ሻሸመኔ ከተማዎች ሊያሻሽሉት ባልቻሉት አባካኝነታቸው መቀጣታቸውን ቀጥለው ዛሬም በፋሲል ከነማ 2ለ1 ተሸንፈዋል።
በ28ኛ ሳምንት የመጀመሪያ መርሐግብር ሻሸመኔዎች በኢትዮጵያ መድን 2ለ0 ከተሸነፉበት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ አቤል ማሞ ፣ ምንተስኖት ከበደ ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ እና አብዱልቃድር ናስር ወጥተው ኬን ሳይዲ ፣ ገዛኸኝ ደሳለኝ ፣ ሄኖክ ድልቢ እና አሸናፊ ጥሩነህ ሲገቡ በዐፄዎቹ በኩል በተደረጉ ሁለት ለውጦች አቤል እያዩ እና ቃልኪዳን ዘላለም ወጥተው ጋቶች ፓኖም እና ናትናኤል ማስረሻ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተካተዋል።
9 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በማጥቃት እንቅስቃሴው ከፍተኛ ብልጫ የነበራቸው ሻሸመኔ ከተማዎች ገና በሴኮንዶች ውስጥ ነበር ወጋየሁ ቡርቃ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደ ውስጥ ቀንሶት ግብ ጠባቂው ሳማኬ በያዘበት ኳስ የተጋጣሚያቸውን ሳጥን መፈተን የጀመሩት።
እንደከዚህ ቀደም ጨዋታዎች ሁሉ በአባካኝነታቸው ጎልተው የታዩት ሻሸመኔዎች 11ኛው ደቂቃ ላይ መሪ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ አግኝተው ኢዮብ ገብረማርያም ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አሸናፊ ጥሩነህ በግንባሩ ከገጨው በኋላ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ሁዛፍ ዓሊ በደካማ ሙከራ አባክኖታል።
በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር በማድረግ አጥቅተው መጫወታቸውን የቀጠሉት ሻሸመኔዎች 24ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ያለቀለት የግብ ዕድል ፈጥረው ወጋየሁ ቡርቃ ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ተከላካዩ ሀቢብ መሐመድ አቅጣጫ ካስቀየረው በኋላ ኢዮብ ገብረማርያም ወደ ውስጥ ቀንሶት ኳሱን ያገኘው ሁዛፍ ዓሊ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳሜኬ አግዶበታል።
ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመጠጋት እጅግ የተቸገሩት ፋሲል ከነማዎች ይባስ ብሎም 27ኛው ደቂቃ ላይ በሠሩት ስህተት ሊቀጡ ነበር። ሀቢብ መሐመድ ወደኋላ የመለሰውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ እጅግ ደካማ በሆነ የመጀመሪያ ንክኪ ለሁዛፍ ዓሊ ሰጥቶት አጥቂው የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
የመጨረሻ ኳሳቸው ደካማ ይሁን እንጂ ጠንካራ የሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የቀጠሉት ሻሸመኔ ከተማዎች 30ኛው ደቂቃ ላይም ከቆመ ኳስ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ገዛኸኝ ደሳለኝ ከቅጣት ምት ያደረገው ግሩም ሙከራ በግቡ የላይ አግዳሚ ሲመለስበት ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ “ሁዛፍ ዓሊ ኳስ እየገፋ ወደ ሳጥን ሲገባ ተከላካዩ ሀቢብ መሐመድ ጥፋት ሠርቷል ፤ የመጨረሻ ሰው ስለሆነ ቀይ ካርድ ይገባው ነበር” ብለው ያመኑት እና የቅጣት ምትም ያላገኙት ሻሸመኔዎች ከፍተኛ ቅሬታ አሰምተዋል።
ቢጫ ካርድ የነበረው ሀቢብ መሐመድም ከሚሠራቸው ተደጋጋሚ ጥፋቶች አንጻር የቀይ ካርድ እንዳይመለከት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ 37ኛው ደቂቃ ላይ በምኞት ደበበ ተክተውታል። ሆኖም ዐፄዎቹ በመጀመሪያ አጋማሽ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ መሃል ሜዳው ላይ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ ጥረቶች ውጪ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ሲሄድ ፋሲል ከነማዎች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ወደ ተሻለ እንቅስቃሴ መምጣት ችለዋል።
ጨዋታው 76ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ዐፄዎቹ ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ዓለምብርሃን ይግዛው ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ጌታነህ ከበደ በግንባር ሊገጨው ሲል ወጋየሁ ቡርቃ ከኋላ ባልተመጣጠነ ኃይል ገፍቶት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ፍቃዱ ዓለሙ ተቀይሮ በገባበት ቅጽበት በግሩም የራስ መተማመን ኳሱን መረብ ላይ አሳርፎታል።
ድራማዊ ክስተት በታየባቸው የመጨረሻ ተጨማሪ 9 ደቂቃዎች ሁለት ግቦች ተቆጥረዋል። በቅድሚያም 90+2ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ከነማዎች በድንቅ የቡድን ቅንጅት ጎል አስቆጥረዋል። ሚኬል ሳማኬ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከጌታነህ ከበደ ጋር ተቀባብሎ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ሲቀንሰው ያገኘው ፍቃዱ ዓለሙ በቀላሉ ግብ አድርጎታል።
ሻሸመኔዎች በርካታ ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን እንዲያባክኑ ግንባር ቀደም ተወቃሽ የነበረው ሁዛፍ ዓሊ 90+3ኛው ደቂቃ ላይ ለባዶ ከመሸነፍ ያዳነቻቸውን ጎል ማስቆጠር ቢችልም 90+11ኛው ደቂቃ ላይ አሸብር ውሮ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ስንታየሁ መንግሥቱ በግንባር ገጭቶት ለጥቂት በግቡ የቀኝ ቋሚ ወጥቶበት ጨዋታው በፋሲል ከነማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሻሸመኔ ከተማው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ሀቢብ መሐመድ በሠራው ጥፋት በቀይ ካርድ አለመውጣቱ የጨዋታውን ውጤት እንደቀየረባቸው እና ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩን አዲሱ የዳኞች ኮሚቴ ከዚህ በኋላ ለሦስት ዓመታት ጨዋታ ይሰጡታል ብለው እንደማያምኑ እንዲሁም ዳኛው ዕድሎችን እንደነጠቃቸው ሲናገሩ ላለመውረድ የሚጫወቱ ቡድኖች ውጤት ላይ ጥገኛ ከመሆን ይልቅ የራሳቸው ውጤት ላይ እንደሚያተኩሩ ሀሳባቸውን ሲሰጡ የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው ሁለቱ አጋማሾች የተለያዩ እንደነበሩ እና በመጀመሪያው አጋማሽ የሻሸመኔን የማጥቃት እንቅስቃሴ መግታታቸው በሁለተኛው አጋማሽ ተጠናክረው እንዲቀርቡ ምክንያት እንደሆነላቸው ገልጸው ተጫዋቾቻቸው ለእሳቸው በማያሳምን ምክንያት በአዕምሮ ነጻ ሆነው እንዳልተጫወቱ ጠቁመው ዳኝነቱ ላይ ውጤት ቀያሪ ስህተት እንዳልተመለከቱ እና ጌታነሀ ከበደ በራሱ ፍቃድ የፍጹም ቅጣት ምቱን ለፍቃዱ ዓለሙ አሳልፎ እንደሰጠው ተናግረዋል።