ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከ3 ጨዋታዎች በኋላ ድል ሲያደርግ ሀምበርቾ 21ኛ ሽንፈቱን  አስተናግዷል

በምሽቱ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ከዕረፍት መልስ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ግርጌ ላይ የሚገኘውን ሀምበርቾ 2-0 ረቷል።

ሊጉ ለብሔራዊ ቡድን ከመቋረጡ በፊት በነበረው የ26ኛ ሳምንት መርሐግብር ሀምበርቾዎች በኢትዮጵያ ቡና የ6ለ1 ሽንፈት ባስተናገደበት ወቅት ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ባደረጉት የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ትዕግስቱ አበራ ፣ ምናሴ በራቱ ፣ ሙና በቀለ እና እንዳሻው ጫሚሶን በዲንክ ዲያር ፣ ታዬ ወርቁ ፣ በፍቃዱ አስረሳኸኝ እና ተስፋጽዮን ዘለቀ ተክተዋቸው ሲገቡ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ የ1ለ0 ሽንፈትን አስተናግደው በነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በኩል በተደረገ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ ጊት ጋትኩትን በአንተነህ ተስፋዬ ፣ ደግፌ ዓለሙን በደስታ ዮሐንስ ፣ አበባየው ዮሐንስን በዮሴፍ ዮሐንስ ፣ ይገዙ ቦጋለን በሀብታሙ ገዛኸኝ እና ይስሃቅ ካኖን በቡልቻ ሹራ ያደረጉት ለውጥ ሆኗል።

የዕለቱ ሁለተኛ በሆነው የሁለቱ ቡድኖች የጨዋታ መርሐግብር የመጀመሪያዎቹ ሀያ ያህል ደቂቃዎች ሜዳ ላይ ከነበሩ እንቅስቃሴዎች ውጪ ጥራት ያላቸውን ሙከራዎች ለመመልከት አስናፍቆናል። ሲዳማ ቡናዎች ሁለቱን ኮሪደሮች በደስታ እና ብርሃኑ ተጠቅመው በጥልቅ አጨዋወት ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ከጨዋታው መጀመር አንስቶ በድግግሞሽ ደርሰው ብንመለከትም ግለት አልባው ጨዋታ በጎል ለማሟሸት ተቃርበው የነበሩት ግን ሀምበርቾዎች ነበሩ።

23ኛው ደቂቃ ላይ በግምት 35 ሜትር ላይ የተሰጠውን የቅጣት ምት አማካዩ ብርሃኑ አሻሞ ወደ ግብ አክርሮ መቶት ኳሷ የግቡን አግዳሚ ለትማ ወጥታለች። ጨዋታውን በአግባቡ ይቆጣጠሩ እንጂ በቀላሉ የሀምበርቾን መረብ ለማግኘት የከበዳቸው ሲዳማ ቡናዎች በግራ በኩል ደስታ ዮሐንስ በጥልቀት ገብቶ በግቡ ቋሚ በኩል ኳሷ ዒላማዋን መጠበቅ ሳትችል ቀርታለች። አጋማሹ ሊገባደዱ በቀሩት አምስት ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች ከፍ ባለ ተነሳሽነት ጎልን ለማስቆጠር ጥረት አድርገው ቢታይም በ0ለ0 ውጤት ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ መሐል ሜዳ ላይ የፈጠራ ችግር የነበረባቸው ሲዳማ ቡናዎች ዮሴፍ ዮሐንስን በአበባየው ዮሐንስ ከተኩ በኋላ በተረጋጋ የኳስ ፍሰት በቀላሉ ጨዋታውን ወደ ራሳቸው በማድረግ በይበልጥ ኮሪደሩን በመጠቀም ጫናዎችን ሲያሳድሩ ተስተውሏል። ሁለቱም ብርሃኑዎች ለቡድኖቻቸው ከርቀት ካደረጓቸው እና በግብ ጠባቂ ከተመለሱ ሙከራዎች ውጪ በሙከራ ሳይደምቅ በነበረው ጨዋታ 65ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማዎች የአጥቂ ክፍላቸው ላይ ዕድሳት በማድረግ ይስሄቅ ካኖን ካስገቡ በኋላ ይበልጥ የሀምበርቾ የግብ ክልል ስር ሲያነፈንፉ የዋሉ ሲሆን በአንፃሩ ተመስገን አሰፋን በትዕግስቱ አበራ የለወጡት ሀምበርቾዎች 74ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስተናግደዋል።

የግብ ዘቡ ምንታምር መለሠ ለተከላካዩ ኪንክ ኪያር ለማቀበል ሲል ይስሀቅ ካኖ ፈጥኖ ኳሷን ለማግኘት ሲታትር በሳጥን ውስጥ በዲንክ መጠለፉን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አበባየሁ ዮሐንስ መረቡ ላይ አሳርፎ ሲዳማን መሪ ያደረገ ሲሆን ከአንድ ደቂቃ መልስ ደግሞ በዛብህ መለዮ በረጅሙ ወደ ጎል የላካትን ኳስ ምንታምር መቆጣጠር ተስኖት ማይክል ኪፕሩቪ ደርሳው ተጨማሪ ጎል አድርጓት ሲዳማን ወደ ሁለት ለምንም አሸጋግሯል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ጨዋታው ተጨማሪ ግብን ሳያስመለክተን 2ለ0 በሆነ ውጤት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድናቸው ጥሩ እንዳልነበር ጠቅሰው ከዕረፍት በኋላ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ልጆች ቀይረው ካስገቡ በኋላ ውጤትን ይዘው እንዲወጡ እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል። የሀምበርቾ አቻቸው ብሩክ ሲሳይ በአንፃሩ ከሞላ ጎደል ጥሩ እንደነበሩ ከገለፁ በኋላ ልምምድ አለመስራታቸው በቡድናቸው ላይ የፊትነስ ችግር እንደፈጠረ በዚህም ሽንፈት ማስተናገድ መቻላቸውን ተናግረዋል።