ሪፖርት | የመቻሎች ድል የሊጉን የዋንጫ ፉክክር ከሳምንት ሳምንት አጓጊ አድርጎታል

ምሽት ላይ የተካሄደው እና የዋንጫ ፉክክሩን የሚወስነው ጨዋታ መቻልን ባለ ድል አድርጎ መቻል የመሪውን ኮቴ እግር በእግር መከተሉን አጠናክሮ ቀጥሎበታል።

ባለሜዳዎቹ ሲዳማ ቡናዎች ከድል መልስ ቡልቻ ሹራ፣ በዛብህ መለዮ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ዮሴፍ ዮሐንስን በማስቀመጥ ደግፌ አለሙ፣ አበባየሁ ዮሐንስ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን እና ይስሐቅ ካኖን ይዘው ሲገቡ በአነንፃሩ መቻሎች በተመሳሳይ ድል ካደረጉበት ስብስብ መካከል ግርማ ዲሳሳን በግሩም ሀጎስ ብቻ በመቀየር ገብተዋል።


ምሽቱ ላይ ኢንተርናሽናል አልቢትር ኃይለኢየሱስ ባዘዘው የመሩትን ይህን ተጠባቂ ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎች ድባብ እና በማርሽ ባንድ በታጀበ ድጋፍ ሞቅ ብሎ አስጀምረውታል። በ7ኛው ደቂቃ በግሩም ሀጎስ ከሳጥን ውጭ የተመታ ጠንካራ ምት ግብ ጠባቂው መክብብ ባዳነው ኳስ በአንፃሩ በሲዳማ ቡናዎች በኩል በ14ኛው ደቂቃ ይስሃቅ ካኖ በሜዳው የቀኝ ክፍል ፍጥነቱን ተጠቅሞ ተጫዋቾችን በመቀነስ ሳጥን ውስጥ ገብቶ በጥሩ መንገድ ማይክል ኪፕሩቪ አቀብሎት ሳይጠቀምበት የቀረው በጨዋታው 30 ደቂቃዎች ውስጥ የተመለከትናቸው ጥቂት ሙከራዎች ናቸው።

በሁለቱም ቡድኖቹ መካከል በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግር ጥሩ የመሸናነፍ ፍላጎት ቢኖርም ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል የሚገቡ ኳሶች ጥራት ይጎላቸው የነበሩ በመሆናቸው ጥራት ያለቸው የግብ ዕድሎችን መመልከት አልቻልንም። ሆኖም 41ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን እንቅስቃሴ የቀየረ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔ ኢንተርናሽናል አልቢትር ኃይለኢየሱስ ባዘዘው ሰጥተዋል። ሽመልስ በቀለ ላይ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን የሠራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ በሁለቱም በኩል ያለ ተጫዋቾች ለውጥ ሲቀጥል መቻሎች ያልጠበቁትን ፈጣን ጎል በ46ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ሽመልስ በቀለ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን በኃይሉ ግርማ በግንባሩ ገጭቶ የቡድኑን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት መቻሎች 52ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ ሳጥን ውስጥ ቦላ የመታው እና ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በጥሩ ቅልጥፍና ያዳነባቸው ከአምስት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ዳዊት ማሞ በማጥቃት ሽግግሩ ተሳትፎ ሳጥን ውስጥ በመግባት ያደረገው ሙከራ ተጫማሪ ጎሎች ለማስቆጠር የተደረጉ ሙከራዎች ነበሩ።

በማጥቃት በኩል ቡድናቸው የተዳከመባቸው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው አቤነዜር አስፋው እና ይገዙ ቦጋለን በማስገባት በቀስ በቀስ ምላሽ ለመስጠት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ 65ኛው ደቂቃ ብርሃኑ በቀለ ከሳጥን ውጭ ግሩም ጎል አስቆጥሯል። በተቆጠረባቸው ጎል ያልተረበሹት መቻሎች ጨዋታውን የበለጠ በመቆጣጠር የሚችሉበትን ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎችን አድርገው በ73ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ማግኘት ችለዋል። አቤል ነጋሽ በጥሩ ዕይታ በተከላካዮች መሐል ያሾለከለትን ከነዓን ማርክነህ በጥሩ አጨራረስ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አድርጎታል።

መቻሎች ካስቆጠሩት ሦስተኛ ጎል በኋላ በጥንቃቄ ሲዳማ ቡናዎች በአንፃራዊነት ወደ ፊት በመሄድ ጫና መፍጠር የቻሉ ሲሆን በተለይ በ86ኛው ደቂቃ ይገዙ ቦጋለ ከርቀት የመታውን እና ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ካዳነበት ኳስ ውጭ ተጠቃሽ የጎል ዕድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ይልቁንም አራተኛ ጎል እንዲቆጠርባቸው ሆኗል። ተቀይሮ ከገባ ወዲህ ተፅዕኖው ከፍ ያለው አቤል ነጋሽ ከሜዳው የግራ ክፍል አንድ ተጫዋች በማለፍ ሳጥን ውስጥ በመግባት ያቀበለውን ከንዓን ማርክነህ በግሩም አጨራረስ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በመቻሎች 4-1 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።


ሽንፈት ያስተናገዱት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በሰጡት አስተያየት በመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታውን መቆጣጠር ችለው የነበረ ቢሆንም ፍፁም ቅጣት ምት መቆጠሩ እና በተለይ ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ እንደገቡ የተቆጠረው ሁለተኛ ጎል ሁሉን ነገር እንዳበላባሸቸው ገልፀው ከነዓንን መቆጣጠር አለመቻላቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው እና ተጫዋቾቻቸው የሚችሉትን መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም ሽንፈቱን ማመን እንደሚገባ ተናግረዋል። ድል የቀናቸው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸው የሲዳማ ቡና አጨዋወት ለበርካታ ጊዜ ማየታቸው እና በአምስት ተከላካይ ሲጫወቱ ነፃ ሜዳ እንደሚያገኙ በማሰብ አጨዋወታቸውን ማስተካከላቸውን ውጤታማ እንዳደረጋቸው ገልፀው። በከነዓን ብቻ ሳይሆን እንደ ቡድን በመጫወታቸው እዚህ መድረሳቸውን ገልፀው በቀጣይ ጨዋታ ከነዓን ባይኖርም በሌሎች ተጫዋቾቻቸው እንደሚተማመኑ አመላክተዋል።