መረጃዎች | 114ኛ የጨዋታ ቀን

ከ18 ዓመታት በኋላ ጊዮርጊስን አሸንፎ ከጦሩ ለማምለጥ ወደ ሜዳ የሚገባው ንግድ ባንክ እና የመጀመሪያው ወራጅ ክለብ ላለመሆን ባልተሟላ ስብስብ የሚፋለመው ሀምበርቾ በየፊናቸው የሚያደርጓቸውን ወሳኝ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ይህ ጨዋታ በዋንጫ ፉክክሩ ላይ የሚፈጥረው ልዩነት የተጋጣሚ ቡድኖችን ብቻ ሳይሆን የሊጉን ተከታታዮች ሁሉ ትኩረት የሳበ ሆኗል።

በመጨረሻው መርሐግብር ከሰባት ሳምንታት ጥበቃ በኋላ ያገኙትን ድል ማስጠበቅ ያልቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአዳማ ከተማ የተነጠቁትን የ5ኛ ደረጃነት ለማስመለስ ከሊጉ መሪ ጋር ይፋለማሉ።

ፈረሰኞቹ በሊጉ ላይ ወጥ ብቃት ማሳየት ከከበዳቸው ቡድኖች መካከል ይጠቀሳሉ። እርግጥ ቡድኑ አሁንም የመከላከል ጥንካሬውን ይዞ መዝለቁ ከተጠባቂው ጨዋታ አንዳች ነገር ይዞ እንዲወጣ ሊያደርገው ቢችልም የግብ ዕድሎች ለመፍጠር አዳጋች የሆነበት አቀራረብ ላይ ለውጦች ማድረግ ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪ
በፈጣኖቹ አጥቂዎች የሚመራው የባንክ የፊት መስመር በነገው ጨዋታ ለፈረሰኞቹ ከባድ ፈተና እንደሚሆን ይታሰባል። ከምንም በላይ በሽግግሮች እና በሁለቱም መስመሮች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የማያቅተውን ተጋጣሚ ለመግታት ልዩ ዝግጅት ማድረግ ሳይኖርባቸውም አይቀርም።


ከተከታታይ ድሎች በኋላ በመጨረሻው መርሐግብር ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ የወጣው ንግድ ባንክ የሦስት ነጥብ ልዩነቱን ለማስጠበቅ ወደ ሜዳ ይገባል። በዋነኛ የዋንጫ ተፎካካሪው መቻል ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ እጅ ያልሰጠው ቡድኑ ልዩነቱን ወደነበረበት ሦስት ነጥብ መልሶ በፉክክሩ ላይ ትንፋሽ ለመውሰድ የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ብቸኛ አማራጩ ነው። ቡድኑ ከአንድ ለዋንጫ የሚፎካከር ቡድን የሚጠበቅ ባሕሪይ ባንፀባረቀበት የመጨረሻው እልህ አስጨራሽ ጨዋታ በከፍተኛ ተጋድሎ ከኋላ ተነስቶ አንድ ውድ ነጥብ ማሳካት ችሏል። ነገር ግን ወደ ጨዋታው ቅኝት ለመግባት የወሰደበት ጊዜ እና የኋላ የኋላ እንዲቸገር ያስገደደው ቀዝቃዛው አጀማመሩ ከእንደነገ ዓይነቱ ወሳኝ ጨዋታ በፊት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ተጋጣሚዎቹ በሊጉ በነበራቸው 36 ያህል ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍተኛ የበላይነት ያለው ሲሆን 24 አሸንፎ ፣ በ9 ጨዋታ አቻ ተለያይተው ንግድ ባንክ 3 ጨዋታ አሸንፏል። ፈረሰኞቹ 67 ጎሎች ሲያስቆጥሩ ሀምራዊዎቹ 19 ጎሎች አስቆጥረዋል። በግንኙነታቸው ንግድ ባንክ ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው በ1998 ዓ/ም ነበር።

ሀምበርቾ ከ ወላይታ ድቻ

በቋፍ ያለው ሀምበርቾ ባልተሟላው ስብስቡ የመጨረሻ የመትረፍ ዕድሉን ለመሞከር የጦና ንቦቹን የሚገጥምበት ጨዋታ የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ነው።

አስቸጋሪ የውድድር ዓመት ያሳለፈው ሀምበርቾ ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ካልቻለ ወደ ከፍተኛ ሊጉ የወረደ የመጀመሪያው ቡድን ይሆናል። በበርካታ የሜዳ ውጭ ጉዳዮች እየተፈተነ የዘለቀው እና ድል ፊቷን ያዞረችበት ቡድኑ በነገው ዕለት በ13 ተጫዋቾች እና ባልተሟላ ስብስብ ወሳኙን ጨዋታ ያከውናል።

የመከላከል ጥምረቱ በአስቸጋሪው ወቅት እጅግ ፈተና የበዛበት የቡድኑ ክፍል ሲሆን ተከታታይ ስድስት ሽንፈቶች በገጠሙባቸው መርሐግብሮች አስራ አምስት ግቦች ለማስተናገድ ተገደዋል።
እንደተጠቀሰው በርከት ያሉ ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ የተከላካይ ክፍል ከፈጣን አጥቂዎች ጋር ሲገናኝ መቸገሩን የቅርብ ጊዜ ጨዋታዎች  ዐሳይቶናል፤ በነገው ዕለትም ከሁለት ጎል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ጠጣሩ የሀድያ ሆሳዕና የመከላከል መዋቅር ላይ ሁለት ግቦች አስቆጥረው ወደዚህ ጨዋታ ከሚቀርቡት የወላይታ ድቻ ፈጣን አጥቂዎች ጋር ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።

ከፊት ያለው የሀምበርቾ ችግር ግን አሁንም ከሌላው የቡድኑ ክፍሎች በተለየ ዋነኛ ክፍተት ሆኖ ዘልቋል። ባለፉት ስድስት ጨዋታዎችም አንድ ግብ ብቻ በማስቆጠር ደካማ ቁጥሮች ያስመዘገበው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ካለ ቋሚ ተሰላፊው አብዱልከሪም ዱግዋ በሚያደርገው የነገው ጨዋታ ይህንን ደካማ ጎን አሻሽሎ መቅረብ ግድ ይለዋል።


ከአራት ተከታታይ ድል አልባ መርሐግብሮች በኋላ ነብሮቹን ረተው ወደ አሸናፊነት የተመለሱት ወላይታ ድቻዎች ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣት የአንድ ደረጃ መሻሻል ያስገኝላቸዋል። በመሪው ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ጉልህ መሻሻሎች ያሳዩት የጦና ንቦቹ ከጠንካራው ባህር ዳር ከተማ ነጥብ ተካፍለው የወጡበት እና በተለይም የማጥቃት አጨዋወታቸው ተሻሻሎ በታየበት ሀድያ ሆሳዕናን ያሸነፉበት ጨዋታ ያሳዩት እንቅስቃሴ የበጎ ለውጡ ማሳያ ነው። የጦና ንቦቹ በቡድናቸው ብቃት እና በተጋጣሚያቸው አስቸጋሪ ሁኔታ መነሻነት ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ አይገመትም።

በ13 ተጫዋቾች ብቻ ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ሀምበርቾዎች ትዕግስቱ አበራን በጉዳት አብዳከሪም ዱግዋን ደግሞ ከክፍያ ጋር በተያያዘ ምክንያት በነገው ጨዋታ አያሰልፉም።

ሁለቱ ቡድኖቹ በታሪካቸው የመጀመርያ የሊግ ጨዋታቸውን ባካሄዱበት መርሐግብር ወላይታ ድቻዎች በቢንያም ፍቅሩ ብቸኛ ግብ ማሸነፋቸው ይታወሳል።