የ27ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሚከናወኑ ሁለት የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ መርሐግብሮች መቋጫውን ያገኛል ፤ ጨዋታዎቹን አስመልክተን ያዘጋጀንላችሁ መረጃም እንደሚከተለው ቀርቧል።
ወላይታ ድቻ ከ ሀዲያ ሆሳዕና
የጦና ንቦች በሊጉ መትረፋቸውን ቀደም ብለው ቢያረጋግጡም የተሻለ ደረጃን ይዞ የውድድር ዓመቱን ለማገባደድ ፤ ነብሮቹ ደግሞ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ የሚገፋቸውን ውጤት ፍለጋ የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሃያ ዘጠኝ ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የጦና ንቦቹ ላለፉት አራት ሳምንታት ከራቃቸው ድል ለመታረቅ ሀድያ ሆሳዕናን ይገጥማሉ።
ለሦስት ጨዋታዎች ከነጥብ ጋር ተራርቆ ከቆየ በኋላ ከጠንካራው ባህርዳር ከተማ አንድ ነጥብ መውሰድ የቻለው ቡድኑ በጨዋታው ለበርካታ ሳምንታት ዋነኛ ችግሩ ሆኖ የቆየውን የመከላከል ድክመት በውስን መልኩ አሻሽሏል። ቡድኑ ተከታታይ ሽንፈቶች ባስተናገደባቸው ሦስት መርሐግብሮች ዘጠኝ ግቦች ቢያስተናግድም በመጨረሻው ጨዋታ ግቡን ሳያስደፍር ወጥቷል።
የመጀመርያውን ዙር 8ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ያጠናቀቀው ወላይታ ድቻ በሁለተኛው ዙር እጅግ ተዳክሞ ብዙ ጠንካራ ጎኖቹ አብረውት የሉም። በጅማሮው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ቡድኑ በአጨዋወት መንገዱ ከተስተዋለው መዳከም በተጨማሪ በውጤት ረገድም አሽቆልቁሏል፤ አንደኛውን ዙር ሃያ ሁለት ነጥቦች ይዞ ያጠናቀቀው ቡድኑ በሁለተኛው ዙር የሰበሰባቸው ነጥቦች ሰባት ብቻ ናቸው። የጦና ንቦቹ ምንም እንኳ በሊጉ የመቆየታቸው ጉዳይ ቀድመው ቢያረጋግጡም የተሻለ ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ በፊት መስመራቸው የሚታየውን የአፈፃፀም ክፍተት ከማረም በተጨማሪ በመጨረሻው መርሐግብር ተሻሽሎ የቀረበው የመከላከል አደረጃጀታቸውን ጥንካሬ ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል።
በሰላሣ አምስት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ነብሮቹ ከተከታታይ ድል አልባ ጨዋታዎችን በኋላ የደረጃ መሻሻል የሚያስገኝላቸውን ነጥብ ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ሀዲያ ሆሳዕና በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ አልቻለም። ለአስራ ስምንት ጨዋታዎች ሳይሸነፍ ከዘለቀ በኋላ በቅርብ ሳምንታት ሦስት ሽንፈቶች ያስተናገደው ቡድኑ በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ የተቀመጠው ሀዋሳ ከተማ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ወደ ሰንጠረዡ አካፋይ ቦታ መሻገርን እያለመ ወደ ነገው ጨዋታ ይቀርባል።
ጠንካራው የሀዲያ ሆሳዕና የመከላከል አደረጃጀት ባለፉት ጨዋታዎች ውስን መንገራገጮች ቢገጥሙትም ከወላይታ ድቻ የማጥቃት አቅም አንፃር በኋላ ክፍላቸው ብርቱ ፈተና ላይገጥማቸው ቢችልም ሰሞኑን በተደጋጋሚ የታየው ዕድሎችን የመጨረስ ችግር ማሻሻል ለአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ቀዳሚው የቤት ሥራ ይመስላል። ፈጣኖቹን አጥቂዎች ያማከለ ሽግግር የሚያደርጉት ነብሮቹ በተቃራኒው የተከላካይ መስመሩን ወደ ፊት ገፍቶ ለመከላከል በሚሞክርበት ጊዜ ተጋላጭ እየሆነ ላለው ቡድን ጫናዎች ሊያበዙ ይችላል። በተለይም በተናጠል ጫናዎችን ማሳደር የሚችሉት የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸው በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ መሆናቸው አይቀሬ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ በዘጠኝ አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና 4 ወላይታ ድቻ ደግሞ 3 ጨዋታዎች ላይ ሲያሸንፉ የተቀሩ ሁለት መርሐግብሮች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።
በሀድያ ሆሳዕናዎች በኩል የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና የለም።
ሻሸመኔ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን
ከደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ በአንድ ደረጃ ከፍ ብለው የሚገኙት ሻሸመኔ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን የወሳኝነት ደረጃው እጅግ የተለያየ ቢሆንም በየመንገዳቸው የነገው ሦስት ነጥብ ይፈልጉታል፤ ሻሸመኔ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው ለመላቀቅ መድን ደግሞ የአሸናፊነት መንገዱን ከማስቀጠል ባለፈ ከአስራ ሰባት ሳምንታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሰንጠረዡ መሃል ሰፋሪዎች ጎራ ለመቀላቀል ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ።
በአስራ አራት ነጥቦች በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኘው ሻሸመኔ ከተማ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በአወንታ የሚነሳለት መሻሻል ቢያሳይም ከመርሐግብሮቹ ከ1 ነጥብ በላይ መሸመት አልቻለም። በሁለት ነጥቦች ብቻ የሚበልጠው ወልቂጤ ከተማ ቀድሞ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ለመትረፍ በሚያደርገው ትንቅንቅ ውስጥ ትልቅ ፋይዳ የሚኖረውን ነጥብ ፍለጋ ኢትዮጵያ መድንን የሚገጥመው ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ያመለጠውን ወርቃማ ዕድል ዳግም ላለማጣት ወደ ሜዳ ይገባል።
ከአራት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ከዋንጫ ተፎካካሪው መቻል አንድ ነጥብ መውሰድ የቻሉት ሻሸመኔ ከተማዎች ጥሩ እንቅስቃሴያቸውን ወደ ውጤት መመንዘር አልቻሉም። ቡድኑ ምንም እንኳ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ባይችልም በወሳኙ ጨዋታ ያሳየው እንቅስቃሴ፤ ከተጋጣሚው ጥንካሬ አንፃር ያሳካው አንድ ነጥብ በአወንታ ይጠቀሱለታል። የመጨረሻው ጨዋታ ከወልቂጤ ከተማ ጋር የነበራቸውን የነጥብ ልዩነት ከማጥበቡ ባለፈ ቡድኑ በተከታታይ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ቆይቶ ያለ ውጤት የሚወጣበትን መንገድ የቀየረ መሆኑ ሲታሰብ የሚሰጠው ዋጋ ትልቅ ሊሆን ይችላል።
ሻሸመኔ ከተማዎች በነገው ዕለት የደረጃ ልዩነቱ ሰፊ ቢሆንም ከባለፈው ሳምንት ተጋጣሚያቸው የማይተናነስ ወቅታዊ ጥንካሬ ያለውን ኢትዮጵያ መድንን በሚገጥሙበት ጨዋታ እጅግ ስኬታማ የነበረውን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው ከማስቀጠል ባለፈ በጨዋታዎች ዋጋ እንዲከፍሉ ያስቻላቸውን የአፈፃፀም ክፍተት መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ የሚያገኛቸውን ዕድሎች ወደ ግብነት እየቀየረ መዝለቅ እንደሚገባው የመጨረሻዎቹ መርሐግብሮች ትምህርት እንደሚሆኑት አያጠያይቅም። ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ጠንካራውን የመድን የፊት መስመር ጥምረት ለመግታት በሚያስችል ጥንካሬ ላይ መገኘት ግድ ይለዋል።
በሁለተኛው ዙር እጅግ ተሻሽለው ከቀረቡ ቡድኖች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት መድኖች ተከታታይ ሰባተኛ ድላቸውን ለማስመዝገብ ከወራጅ ቀጠናው ለመላቀቅ በመታተር ላይ የሚገኘውን ሻሸመኔ ከተማ ይገጥማሉ።
ከሁለተኛው ዙር ጅማሮ አንስቶ በመድን በኩል ነገሮች ጥሩ እየሄዱ ነው። ቡድኑ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ጉልህ ለውጥ ባሳየባቸው ያለፉትን ስድስት ሳምንታት አስራ ሰባት ግቦች ሲያስቆጥር ያስተናገዳቸው ግቦች ሁለት ብቻ ናቸው። ቡድኑ ጨዋታዎች ካሸነፈበት መንገድ በተጨማሪ ከላይ የተጠቀሱት ሁለት መመዘኛዎች ጉልህ ዕድገት እንዳስመዘገበ የሚያመላክት ነው። ጨዋታው ከኢትዮጵያ መድን ይልቅ በሊጉ ለመክረም ከፍተኛ ትግል የሚጠበቅበትን ሻሸመኔ ከተማ ያለው ትርጉም የላቀ ቢሆንም መድኖችም ከዚህ ጨዋታ የሚያገኙት ሙሉ ነጥብ የደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል።
መድኖች የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ በግሩም የአፈፃፀም ብቃት በታጀበባቸው ያለፉት ጨዋታዎች የተጠቀሙበት የተለመደው የቀጥተኛ እና የፈጣን ሽግግር ነገም እንደሚተገብሩ ይታመናል። የነገው ተጋጣሚያቸውም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስተናገደ እና ለመሰል ጥቃቶች ተጋላጭ እየሆነ እንደመምጣቱ ከባድ ፈተና ላይገጥማቸው ይችላል፤ ሆኖም ተጋጣሚያቸው ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ የመጣ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ከመርሐግብሩ ወሳኝነት አንፃር ለመልሶ ማጥቃቶች ራሱን አዘጋጅቶ ሊገባ የሚችልበት ዕድልም ጠባብ አይደለም። ስለዚህ ባለፉት ጨዋታዎች ውጤታማ እና ስል የነበረው የፊት ጥምረታቸው ውጤታማነት ከማስቀጠል በዘለለ ተጨማሪ የማጥቂያ መንገዶችን ማበጀት ይጠበቅባቸዋል።
በሻሸመኔ ከተማ በኩል ገዛኸኝ ደሳለኝ በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም ከዚህ በተጨማሪ አብዱልቃድር ናስር ለጨዋታው መድረሱ አጠራጣሪ ነው። በኢትዮጵያ መድን በኩል ግን የቅጣትም ሆነ የጉዳት ዜና የለም።
ዘንድሮ ከ16 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኞች በሊጉ 4 ጨዋታ ላይ የተገናኙ ሲሆን ሁለቱም አንድ አንድ ጨዋታዎች በእኩሌታ ሲያሸንፉ በ2 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል፤ በግንኙነቱ ከተመዘገቡ 6 ግቦችም ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ 3 ግቦች አስቆጥረዋል።