የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ28ኛ ሳምንት ምርጥ 11


የ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መነሻ በማድረግ ይሄንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አሰላለፍ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ባሕሩ ነጋሽ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከባለፉት ተከታታይ ዓመታት ስኬት አንፃር ዘንድሮ የተቀዛቀዘ የውድድር ዘመን እያሳለፉ የሚገኙት ፈረሰኞቹ በሊጉ መሪ ብልጫ ቢወሰድባቸውም አንድ ነጥብ አሳክተው እንዲወጡ የግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ብቃት እጅግ አስፈላጊው ነበር። በጊዜ አጠባበቅም ሆነ ዕድሎችን በማምከን ንቁ ሆኖ የዋለው ባሕሩ በተለይም ሦስት ግልፅ የጎል ዕድሎችን ያመከነበት መንገድ ልዩ ነበር። በዚህ ሳምንት በነበረው የምርጥ አስራ አንድ ስብስባችን ውስጥ ከሀምበርቾው ምንታምር መለሰ ጋር ተፎካክሮ በስብስብ ውስጥ ሊካተት ችሏል።


ተከላካዮች

አስራት ቱንጆ – ኢትዮጵያ ቡና

እጅግ ፈታኙን የጉዳት ጊዜ አሳልፎ ከሰሞኑ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ እየገባ ያለው አሥራት ወደ ቀድሞ ምርጥ ብቃቱ እየተመለሰ መሆኑን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎቹ ምስክር ናቸው። የቡድኑን የቀኝ መስመር ከኋላ በመነሳት በመምራት ጥቃት በማስጀመር እና ቀድሞ የሚታወቅባቸውን አንድ ሁለት ቅብብሎችን በማድረግ ሳጥኑ ውስጥ በተደጋጋሚ በመግባት ዕድሎችን መፍጠር የቻለው አሥራት በራስ መተማመኑ እየተመለሰለት መሆኑን ዐሳይቷል።

ወልደአማኑኤል ጌቱ – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡናው ተከታታይ አምስተኛ ድሉን ባሳካበት ጨዋታ የመሃል ተከላካዩ በዚህ ሳምንት በራሱ ሳጥን ውስጥ ካለው ከዋና ኃላፊነቱ በላይ የቡድኑን ውጤት ለመቀየር የወሰደው ተነሳሽነት ትኩረትን የሚስብ ነበር። ተጫዋቹ የኢትዮጵያ መድንን የመልሶ ማጥቃት ከማቋረጥ ባለፈ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት የበላይ በመሆን የመድኖችን ቅብብሎች ያቋርጥ ነበር። በተለይ ወገኔ ገዛኸኝ ወደ ጎል የመታው ኳስ ግብ ጠባቂውን በረከትን አልፎ ጎል ተቆጠረባቸው ሲባል ወልደአማኑኤል ጌቱ በጥሩ የመከላከል ብቃት ኳሱ ጎል እንዳይሆን በግንባሩ ወደ ውጭ ያወጣበት መንገድ አስደናቂ ነበር።

ቃለአብ ውብሸት- ሀዲያ ሆሳዕና

በቋሚነት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ለመግባት እየታገለ የሚገኘው ወጣቱ ተከላካይ ቃለአብ ውብሸት የተሰጡትን ዕድሎች በመጠቀም በኩል ችግር እንደሌለበት በተደጋጋሚ እያሳየ ይገኛል። ሀዲያ ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች በኋላ ድሬዳዋ ከተማን በመርታት ወደ አሸናፊነት ሲመለስ ቃለአብ የመከላከል ሥራውን በአግባቡ ከመወጣቱ በላይ የቡድኑን ሁለተኛ ጎል በሚገርም ዕርጋታ ያስቆጠረበት መንገድ በምርጥ አስራ አንድ ስብስባችን ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል።

ዳዊት ማሞ – መቻል

መቻል ካደረጋቸው 28 ጨዋታዎች በ27 ጨዋታዎች ላይ በግራ የተከላካይ መስመር ላይ በወጥነት እየተሰለፈ የሚገኘው ዳዊት ዘንድሮ ቡድኑ ላሳየው ጥንካሬ የራሱን ድርሻ በተገቢው መንገድ እየተወጣ ይገኛል። መቻል ሲዳማ ቡናን በመርታት በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ባሳካበት ጨዋታ ዳዊት በመከላከሉ ረገድ የተሰለፈበትን ኮሪደር ከጥቃት ለመጠበቅ ካሳየው ትጋት በተጨማሪ ወደ ፊት በመሄድ በማጥቃት ረገድ የነበረው ሚና ምርጫ ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

አማካዮች

ግርማ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

ባለ ብዙ ልምዱ ተጫዋች ግርማ በቀለ በሀዲያ ቤት በተለያዩ አማራጭ ቦታዎች በመጫወት ቡድኑን ባለው ልምድ እያገለገለ ይገኛል። የተከላካይ አማካይ በመሆን በዚህ ሳምንት ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው ግርማ የድሬዳዋን የኳስ ፍሰት እንዳይሰምር በተደጋጋሚ እንቅስቃሴዎችን ያቋርጥ የነበረበት መንገድ እና ሀዲያ ሆሳዕና በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተወስዶበት ጫና ውስጥ እንዳይገባ ያደረገበት ሂደት ድንቅ የነበረ ሲሆን የቡድኑን ቀዳሚ ጎል በሚገርም ዝላይ በግንባሩ በመግጨት ያስቆጠረበት ሁኔታ ግርማን በምርጥ አስራ አንድ ውስጥ ያለ ተቀናቃኝ እንዲገባ አድርጎታል።

የአብሥራ ተስፋዬ – ባህር ዳር ከተማ

የጣና ሞገዶቹ ከሁለት ጊዜ መመራት ተነስተው አዳማ ከተማን 3ለ2 ሲያሸንፉ የአማካዩ ብቃት ግሩም ነበር። በተለይም ቡድኑ ገና በ3ኛ ደቂቃ ቀድሞ ቢቆጠርበትም ብዙም ሳይቆይ ወደ ጨዋታው የተመለሰበትን ግብ ከሳጥን ውጪ በአስደናቂ ሁኔታ ማስቆጠር ሲችል ወንድወሰን በለጠ ላስቆጠራት ግብም ቁልፍ መነሻ ነበር።

ኤልያስ ለገሰ – አዳማ ከተማ

አዳማዎች ሁለት ጊዜ መርተው በመጨረሻ ደቂቃዎች በተቆጠሩባቸው ሁለት ግቦች 3ለ2 በተሸነፉበት የባህር ዳር ከተማው ጨዋታው የኤልያስ ብቃት ጎልቶ መታየት ችሏል። አማካዩ 73ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ቢወጣም በቆየባቸው ደቂቃዎች የቡድን የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር ሲችል ለዮሴፍ ታረቀኝ ግብም በድንቅ ዕይታ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

አጥቂዎች


ጋዲሳ መብራቴ – ወልቂጤ ከተማ

ሠራተኞቹ ላለመውረድ በሚደረገው ትንቅንቅ ከሁለት ጊዜ መመራት ተነስተው ከሀዋሳ ከተማ ጋር 2ለ2 ሲለያዩ የመስመር አጥቂው ተቀይሮ ገብቶ የፈጠረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነበር። ጋዲሳ የቡድኑን ሁለት ጎሎች በፍጹም ቅጣት ምት እና በቅጣት ምት ማስቆጠር ሲችል ዕረፍት የለሽ በሆነ እንቅስቃሴ በሰጠው ግልጋሎትም በምርጥ 11 ቡድናችን ውስጥ ተካትቷል።

ፍቃዱ ዓለሙ – ፋሲል ከነማ

ዐፄዎቹ ከተከታታይ ሽንፈቶች አገግመው ሻሸመኔ ከተማን 2ለ1 በመርታት ወደ ድል እንዲመለሱ ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ ዓለሙ እንቅስቃሴ አስፈላጊ ነበር። የቋሚነት ቦታውን ከተነጠቀ ወራት ያስቆጠረው ፍቃዱ አንድ ግብ በፍጹም ቅጣት ምት እና አንድ ግብ በጨዋታ ከመረብ በማሳረፉም የፊት መስመራችንን እንዲመራ ተመርጧል።

ከነዓን ማርክነህ – መቻል

መቻል ሲዳማ ቡናን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት 4ለ1 አሸንፎ ከመሪው ንግድ ባንክ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ሲያጠብ ግዙፉ የመስመር አጥቂ ካደረገው ጠንካራ እንቅስቃሴ ባሻገር የቡድኑን የመጨረሻ ሁለት ጎሎች በድንቅ አጨራረስ በማስቆጠሩ በምርጥ 11 ቡድናችን ውስጥ ተካትቷል።

አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ – ኢትዮጵያ ቡና

የቡናማዎቹን የአሰልጣኝነት መንበር ከተቆናጠጠባት ዕለት ጀምሮ ትልቅ ዋጋ የሚሰጣቸው እልፍ ለውጦች በማምጣት ኢትዮጵያ ቡና ገጥሞት ከነበረው የውጤት መዋዠቅ አላቆ ቡድኑን በሰንጥረዡ ከወገብ በላይ እንዲደላደል ትልቅ ድርሻ የተወጣው አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ተከታታይ ድሎቹን ያስቀጠለበት ውጤታማ ሳምንት አሳልፏል። አሰልጣኙ በተመሳሳይ ውጤታማ ጉዞ ላይ የነበረውን ጠንካራው ኢትዮጵያ መድን ባሸነፈበት እና ተከታታይ አምስተኛ ድሉን በተጎናፀፈበት ዕለት በወሰናቸው ውጤታማ ውሳኔዎችም የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችንን እንዲመራ መርጠነዋል።

ተጠባባቂዎች

ምንታምር መለሰ – ሀምበርቾ
አማኑኤል ተርፉ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
መናፍ አወል – ፋሲል ከነማ
አምሳሉ ሳሌ – ባህር ዳር ከተማ
ባሲሩ ኦማር – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
አብዱልከሪም ወርቁ – ኢትዮጵያ ቡና
ቸርነት ጉግሳ – ባህር ዳር ከተማ
አቤል ነጋሽ – መቻል