ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ከሁለት ጊዜ መመራት ተነስተው ድል ተቀዳጅተዋል

ማራኪ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማዎች ከሁለት ጊዜ መመራት ተነስተው አዳማ ከተማን 3ለ2 አሸንፈዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ አዳማዎች በ27ኛው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን 5ለ0 ካሸነፉበት አሰላለፍ መላኩ ኤልያስ እና ዮሴፍ ታረቀኝን አስወጥተው ጀሚል ያዕቆብ እና ቦና ዓሊን ሲያስገቡ ከንግድ ባንክ ጋር 2ለ2 ተለያይተው የመጡት የጣና ሞገዶቹ በአንጻሩ ፔፔ ሰይዶ ፣ ጸጋዬ አበራ እና ሐብታሙ ታደሰን አስወጥተው አላዛር ማርቆስ ፣ ቸርነት ጉግሳ እና ወንድወሰን በለጠን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አስገብተዋል።

9 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ ፊሽካ የተጀመረው ጨዋታ ጎል ያስመለከተን ገና በ3ኛው ደቂቃ ነበር። አቤኔዘር ሲሣይ ከሳጥኑ የግራ ክፍል በጥሩ ዕይታ ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው ኤልያስ ለገሠ በውጪ እግሩ በመምታት ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎ አዳማ ከተማን መሪ ማድረግ ሲችል 7ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ የግብ ዕድል ፈጥረው ኤልያስ ለገሠ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ነቢል ኑሪ በግንባሩ ሳያገኘው ቀርቷል።

የጣና ሞገዶቹ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ መጫወት ሲችሉ 10ኛው ደቂቃ ላይም ግብ አስቆጥረዋል። ቸርነት ጉግሳ በግራ መስመር ከራሱ የግብ ክልል ጀምሮ እየገፋ የወሰደውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያቀብለው ኳሱን ያገኘው የአብሥራ ተስፋዬ በአንድ ንክኪ ከሳጥን ውጪ በአስደናቂ ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ይደረግ እንጂ ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመግባቱ በኩል ብልጫ የነበራቸው ባህር ዳር ከተማዎች 24ኛው ደቂቃ ላይ በጉዳት ምክንያት በጸጋዬ አበራ ተቀይሮ ለመውጣት የተገደደው ፍጹም ጥላሁን 13ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ከያዘበት ኳስ ውጪ ግን ንጹህ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በሚያገኟቸው ኳሶች በጥቂት ንክኪዎች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ጥረት ያደረጉት አዳማዎች 36ኛው ደቂቃ ላይ ቦና ዓሊ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ሙከራ ውጪ ተጨማሪ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ሳይችሉ ቀርተው በአቻ ውጤት ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ አዳማዎች ነቢል ኑሪ እና አቤኔዘር ሲሣይን አስወጥተው ዮሴፍ ታረቀኝ እና አድናን ረሻድን ሲያስገቡ ጨዋታው ግን እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የጋለ እንቅስቃሴ አልነበረውም። በአንጻሩ የጣና ሞገዶቹ በቁጥር እየበዙ ተጭነው መጫወታቸውን ቢቀጥሉም የመጨረሻ ኳሳቸው ፈታኝ አልነበረም።

64ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ አዳማዎች በድጋሚ መምራት ጀምረዋል። የባህር ዳሩ ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ በትክክል ያላራቀውን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ዐይተን ለኤልያስ ለገሠ አቃብሎት ኤልያስም በድንቅ ዕይታ የሰነጠቀውን ኳስ ያገኘው ዮሴፍ ታረቀኝ ኳሱን በግብ ጠባቂው እግሮች መሃል በማሳለፍ ግብ አድርጎታል።

ባህር ዳሮች ለሁለተኛ ጊዜ መመራት ከጀመሩ በኋላ ወደ አቻነት ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ባልተረጋጋ እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተደራጅተው ለመድረስ ሲቸገሩ አዳማዎች በአንጻሩ 72ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር።

አድናን ረሻድ ከጀሚል ያዕቆብ የተቀበለውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ኳሱን ያገኘው ተቀይሮ የገባው ዊልያም ሰለሞን ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ አግዶበታል።

ፉክክሩ እየተጋጋለ በሄደበት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማዎች አምሳሉ ሳሌን እና ይኸነው የማታን በጸጋዬ አበራ እና መሳይ አገኘሁ ቀይረው በማስገባት አጥቅተው መጫወት ሲችሉ 85ኛው ደቂቃ ላይም ተሳክቶላቸዋል። አምሳሉ ሳሌ ያመቻቸለትን ኳስ የአብሥራ ተስፋዬ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደ ውስጥ ቀንሶት ይኸነው የማታ በግንባር ሲጨርፈው ወንድወሰን በለጠ አግኝቶት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ትኩረት ሳቢ በነበሩት ተጨማሪ 6 ደቂቃዎች ውስጥ 90+1ኛው ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ ከሁለት ጊዜ መመራት ተነስተው ወደ መምራት የመጡበትን ጎል አግኝተዋል። አምሳሉ ሳሌ ያቀበለውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ወደ ግብ ሲመታው ኳሱን ለማውጣት ጥረት ያደረገው ፍቅሩ ዓለማየሁ ኳሱን የራሱ መረብ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በባህር ዳር ከተማ 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በትኩረት ማጣት ምክንያት በመጨረሻ ደቂቃዎች ሁለት ጎሎችን ማስተናገዳቸውን ገልጸው ዕድል ላላገኙ ተጫዋቾች ለማዳረስ ሳይሆን ቦታው ስለሚገባቸው ዕድል እንሰጣለን ሲሉ መሃል ሜዳው ላይ ብልጫ እንደተወሰደባቸው ሆኖም ግን የተሸነፉት ሰፊ ብልጫ ስለተወሰደባቸው እንዳልሆነ ጠቁመዋል። የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በበኩላቸው እንደ ቡድን መጫወታቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ተናግረው የታዳጊ ተጫዋቾቻቸውን በጫና ውስጥ ውጤታማ መሆን አድንቀዋል።