ሪፖርት | የጦና ንቦቹ እና አፄዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል

ሁለት ጥራት ያለው ሙከራ ብቻ የተደረገበት የወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል።

በሊጉ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታን ከሀምበርቾ ጋር ያለ ጎል የፈፀሙት ወላይታ ድቻዎች የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገው ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርቡ በዚህም አበባየሁ ሀጂሶ ፣ አብነት ደምሴ እና ብሥራት በቀለን በማሳረፍ መሳይ ኒኮል ፣ ፊኒያንስ ተመሰገን እና ባዬ ገዛኸኝ በቋሚነት ሲተኩ ሻሸመኔ ከተማን በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት የረቱት ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው የአራት ተጫዋቾችን ለውጥ ያደረጉ ሲሆን ዮናታን ፍሰሃ ፣ ሽመክት ጉግሳ ፣ ጋቶች ፓኖም እና ናትናኤል ማስረሻን በምኞት ደበበ ፣ አቤል እያዩ ፣ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እና ፍቃዱ ዓለሙ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።

በፀሐያማ የዐየር ፀባይ ውስጥ ሆኖ የተደረገው የቡድኖቹ ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች ተመሳሳይ የጨዋታ ቅርፅን ያስተዋልን ቢሆንም በሂደት ሳጥን ጠርዝ ደርሶ በጨዋታው ሙከራን ከማድረግ አኳያ ግን በእጅጉ ወረድ ያለ አቀራረብን አስተውለናል። በቀኝ መስመር በኩል የሚደረጉ አጨዋወቶች በይበልጥ በተበራከቱበት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች በአንፃራዊነት ወላይታ ድቻዎች በተደራጀ ሽግግር ለመንቀሳቀስ ጥረቶች ሲያደርጉ ብንመለከትም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ደርሶ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ፍጹም ዝንጉዎች ሆነው ታይተዋል።

በቀላሉ ወደ ጨዋታው ለመግባት ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ለመጠበቅ የተገደዱት ዐፄዎቹ ከመሐል ሜዳ መነሻቸውን ባደረጉ ኳሶች የጥቃት መነሻቸውን ከመስመር በማድረግ የታተሩት ዐፄዎቹ ከቆመ የቅጣት ምት ኳስ ጌታነህ ከበደ መትቶ በግቡ አግዳሚ ብረት ወደ ውጪ የወጣችዋ ዒላማዋን ያልጠበቀች አጋጣሚ በጨዋታው 40 ደቂቃዎችን ጠብቀን የተመለከትናት ጥራት አልባ ሙከራ ሆናለች። በብዙ መልኩ የወረዱ ፉክክሮችን እያስመለከተን ጨዋታው ቀጥሎ 44ኛው ደቂቃ ላይ በድቻ በኩል ናታን ጋሻው የሳማኪን ከግብ ክልል መውጣት ተመልክቶ ያደረጋት እና በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ወደ ውጪ ኳሷ ከወጣች በኋላ አጋማሹ ያለ ጎል ተጋምሷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ከፍ ባለ ተነሳሽነት የተመለሱት ወላይታ ድቻዎች መሐል ሜዳውን በመቆጣጠር በተለይ የብዙዓየሁ ሰይፉን ንክኪ በመጠቀም ዕድሎችን በመፍጠር ከተጋጣሚያቸው ፋሲል ከነማ ተሽለው ቀርበዋል። 54ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ከግራ ናታን ጋሻው እየገፋ የሄደውን ኳስ በአግባቡ ሰንጥቆ ያቀበለውን ብዙዓየሁ ወደ ጎልነት ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ ሳማኬ ሚኬል መክቶበታል። በ56ኛው ደቂቃ ላይ የተጫዋች ለውጥን ጭምር በማድረግ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች የጥቃት ምንጫቸው አድርገው የተንቀሳቀሱት ዐፄዎቹ ዕድሎችን ልዩነት ፈጥሮ ለመገኘት ያደረጉት ጥረት ግን ደካማ ሆኖ ታይቷል።

በአንፃሩ በአጋማሹ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመድረስ የተዋጣላቸው ድቻዎች 60ኛው ደቂቃ ላይ ብዙዓየሁ በፋሲል ተከላካዮች መሐል ለመሐል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ወጣቱ ናታን ጋሻው ወደ ግብነት ለወጠው ሲባል ሳማኬን በቀላሉ አሳቅፎታል። 72ኛው ደቂቃ ላይ በፋሲሎች በኩል ከቆመ ኳስ ኤልያስ ማሞ ያሻገረውን ኳስ ፍቃዱ ዓለሙ በግንባር ገጭቶ የግቡን መረብ ታካ ኳሷ ወጥታለች። የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች ወረድ ባለ መቀዛቀዝ ውስጥ ጨዋታው ቀጥሎ ፋሲሎች 90+4 ላይ ዳግም አወቀ ከርቀት አክርሮ መትቶ ቢኒያም ገነቱ ካመከናት በኋላ ጎል ሳይቆጠርበት 0ለ0 መቋጫውን አግኝቷል።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ በተሰጡ የአሰልጣኝ አስተያየቶች የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጨዋታው መጥፎ እንዳልነበር ጠቁመው በመጀመሪያው አጋማሽ አየሩ ከባድ መሆኑን እና የተቀዛቀዘ ጨዋታም መታየቱን ጠቁመው በሽግግር ተጋጣሚያቸው ሲመጣ በቡድናቸው ላይ መጠነኛ ክፍተት እና የመደራጀት ችግር እንደታየ አክለው ተናግረዋል። የወላይታ ድቻ አቻቸው ያሬድ ገመቹ በአንጻሩ ጥሩ ጨዋታ እንደነበር የተገኙ አጋጣሚዎችን ግን ወደ ጎል በመቀየሩ ረገድ ችግሮች መታየታቸውን ገልጸው ከልምድ ማነስ አኳያ ናታን ጋሻው ያገኛቸውን መልካም ዕድሎች ማባከኑንም አያይዘው ገልፀዋል።