ሳቢ ሳይሆን በዘለቀው ጨዋታ 22ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ በግራ መስመር ከማዕዘን ያሻማው ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ ያገኘው የቅዱስ ጊዮርጊሱ በረከት ወልዴ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ በመጠኑ  ተጠቃሽ ነው።

በአጋማሹ ብቸኛ የሆነው የጠራ የግብ ዕድል 33ኛው ደቂቃ ላይ ተፈጥሮ ሱራፌል ጌታቸው ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አቤል አሰበ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በተከላካዩ አማኑኤል እንዳለ ተጨርፎ ወደ ግብ ቢያመራም ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ በጥሩ ንቃት መልሶታል።

እጅግ አሰልቺ ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ ፈረሰኞቹ 45+2ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ዳዊት ተፈራ ከተገኑ ተሾመ በተመቻቸለት ኳስ ተከላካዮችን አታልሎ ያደረገው ግሩም ሙከራ በግቡ የላይ አግዳሚ ተመልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መንገድ የጨዋታው ግለት እጅግ ተሻሽሎ ሲቀጥል ግሩም አጀማመር ያደረጉት ብርቱካናማዎቹ 47ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል አግኝተው ከመሃል የተሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ኳሱን ያገኘው ተመስገን ደረሰ ያደረገውን ሙከራ አማኑኤል ተርፉ አስወጥቶበታል። በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ ከማዕዘን ተጀምሮ ሱራፌል ጌታቸው ወደ ሳጥን ያሾለከውን ኳስ አቤል አሰበ ወደ ግብ ቢመታውም ባሕሩ በጥሩ ንቃት አግዶበታል።

ጨዋታው 48ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ድሬዳዋ ከተማዎች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በዚህም ተመስገን ደረሰ ከአሜ መሐመድ ተሻግሮለት ሻሂዱ ሙስጠፋ በደንብ ሳያርቀው የቀረውን ኳስ በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጎሉም ለአጥቂው በውድድር ዓመቱ 2ኛ ጎሉ ሆኖ ተመዝግቧል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ እጅግ በመነቃቃት ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተራቸውን የቀጠሉት ፈረሰኞቹ 53ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው አማኑኤል እንዳለ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ዳዊት ተፈራ ያመቻቸለትን ኳስ የአብሥራ ተስፋዬ በጥሩ ሁኔታ ኳሱን ተቆጣጥሮ ቢያመቻቸውም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።

ብርቱካናማዎቹ የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመመከት ለመቆየት ቢገደዱም 65ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ሊያስቆጥሩ የሚችሉበትን አጋጣሚ አግኝተው ተመስገን ደረሰ ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት በመምታት ያቀበለውን ኳስ በተረጋጋ ሁኔታ ያገኘው አቤል አሰበ ባልተመጠነ ሙከራ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በሚያገኙት ኳስ ሁሉ በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ጊዮርጊሶች 72ኛው ደቂቃ ላይ በበረከት ወልዴ አማካኝነት ሙከራ አድርገው በአብዱለጢፍ መሐመድ ሲመለስባቸው 76ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ሻሂዱ ሙስጠፋ ለመሻማት በሚመስል መልኩ ከግራ መስመር ያሻገረው ኳስ አቅጣጫ ቀይሮ መረቡ ላይ ሊያርፍ ሲል የግቡ አግዳሚ መልሶበታል።

የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ማጥቃታቸውን ያለ ማቋረጥ የቀጠሉት ፈረሰኞቹ 78ኛው ደቂቃ ላይ በአማኑኤል ኤርቦ 80ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በተገኑ ተሾመ አማካኝነት ያለቀላቸውን የግብ ዕድሎች አግኝተው ዒላማቸውን ባልጠበቁ ሙከራዎች አባክነዋቸዋል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከተማዎች ግባቸውን በጥንቃቄ በመጠበቅ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲያመክኑ በቢኒያም እንዳለ እና በዳግማዊ አርዓያ ሙከራ ተደርጎባቸውም ፈተናውን ተቋቁመው 1ለ0 አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ ሆነው መቅረባቸውን በመግለጽ አጨራረስ ላይ በልምምድ ቦታ ጠንክረው ቢሠሩም በጨዋታው ውጤታማ እንዳላደረጋቸው ሀሳባቸውን ሲሰጡ የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ሽመልስ አበበ በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ የመሸናነፍ ስሜት እንደነበረው እና ቀድመው እንደጠበቁት ማግኘታቸውን ጠቁመው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በደርሶ መልስ ማሸነፍ መቻል ትልቅ ዋጋ እንዳለው በመግለጽ ተመስገን ደረሰ ዛሬ ጎል ማስቆጠሩ ተጨማሪ ጥሩ ነገር እንደሚፈጥርላቸው ተናግረው በቀሪ ጨዋታዎች ዕድል ላላገኙት ተጫዋቾች ዕድል በመስጠት ደረጃቸውን አሻሽለው መጨረስ እንደሚፈልጉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።