የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተካፋዩ ክለብ ሀዲያ ሆሳዕና ለወዳጅነት ጨዋታ እና ለገቢ ማሰባሰቢያ ወደ ፕሪቶሪያ ያመራል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ እየተወዳደረ የሚገኘው የሀዲያ ሆሳዕና እግር ኳስ ቡድን ራሱን በገቢ ለማጠናከር ይረዳው ዘንድ በቀጣዩ ሳምንት የሊጉን መጠናቀቅ ተከትሎ ወደ ደቡብ አፍሪካዋ ሀገር ፕሪቶሪያ ያመራል። በትላንትናው ዕለት በክለቡ መቀመጫ ከተማ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አባተ ተስፋዬ እና የወዳጅነት ጨዋታውን ያዘጋጀው የፊፋ የጨዋታ ኤጀንት ፍጹም አድነው በጋራ መግለጫውን ሰጥተዋል።
በመግለጫው እንደተገለፀው ሀዲያ ሆሳዕና ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጠናቀቅ በኋላ ወደ ፕሪቶሪያ በማምራት በደቡብ አፍሪካ ናሽናል ዲቪዢን ላይ ተሳታፊ በሆነው ጂ ዲ አር ስታር ከተባለው ክለብ ጋር የወዳጅነት ጨዋታን የሚያደርግ ሲሆን በመቀጠል የገቢ ማሰባሰብ መርመግብርም ይኖራል ተብሏል። ይህ የወዳጅነት ጨዋታ በሁለቱ ሀገራት መካከል ጥብቅ የሆነ ወዳጅነት ከመፍጠሩም በላይ ለተጫዋቾች እና ለአሰልጣኞች የኢንተርናሽናል የጨዋታ ልምድ የሚያገኙበት መሆኑን እና ክለቦች ከጨዋታው ባሻገር ደጋፊዎቻቸውን የሚያደራጁበት እና ቡድኑን ሕዝባዊ መሠረት ለማስያዝ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው የውድድሩ አዘጋጅ የፊፋ የጨዋታ ኤጀንት ኢንጅነር ፍጹም አድነው ገልፀዋል። ጨዋታውን በዚህ ወቅት ማከናወን ለምን ተፈለገ? እና ቀጣይ እንዲህ ዓይነት የወዳጅነት ጨዋታዎች ለሌሎች ክለቦች ለማዘጋጀት የታቀደ ዕቅድ አለ ወይ? ተብሎ ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ የወዳጅነት ጨዋታውን በዚህ ወቅት ለማድረግ ዕቅድ እንዳልነበረ እና ቀድሞ የተያዘ ፕሮግራም ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ተገፍቶ የመጣ ፕሮግራም እንደሆነ ጠቅሰው በቀጣይ ሌሎች ክለቦችንም ወደ ተለያዩ ሀገራት ወስደው የማጫወት ዕቅድ እንዳላቸው የውድድሩ አዘጋጅ ተናግረዋል።
የሀዲያ ሆሳዕና ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ አባተ ተስፋዬ በበኩላቸው ይህ የወዳጅነት ጨዋታ ከክልል ክለቦች የመጀመሪያው እንደመሆኑ መጠን ታሪካዊ እንደሚያደርገው ገልጸው ጨዋታው ሐምሌ 6/2016 ዓ.ም በሀዲያ ሆሳዕና እና በጂ ዲ አር ክለብ መካከል የሚደረግ መሆኑን በመናገር የጨዋታው ዓላማ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ ተጨዋቾችን ለተለያዩ ክለቦች የመታየት ዕድልን እንደሚያሰፋላቸው የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ እንደሚያገኙ እና በተጨማሪም የክለቡ ጽሕፈት ቤት የፋይናንስ አጠቃቀም በስፖርቱ የባለሀብቶች ተሳትፎ የደጋፊዎች ድርሻ የአካዳሚ እና የስታዲየም ግንባታ ፣ የታዳጊ ወጣቶች ምልመላ ስርዓት ፣ የተጫዋቾች የዝውውር ሂደት እና የደመወዝ ክፍያ ስርዓታቸው ተሞክሮ የሚያገኙበት መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል። ሐምሌ 3 የክለቡ የልዑካን ቡድን አባላት ወደ ስፍራው የሚያመሩበት ቀን እንደሚሆን ይጠበቃል።