መረጃዎች | 112ኛ የጨዋታ ቀን

በ27ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚከናወኑ ሁለት መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

አዳማ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

በሁለት ነጥብ የሚበላለጡ እና በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኙ ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ተጠባቂ መርሐግብር ነው።

በኢትዮጵያ መድን የደረሰባቸውን የአራት ለአንድ ሽንፈት ሀዋሳ ከተማን አምስት ለባዶ በማሸነፍ ያካካሱት አዳማ ከተማዎች ነጥባቸውን አርባ አራት በማድረስ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

አዳማዎች የተለያየ መልክ ያላቸው ሁለት ሳምንታት ነው ያሳለፉት፤ በሰፊ የግብ ልዩነት ካሸነፉበት አስደናቂው ሰሞነኛ ብቃታቸው በኋላም ደረጃቸውን ለማሻሻል በሁለት ነጥብ ከፍ ብሎ ከተቀመጠው ባህር ዳር ከተማ ብርቱ ፈተና ይጠብቃቸዋል። ካላቸው የስብስብ ጥራት፣ ጥልቀት እና ልምድ አንጻር ሲታይ ውጤታማ የውድድር ዓመት ያሳለፉት አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ዓመቱን በተሻለ ደረጃ ለማገባደድ በቀጣይ ከባህር ዳር ከተማ እና ድሉን በአንገብጋቢ ሁኔታ ከሚሻው መቻል ጋር ይጫወታሉ፤ ይህንን ለማሳካት ደግሞ ከቅርብ ተፎካካሪያቸው በሚያደርጉት መርሐግብር ትልቁን እርምጃ ወደ ፊት መራመድ ይገባቸዋል።


በጨዋታውም በተከታታይ ሳምንታት ከታየባቸው ውስን መቀዛቀዝ በኋላ በመጨረሻው መርሐግብር አምስት ግቦች ያስቆጠሩት የፊት መስመር ተሰላፊዎች ከጠንካራው የባህር ዳር ከተማ የመከላከል አደረጃጀት የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል።

በመጨረሻው ሳምንት ከመሪው ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ ተጋርተው በመውጣት ለሳምንታት የቆዩበትን ደረጃ ለኢትዮጵያ ቡና አሳልፈው የሰጡት ባህርዳር ከተማዎች ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ አዳማ ከተማን ይገጥማሉ።

ጠጣርና በቀላሉ መረቡን የማያስደፍር የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን የገነቡት የጣና ሞገዶቹ ላለፉት አስራ ሦስት ጨዋታዎች ሽንፈት አልቀመሱም፤ ቡድኑ ካለፉት አስራ ሦስት ጨዋታዎች ከሽንፈት ከመራቁ በተጨማሪ በዘጠኙ መረቡን ሳያደፍር በመውጣት ጥሩ የመከላከል ቁጥሮች ቢያስመዘግብም ተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶች በጉዞው ላይ እክል ሆነውበታል። ባሳለፍነው ሳምንት የሊጉን መሪ ነጥብ ያስጣለው የአሠልጣኝ ደግአረግ ስብስብ ከነገ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ለመገናኘት ይጠቅመዋል፤ ከዚ በተጨማሪም
እስከ ሦስተኛ ደረጃ የመጨረስ ዕድላቸውን ለመጠቀም ድሉ አስፈላጊያቸው ነው።

አዳማ ከተማዎች የቻርለስ ሪባኑን ግልጋሎት አያገኙም፤ የተቀሩት ተጫዋቾች ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በባህር ዳር ከተማ በኩልም ሙሉ ስብስቡ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 9 ጊዜ ተገናኝተው ባህር ዳር ከተማ 6 በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው አዳማ 2 አሸንፎ አንዱን አቻ ተለያይተዋል። ባህር ዳር 10 ሲያስቆጥር አዳማ 3 አስቆጥሯል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

ብርቱካናማዎቹን ከ ነብሮቹ የሚያገናኘው ጨዋታ ምሽት ላይ ይደረጋል።

ሁለት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ነጥባቸውን አርባ በማድረስ 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ድሎች ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ብርቱካናማዎቹ በመድን የደረሰባቸውን አስከፊ ሽንፈት ጨምሮ ሦስት ድል አልባ ጨዋታዎች ካሳለፉ በኋላ በተከታታይ ሁለት መርሐግብሮች ሙሉ ሦስት ነጥብ ሰብስበው በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛሉ። በተለይም አምስት ግቦች ካስተናገደ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረው የቡድኑ የኋላ ክፍል የቀደመ ጥንካሬውን መልሶ አግኝቷል።

በነገው ዕለት ግን ተጋጣሚያቸው ከውጤት ፈላጊነት አንፃር ከፍ ባለ የማጥቃት አጨዋወት ሊቀርብ የሚችልበት ዕድል ስላለ ለቀጥተኛ እና ለመልሶ ማጥቃቶች በሚችለው መጠን መዘጋጀት ይኖርበታል።


በሊጉ ጅማሮ ከገጠማቸው ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ረዘም ላለ ጊዜ ተከታታይ ሽንፈት ሳይቀምሱ የቆዩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ተከታታይ ሽንፈቶች አስተናግደዋል። ነብሮቹ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከድል ጋር ከመራራቅ ባለፈ ከዚህ ቀደም የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸውን ጥንካሬ ማስቀጠል አልቻሉም። ለረዥም ጊዜ የሊጉን ዝቅተኛ ጎል ያስተናገደ ክለብ ሆኖ የዘለቀው ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ብቻ አራት ግቦች አስተናግዷል፤ ይህንን ተከትሎም ቦታውን ሃያ አንድ ግቦች ባስተናገደው ባህር ዳር ከተማ ተነጥቋል።

ቡድኑ በወላይታ ድቻው ጨዋታ ላይ ቀድሞ መምራት ቢጀምርም ውጤቱን ማስጠበቅ ሳይችል ቀርቶ ሽንፈት አስተናግዷል፤ ተከታታይ ነጥብ በጣለባቸው ጨዋታዎች ላይ በበቂ ደረጃ የግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻለው ቡድኑ ይህን ክፍተት ነገ ቀርፎ ካልመጣ ከሁለቱ ተጋጣሚዎች የተሻለ የመከላከል አደረጃጀት ያለውን፤ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን የማይፈቅደው እና በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሐግብሮች መረቡን ያላስደፈረው ድሬዳዋ ከተማን ስለሚገጥም ሊቸገር ይችላሉ።

ቡድኖቹ በሊጉ 9 ጊዜ ተገናኝተው ድሬዳዋ 4 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን 2 ጨዋታ አቻ ተለያይተው 3 ጨዋታ ሆሳዕና አሸንፏል። 24 ግቦች በተስተናገዱበት ግንኙነት ሁለቱም ቡድኖች እኩል 12 ጎሎች አስቆጥረዋል።