አራት ጎል የተስተናገደበት የምሽቱ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና ከተከታታይ ሁለት ጨዋታ ሽንፈት መልስ ወደ ድል ሲመልስ ድሬደዋ ከተማን ተሸናፊ አድርጓል።
ድሬደዋ ከተማ ፈረሰኞቹን ድል ካደረገው ስብስባቸው መሀከል ግብጠባቂ አብይ ካሳዬ፣ ኢስማኤል አብዱል ጋኒዬ፣ አቤል አሰበ እና ሱራፌል ጌታቸውን በማስቀመጥ ግብጠባቂ ዳንኤል ተሾመ፣ ቴዎድሮስ ሀሙ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና ቻርልስ ሙሴንጌን በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል። ሀድያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው በወላይታ ድቻ ከደረሰባቸው ሽንፈት ግብጠባቂ ታፔ አልዛየር፣ ሄኖክ አርፊጮ፣ ዳግም ንጉሴ፣ አስጨናቂ ፀጋዬ እና ዳዋ ሆጤሳ አሳርፈው ግብጠባቂ ያሬድ በቀለ፣ ቃለአብ ውብሸት፣ ካሌብ በየነ፣ ግርማ በቀለ እና ደስታ ሚሻሞ በቋሚ አስተላለፍ ተጠቅመዋል።
የምሽቱን ጨዋታ ፌደራል ዳኛ ሶሬሳ ከማል እንዳስጀመሩት ገና በመጀመርያው አንድ ደቂቃ ነበር የነብሮቹን ፈጣን ጎል ያስመለከተን። ቴዎድሮስ ታፈሰ ከሜዳው ግራ ክፍል የተሰጠውን ቅጣት ምት በተመጠነ መንገድ ያሻገረውን አንበሉ ግርማ በቀለ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።
በግርማ በቀለ ፈጣን ጎል የተነቃቁት ሀድያዎች በ12ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል ፈጥረው ነበር። ኢያሱ ለገሰ በተገቢው ሁኔታ ማራቅ ያልቻለውን ኳስ ደስታ ሚሻሞ ግኝቶ ግብጠባቂውን ዳንኤል ተሾመን በማለፍ በጥሩ ዕርጋታ ነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው ቴዎድሮስ ታፈሰ አቀብሎት በቀጥታ ወደ ጎል የመታውን የድሬደዋ ተከላካይ ቴዎድሮስ ሀሙ ጎል እንዳይሆን አድርጎበታል።
የሚያደርጓቸው ቅብብሎቻቸው ስኬት ያልነበሩት ድሬደዋዎች አብዛኛው እንቅስቃሴያቸው በመሀለኛው ሜዳ ላይ ያመዘነ ሆኖ ግብ ጠባቂውንም ሆነ ተከላካዮቹን የሚፈትኑ ተከታታይ ሙከራዎችን ለማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። የግብ ዕድል ለመፍጠር የሚረዱ የተሻሉ የሚባሉ ኳሶችን አልፎ አልፎ ሲጥሉ የነበሩት ነብሮቹ ከዚህ እንቅስቃሴያቸው በመውጣት ወደ ኋላ አፈግፍገው ለመጫወት ቢመርጡም አደገኛው ቀጠና በመድረስ ጫና ለመቀነስ ይሞክሩ ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አንስቶ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረግ የጀመሩት ቡርትካናማዎቹ ከወትሮ ባነሰ ሁኔታ ለአጥቂዎቻቸው የተሻሉ ጥራት ያላቸው ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበሉ ረገድ የነበራቸው ድክመት እንዳለ ቢሆንም በተደጋጋሚ ወደ ፊት ይደርሱ ነበር። በዚህ መልኩ በ54ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን ቅጣት ምት ካርሎስ ዳምጠው በጠንካራ ምት የመታውን ግብጠባቂው ያሬድ በቀለ እንደምንም አድኖበታል።
በአንፃሩ ነብሮቹ በተወሰነ መልኩ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት ከሚገኙ ዕድሎችም ወደ ጎል የቀረቡባቸው ጊዜዎች ነበሩ። በዚህ ሂደት ነበር በ64ኛው ደቂቃ የተሰጠውን ቅጣት ምት ቴዎድሮስ ታፈሰ ያሻማውን በተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ ካሌብ ወደ ጎል ሲመታው ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ የመለሰውን ከኳሱ በቅርብ ርቀት የነበረው ቃለአብ ውብሸት ተረጋግቶ ወደ ጎልነት በመቀየር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።
የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ወደ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግባት አስበው ጥረት እያደረጉ ባለበት ጊዜ ሁለተኛ ጎል በማስተናገዳቸው የወረዱት ቡርትካናማዎቹ በተለይ የተከላካዮቻቸው ያልተደራጀ የመከላላከል ስራ ዋጋ አስከፍሏቸው ተጨማሪ ሦስተኛ ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል። 89ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሰመረ ሀፍታይ በተከላካዮች ስህተት የተገኘውን ኳስ በጥሩ መንገድ በመጠቀም የቡድኑን ሦስተኛ ጎል አስገኝቷል።
ጨዋታው የሚፈልገውን እንቅስቃቃቄ በሙሉ ትኩረት ዘጠና ደቂቃውን መዝለቅ የቻሉት ሀድያዎች የጨዋታው መጠናቀቀ የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ጊዜ የነብሮቹ ግብጠባቂ ያሬድ ስህተት ተክሎበት አድናን መኪ ካልተጠበቀ አቅጣጫ ለቡድኑ የማስተዛዘኛ ጊል አስቆጥሮ ጨዋታው በሀድያ ሆሳዕና 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሽንፈት ያስተናገዱት አሰልጣኝ ኮማደር ሽመለስ በአስተያየታቸው በመጀመርያው ደቂቃ የተቆጠረባቸው ጎል እና የሀድያ የኃይል አጨዋወት ተደምሮ ከፈለጉት እንቅስቃቃቄ እንዲወጡ እንዳደረጋቸው አንስተው በቀጣይ ከስህተታቸው ታርመው ወደ ድል ለመመለስ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ድል የቀናቸው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው ጨዋታውን ከመጀመርያው ደቂቃ ጀምሮ በሚፈልጉት መንገድ መሄዱ በጣም ደስተኛ እንዳደረጋቸው ገልፀው እንደ ቡድን በህብረት መጫወታቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው እና ሦስተኛ የሜዳ ክፍላይ የነበራቸው የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲሁም የተጫዋቾቹ የነበራቸው ተነሳሽነት ለድሉ አስተዋፆኦ ማድረጉን ተናግረዋል።