በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ከ4-1 ሽንፈት የተመለሰው አዳማ ከተማ ሀዋሳ ከተማ ላይ አምስት ግቦችን በማዝነብ ጣፋጭ ድል አጣጥሟል።
የዕለቱ ተጋጣሚዎች ከሊጉ መቋረጥ በፊት ካደረጓቸው ጨዋታዎች አንፃር በተደረጉ ለውጦች ሀዋሳ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን ከረታበት ቀዳሚ አሰላለፍ በሰለሞን ወዴሳ እና ሲሳይ ጋቾ ምትክ ፈቃደሥላሴ ደስአለኝ እና እንየው ካሳሁንን ሲጠቀም በኢትዮጵያ መድን ከባድ ሽንፈት ያስተናገዱት አዳማ ከተማዎች ከግማሽ በላይ የአሰላለፍ ለውጥ አድርገዋል። በዚህም መሰረት ሰዒድ ሀብታሙ ፣ መላኩ ኤልያስ ፣ አህመድ ረሺድ ፣ አቤኔዘር ሲሳይ ፣ ኤልያስ ለገሰ እና ነቢል ኑሪ የዛሬውን ጨዋታ እንዲጀምሩ ሆኗል።
በሀዋሳ ከተማ ወደ ግራ ያደላ ፈጣን ጥቃት የጀመረው ጨዋታ በጊዜ በአዳማ ከተማ የጎል ምላሽ የተሰጠበት ሆኗል። 8ኛው ደቂቃ ላይ ከነቢል ኑሪ የተነሳውን ኳስ በግራ የሳጥኑ ክፍል እየገፋ የገባው ቢኒያም አይተን ከተከላካዮች አምልጦ መልሶ አሳልፎለት ነቢል አዳማን ያስቀደመች ጎል አስቆጥሯል።
ከግቡ በኋላም የሀዋሳ ከተማ ወደ ግራ ያደላ እንዲሁም በቀጥተኛ ኳስ የታጀበ የማጥቃት ጥረት ቢታይም ወደ ፈታኝ ሙከራነት መቀየር አልቻለም። ይልቁኑም ቡድኑ ከኋላ ከሚታይበት አለመረጋጋት ጋር ተደምሮ አዳማ ከተማዎች ኳስ መስርተው በመውጣት በሳጥኑ ዙሪያ አደገኛ ቅፅበቶችን ለመፍጠር ቢቃረቡም የመጨረሻ ውሳኔዎቻቸው ፅዮን መርዕድን ከመፈተን አግዷቸው ቆይቷል።
ጨዋታው 40ኛው ደቂቃ ላይ የቢኒያም እና ነቢል ጥምረት በድጋሚ ለአዳማ ልዩነት ፈጥሯል። ነቢል ቢኒያም ያሳለፈለትን ኳስ ሳጥን ውስጥ ለመቆጣጠር ሲሞክር ፂዮን መርዕድ የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ዮሴፍ ታረቀኝ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል።
በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማ በጭማሪ ደቂቃ ማይክል ኦቶሎ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ ሌላ ጠንካራ ዕድል መፍጠር አልቻለም። ይልቁኑም ለአጋማሹ መጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩ ነቢል ኑሪ በመጀመሪያው ግብ አኳኋን አሁንም ከቢኒያም አይተን የደረሰውን ነፃ ኳስ ለጥቂት የሳተበት አጋጣሚ ትኩረትን የሚስብ ነበር።
ከዕረፍት መልስ ሀዋሳ ከተማዎች ሦስት ቅያሬዎችን በማድረግ ወደ ሜዳ ተመልሰዋል። ይህንን ተከትሎም ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወደ አዳማ ሳጥን መጠጋት ችለዋል። ከእስራኤል እሸቱ እና እዮብ ዓለማየሁ የግራ መስመር ጥረቶች በኋላ ከተቀያሪዎቹ አንዱ የሆነው ያሬድ ብሩክ 62ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት ያረገው ሙከራ ለግብ የቀረበ ነበር። ከማጥቃቱ ባለፈ ሀዋሳዎች የአዳማን ተደጋጋሚ ጥቃት በተሻለ ሁኔታ ተቆጣጥረው መቆየት ችለው ነበር። ሆኖም 70ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም አይተን በፍጥነት ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ከኳስ ጋር ባረገው ሩጫ በመድሀኔ ብርሀኔ ጥፋት ተሰርቶበታል። የተሰጠውን የጨዋታውን ሁለተኛ የፍፁም ቅጣት ምትም ድንቅ ሆኖ የዋለው ራሱ ቢኒያም አይተን አስቆጥሮታል።
80ኛው ደቂቃ ላይ ዓሊ ሱለይማን በሬድዋን ሸሪፍ በተሰራበት ጥፋት የፍፁም ቅጣት ጥያቄ የነበራቸው ሀዋሳዎች የተደራጀ ባይሆንም ልዩነቱን ለማጥበብ ተንቀሳቅሰዋል። ነገር ግን በተሻለ የኳስ ቁጥጥር እና እርጋታ ውስጥ የቀጠሉት አዳማዎች በቁጥር ብልጫ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል በመድረስ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም አደገኛ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል። በጭማሪ ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸውም አራተኛውን ጎል አግኝተዋል። ቦና ዓሊ በተከላካዮች መሀል ያሳለፈለትን ኳስ ተከትሎ በቀኝ መስመር ሮጦ ሳጥን ውስጥ የደረሰው አህመድ ረሺድ ፂዮን መርዕድን በማለፍ ጭምር የአዳማን መሪነት አራት አድርሷል። አፍታም ሳይቆይ በቦና ዓሊ እና አድናን ረሻድ የተዘጋጀውን ኳስ ዮሴፍ ታረቀኝ ከመረብ አሳርፎ አዳማን የ5-0 ባለድል አድርጓል።
የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ተጫዋቾቻቸው በተለያዩ ምክንያቶች ስሜታዊ ሆነው ከእንቅስቃሴ እንደወጡ ጠቁመው ከተጨዋቾች ልምድ ማጣት እና ከመከላከል ድክመት በጨዋታው መሻሻል እንዳልቻሉ እና ችግሮቻቸውን አርመው ወደ አሸናፊነት እንደሚመለሱ ያላቸውን እምነት ገልፀው ደጋፊዎቻቸውንም ይቅርታ ጠይቀዋል። አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው ተጫዋቾቻቸው ከጅምሩ ጥሩ እንደነበሩ ገልፀው ከድሉ ባለፈ በወጣት ተጫዋቾቻቸው ላይ ባዩት አቅም መደሰታቸውን ተናግረው ከበፊት ደረጃቸው መሻሻል እና ቀጣዮቹን ወጣቶች መመልከት የቀሪ ሳምንታት ግባቸው መሆኑን ገልፀዋል።