ሚሊዮን ሰለሞን እና ሳይመን ፒተር ቅጣት ተጥሎባቸዋል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር አመራር እና ስነስርዓት ኮሚቴ ተፈጽመዋል ባላቸው የዲስፕሊን ጥሰቶች ዙሪያ ውሳኔ አሳልፏል።


ከሳምንት ሳምንት አጓጊነቱ እየጨመረ የመጣው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እያመራ ይገኛል። ሆኖም በዋንጫ ፉክክሩም ሆነ ባለመውረድ ትንቅንቁ ብዙ ትርጉም የነበራቸውን ጨዋታዎች ባስመለከተው የ28ኛ ሳምንት በርካታ ተጫዋቾች በፈጸሙት የዲስፕሊን ግድፈት ቅጣት ተጥሎባቸዋል።

ከበድ ያሉ ቅጣቶችን ካስተናገዱ ተጫዋቾች መካከል የኢትዮጵያ መድኑ ሚሊዮን ሰለሞን አንዱ ነው። የመሃል ተከላካዩ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበራቸው ጨዋታ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ላይ ምራቁን ስለመትፋቱ ሪፖርት ቀርቦበት ለፈጸመው ጥፋት ስድስት (6) ጨዋታዎች እንዲታገድ እና 3000 (ሦስት ሺህ) ብር እንዲከፈል ተወስኖበታል።

በሌላ ቅጣት ባደጉበት ዓመት ዋንጫውን ለማንሳት እየታተሩ የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች አጥቂ የሆነው ሳይመን ፒተር ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረገው ጨዋታ የተጋጣሚን ተጫዋች በመማታት በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን አራት (4) ጨዋታ እንዲታገድ እና ሦስት ሺህ (3000) ብር እንዲከፍል ውሳኔ ተላልፎበታል።