በመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች ከቆመ ኳስ መነሻቸውን ያደረጉት የሲዳማ ቡና ሁለት ጎሎች ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማን 2-0 እንዲያሸንፍ አድርገዋል።
ከሽንፈት የተመለሱት ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ ሦስት ለውጦችን አርገዋል። ድሬዳዋ ከተማ ከሆሳዕናው ሽንፈት አንፃር በዳንኤል ተሾመ ፣ መሐመድ አብዱል ላጢፍ እና እያሱ ለገሰ ምትክ አብዩ ካሳዬ ፣ ዳግማዊ አባይ እና ኢስማኤል አብዱልጋኒዩን ሲተካ ሲዳማም ከመቻሉ ሽንፈት በዛብህ መለዮ ፣ ይገዙ ቦጋለ እና ቡልቻ ሹራን በብርሀኑ በቀለ ፣ አበባየሁ ዮሐንስ እና ይስሀቅ ካኖ ቦታ ለውጧል።
የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች የሲዳማ ቡናው አምበል ደስታ ዮሐንስ ልዩነት ፈጣሪ ሆኖባቸው ታይቷል። 5ኛው ደቂቃ ላይ የመስመር ተከላካዩ ያሻማው ከቀኝ የተነሳው የቅጣት ምት አብዩ ካስዬን አልፎ ቋሚውን ገጭቶ ሲመለስ ኢማኑኤል ላሪዬ ጎል አድርጎታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ደስታ ከዛው ወደ ቀኝ ካደላ የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ኳስ በድጋሚ የአብዩ ካሳዬ ድክመት ተጨምሮበት ሁለተኛ ጎል ሆኖ ሲዳማ በጊዜ 2-0 መምራት ጀምሯል።
በጊዜ የተመሩት ድሬዎች የኳስ ቁጥጥር ደርሻቸውን ጨምረው ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ለመግባት ቢሞክሩም ተዳክሞ የታየው የቡድኑ መዋቅር ፍሬ ያለው ዕድል መፍጠር አልቻለም። ይልቁኑም አስፈሪ የነበረው የሲዳማ ቡና መልሶ ማጥቃት መቋጫውን ቡልቻ ሹራ እና ማይክል ኪፕሩቪን በማድረግ ለሦስተኛ ግብ ሲቃረብ ታይቷል። በተለይም 20ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በከፈቱት መልሶ ማጥቃት ይገዙ ቦጋለ ሳጥን ውስጥ ያመቻቸለትን ኳስ ቡልቻ ሹራ ሞክሮ አብዩ ጨርፎት ነበር ለጥቂት የወጣበት።
አሰልጣኝ ሽመልስ አበበ 35ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ሀሰንን በአሜ መሐመድ በመቀየር ካርሎስ ዳምጠውን ከአማካይ ወደ ፊት እስካመጡበት ድረስ በእንቅስቃሴ ሲዳማዎች በበላይነት ዘልቀዋል። በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች የጨዋታውን ሚዛን ማሻሻል የቻሉት ድሬዎች 36ኛው ደቂቃ ላይ ለጎል ቀረበው ነበር። ተመስገን ደረሰ ከኤልያስ አህመድ የደረሰውን ተንጠልጣይ ኳስ በመክብብ ደገፉ አናት ላይ ለማስቆጠር ሞክሮ ወደ ላይ ተነስቶበታል ።
አካላዊ ንክኪ በርከት ብሎበት በጀመረው ሁለተኛ አጋማሽ ጠንካራ ሙከራዎች ባይታዩም የመሀል ሜዳ ፍልሚያው ከፍ ብሎ ነበር። ሆኖም 63ኛው ደቂቃ ላይ የስታድየሙ መብራት መጥፋት ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ይልቅ አነጋጋሪ ክስተት ሆኖ ታይቷል። ከ10 ደቂቃዎች በኋላ መብራቱ ተመልሶ ጨዋታው ሲቀጥል በጠንካራ ሙከራ ባይታጀብም ሲዳማ ቡና በተሻለ የኳስ ቁጥጥር እና በቀኝ መስመር ከደግፌ ዓለሙ በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ጫና ሲፈጥር ተስተውሏል።
በጨዋታዎቹ ቀሪ ጨዋታዎች ቡድኖቹ አልፎ አልፎ በእንቅስቃሴ እና ከቆሙ ኳሶች መነሻነት የግብ ዕድል ለመፍጠር ሞክረዋል። ሆኖም በጉሽሚያዎች ይቆራረጥ የነበረው ጨዋታ እምብዛም ማራኪ ሳይሆን እስከ ፍፃሜው ዘልቋል። ጨዋታው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የድሬዳዋ ከተማው አጥቂ ካርሎስ ዳምጠው ኢላማውን ባልጠበቀ አደገኛ የግንባር ሙከራ እና መክብብ ደገፉን በፈተነ የረጅም ርቀት የቅጣት ምት ድሬዳዋን ለአቻነት ቢያቀርብም ሳይሳካለት ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ ውጤት በሲዳማ ቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የዛሬውን ሽንፈት ከላፈው ጨዋታ ሽንፈት ጋር ሲያመሳስሉት ኮማንደር ሽመለስ አበበ መብራቱ መቀዛቀዝን መፍጠሩን ጠቅሰው ካርሎስ ዳምጠው ከአማካይ ይልቅ ፊት መስመር ላይ የተሻለ እንደሚሆን ሲያስረዱ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ጎል ማስተናገዱ የቡድኑ ደካማ ጎኑ መሆኑን አንስተዋል። አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በበኩላቸው ቡድኑ የተሻለ ተረጋግቶ መታየቱን እና በኳስ ቁጥጥር ላይ መመስረቱን አስረድተው በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ ብሎ መጨረስ ለቀጣይ ጊዜያት ያለውን ትርጉም በማንሳት ቀድሞ ጎል ማስቆጠር ያለውን ዋጋም አብራርተዋል።